
(ብ/ም/ቤት 4ኛ ዓመት 2ኛ ልዪ አስቸኳይ ስብሰባ ጳጉሜ 1 ቀን 2008 ዓ.ም)
ሰማያዊ ፓርቲ ከግንቦት 16/2007 ምርጫ ማግሥት ጀምሮ በተደጋጋሚ እንደገለጸው፣ ያለ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ሥልጣን ኮርቻ ላይ መቆየት የሕግም ሆነ የሞራል ርካብ የለውም በማለት ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን፣ ኢህአዲግ መራሹ መንግሥት የግንቦት 2007ቱን ምርጫ መቶ በመቶ (100%) አሸንፌያለሁ በማለት ከተኩራራበትና ከተመፃደቀበት ቀቢጸ-ተስፋ በአንድ አመት ውስጥ ጀግኖቹ የኦሮሞና የአማራ ክፍለ ሀገር ወጣቶች አባነው ቀስቅሰውታል፡፡
በሙስና፣ በዘረኝነትና በሥልጣን ዋልጌነት የሚምነሸነሸው ኢህአዲግ መራሹ መንግሥት፣ ዳግም ላያንቀላፋና በኢትዮጵያውያን ላይ እንዳይፈናጠጥ ቆራጦቹ የኢትዮጵያ ልጆች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ድረስ እንቢተኝነታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ የሕዝባዊ እንቢተኝነቱም ይዧቸው የተነሳው ብሶቶችና ምሬቶች ሁሉ፡- የመብት፣ የመሬት ባለቤትነት፣የእምነት ነፃነት፣ የማንነት፣ እና የሕዝባዊ መንግሥት የማያወላውል ፍላጎቶች እንጂ፣ የህወሓት/ኢህአዲግ ሹማምንት ሊያሽሞነሙኑት እንደሚሹት “የኢኮኖሚ ዕድገት ያመጣው፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ” አይደለም፡፡
ህውሓት/ኢህአዲግ/መራሹ አገዛዝ ላለፉት ሃያ አምስት (25) አመታት እና ከዚያም በፊት በበረሃ ቆይታቸው ወቅት ጭምር የተዘራውና የተኮተኮተው ዘረኝነት፣ አገራችንን ከፋፍሎ ለመግዛት የጭፍን ብሔረተኝነት የሥልጣን ጥማት ማሣያ እንደሆነ የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ይረዳል፡፡ ይህንን ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ፣ በንቃትና በትጋት ሲከታተለው የነበረው፣ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የሐረሪ፣ የሱማሌ፣ የአፋር፣ የጋንቤላና የቤንሻንጉል ክፍለ አገር ኢትዮጵያውያን፣ በአንድ ድምጽ “ዘረኝነት በቃን! ከፋፋዮችም ዞር በሉልን !” እያሉ ነው፡፡ እጅግ የሚያመረቃና ከፍተኛ ኃይልና ግርማ ያለው ሕዝባዊ ድምጽ ነው፡፡

ነገሩን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው እራሳቸውን ከየትኛውም አድጋ ለመከላከል የማይችሉ እሰረኞች፣ በእሳት እና በጥይት ተቃጥለው እና ተደብደበው ሕይወታችውን እንዲያጡ መደረጉ ፍፁም አረመናዊነት ተግባር ነው፡ የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ይህን ዘግናኝ ተግባር አጥብቆ ያወግዛል፡፡ በተለይ በዚህ አረመናዊ ድርጊት ሕይወታቸውን ያጡ እነማን እንደሆኑ አለመታወቁ የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት በእጅጉ እያሳስበዋል፡፡ በመሆኑም ሕይወታቸውን ያጡ እና ጉዳት የደረሳባቸው እነማን እንደሆኑ በአስቸኳይ ያሰራቸው አካል እንዲገልጽ እናሳስባለን፡፡ በአማራ እና በኦርሚያ ክፍለ አገር እየተካሄደ ባለው ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ፣የተሰውት ኢትትዮጵያውያን ሁሉ፣ የተጀመረው የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ትግል ሰማዕታት በመሆናቸው ክብር ይገባቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ የኢትዮጵያውያን ደም በፍርድ አደባባይ እንደሚጠየቁ የዛሬዎቹ ባለሥልጣናትም ሆኑ ግብረ-አበሮቻቸው ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል፡፡
በመጨረሻም፣ የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤትና መላው የፓርቲው አባላት፣ ከሚደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትና የሉዓላዊነት ማረጋገጥ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ጎን፣ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የሚሰለፉ መሆናቸውን በአንድ ድምጽ ያረጋግጣሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በዘረኝነት፣ በአድሎአዊነት፣ በከፋፋይነትና በእኔ ብቻ ልብላው በሚሉ ሕገ-አራዊት የሆነ የጭፍን አገዛዝና የፖለቲካ ደባ ለመቃወም የሚደረገው ሕዝባዊ እንቢተኝነት እና ተቃውሞ፣ትክክለኛው ምላሽ የሥርዓት ለውጥ ብቻ ነው !!! ክብር ለተሰው የኢትዮጵያ ወጣቶችና የለውጥ ታጋዮች በሞላ! ክብር የሥልጣን ባለቤት ለሆነውና ለሉዓላዊው የኢትዮጵያ ሕዝብ! ክብር ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ ፈላጊዎችና ታጋዮች! ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
No comments:
Post a Comment