Sunday, September 4, 2016

መቋጫው የሚናፈቀው ትኩሳት ኢኮኖሚውን መጫን ጀምሯል:: (ብርሃኑ ፈቃደ )

መቋጫው የሚናፈቀው ትኩሳት ኢኮኖሚውን መጫን ጀምሯል:: (ብርሃኑ ፈቃደ )


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከምን ጊዜውም ይልቅ በውስጣዊ የፖለቲካ ትኩሳት ተጠምደዋል፡፡ በውጭ ሲካሄዱ የሰነበቱ ትልልቅ የኢኮኖሚ ስብሰባዎች ላይ እንደሚገኙ ሲጠበቁ የውኃ ሽታ ሆነዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ኬንያ ያስተናገደችው የጃፓን አፍሪካ ኮንፈረንስ፣ በመጠሪያው ቶኪዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ከአፍሪካ ልማት (ቲካድ) በመላ አኅጉሪቱ የሚገኙ አገሮችና ዋና ዋና መሪዎች ሲታደሙ፣ እሳቸው አገር ቤት እዚህም እዚያም እየተነሳ ፋታ በነሳቸው ተቃውሞና ተቃውሞውን ተንተርሰው እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች፣ የሰው ሕይወት፣ የንብረት መውደምና የመሠረተ ልማቶች መፈራረስ ችግሮችን እንዴት እንደሚያስቆሙ መላ በማፈላለግ ሥራ ላይ ተጠምደው ሰንብተዋል፡፡
በዚህ ሳምንት በሩዋንዳ፣ ኪጋሊ ከተማ በሚካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ መገኘታቸውም አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ ቀስ በቀስ እየተዛመተና ሥር እየሰደደ የመጣው ግጭት ከሳምንት ሳምንት፣ ከወራት ወራት እየቀጠለ ማባሪያ ያጣ ሆኗል፡፡ በግጭቱ ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ለጉዳት መዳረግ ጀምረዋል፡፡ የአበባ እርሻዎች፣ የአትክትልና ፍራፍሬ አምራቾች፣ የሲሚንቶ ፋብሪካ የጉዳት ሰለባ መሆን ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ የውጭ ኩባንያዎች ለቀው የመውጣቸው ነገር አይቀሬ መሆኑ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በአሮሚያ ክልል የተቃጠሉ የአበባ እርሻዎች፣ የተዘረፉ ፋብሪካዎችና ሌሎችም ያሳደሩት ሥጋት ሳይገፈፍ፣ በባህር ዳር ከተማ ግምቱ ከአሥር ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚገመት የአበባ እርሻ መውደሙ ተሰምቷል፡፡ ባህር ዳር በሆርቲካልቸር ዘርፍ በተለይም በአትክልት፣ ፍራፍሬና በአበባ እርሻ መስክ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ዘግይታ የገባች ከተማ ነች፡፡ ዳያስፖራዎችና የውጭ ኢንቨስትሮች ወደ ባህር ዳር እንዲገቡ ሲወተወቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተነሳው ግጭት ሳቢያ ግን እርሻዎቻቸው መቃጠል፣ አንዳንዶቹም እስከ 500 ሠራተኞችን ለመበተን ተገደዋል፡፡ ሌሎችም ኢንቨስተሮች የደረሰባቸውን ጉዳትና ኪሳራ ሪፖርት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ነገሮች ከመረጋጋትና ከመስከን ይልቅ ከባድ ጉዳት ማስከተል በመጀመራቸው ከውጭ ሊመጡ የነበሩ ኢንቨስትሮች የጉብኝት ጊዜያቸውን ላልተወሰኑ ጊዜያት ማራዘም ጀምረዋል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ከአሜሪካ ሊመጡ ቀን ቆርጠው የነበሩ ትልልቅ ኩባንያዎች፣ በደኅንነት ጉዳዮች አማካሪዎች ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ሊያድርጓቸው የነበሩ ጉብኝትዎችና የቢዝነስ ውይይቶች እንዲራዘሙ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከወዲሁ አገሪቱ እያስመዘገበችው ባለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ከወዲሁ ሥጋት እያሳደረ ነው፡፡
መንግሥት ወቅታዊው ትኩሳት ከቁጥጥሩ ውጭ እንዳልሆነ፣ ጥያቄዎቹም ከሕዝብ ብቻም ሳይሆን ከ‹‹ኢትዮጵያ ጠላቶች›› እየሠረጉ በመግባት ሰላም እያደፈረሱ እንደሚገኙ በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህም ገፍተው አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ የፀጥታ አካላትን አዘዋል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ላይ የሚገኘው አገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ኢኮኖሚው ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ከወዲሁ ትኩረት መሳብ ጀምሯል፡፡ ግጭቱ እንዲቆም የሚጠይቁ አካላት፣ መንግሥት ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ፣ ትክክለኛ ጥያቄ የሚያቀርበውና መንግሥትን የሚቃወመው ሕዝብም የወደፊቱን በማስተዋል እንዲንቀሳቀስ የሚጠይቁ፣ ከውጭ ኢንቨስትሮችን በማስመጣት አገር ውስጥ ኩባንያዎቻቸውን እንዲያቋቁሙ እያገዟቸው ያሉ ዜጎችም ተማጽኗቸውን እያሰሙ ነው፡፡
ከሰሞኑ በሚካሄዱ የንግድና የኢንቨስትመንት ስብሰባዎች ጎን የሚደረጉ የእርስ በርስ የጎንዮሽ ጭውውቶች ወቅት ሲነገር እንደተደመጠውም፣ ነገሮች ከሚገባው በላይ ከመካረራቸው ቀድሞ፣ በመብት ላይ ተመርኩዘው የሚቀርቡ ጥያቄዎችም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመሩ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ይሸማገል፣ የአገር ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብተው መንግሥትና ሕዝብን እንዲዳኙ ሐሳብ የሚያቀርቡም ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ዱሮ ኧረ በባንዲራው፣ ኧረ በኢትዮጵያ አምላክ እየተባለ የተቀጣጠለ እሳት እንዲበርድ፣ ያጠፋም ያለማም በአውጫጭኝ የሚሟገትበት አካሄድ እንዲመጣ ቀናዔዎች መነሳት አለባቸው፤›› የሚሉ ምክረ ሐሳቦችን የሚሰነዝሩ አንጋፋ ባለሀብቶችም ታይተዋል፡፡
እንዲህም ተደርጎ የተነሳው ግጭት በቶሎ ባይቆም ሊከሰት የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያየለ እንደሚመጣ ተቋሚዎችን በመጥቀስ የሚሰነዘሩ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያዎች መበራከት ጀምረዋል፡፡ ከሳምንታት በፊት፣ አራተኛ መደበኛ ጉባዔውን ያካሄደው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ምክር ቤት አባላት፣ ለምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል፣ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማኅበር ያቀረበው ይጠቀሳል፡፡
የሆቴል ባለንብረቶቹ ማኅበር በፕሬዚዳንቱ በአቶ ብንያም ብሥራት አማካይነት ያቀረበው ጥያቄ በወቅቱ ትኩሳት ምክንያት የቱሪዝምና የሆቴል ዘርፉ ላይ ያነጣጠረውን ተፅዕኖ ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ ከመላው አፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ በብቸኝነት ያለ ምንም ሥጋት መጓዝ የሚቻልባት አገር ተብላ ትጠቀስ እንደነበር የገለጹት አቶ ብንያም፣ እ.ኤ.አ. ከ2015 መጨረሻ ወዲህ ግን የጉዞ ምክር ብሎም እንዳትሄዱ የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች መውጣት ጀምረዋል፡፡ ለቱሪዝም ተመራጭ አገር መሆኗም ሲነገር ቆይቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ መጎብኘት የሚገባት አገር መሆኗን ለዓለም ካወጀ ጥቂት ጊዜ ነው፡፡
ይሁንና የደፈረሰው ሰላምና ፀጥታ ግን የሰዎችን ሕይወትና የቀን ተቀን ኑሮ ከማወክ አልፎ፣ የኢኮኖሚውን ተዋናዮች መነካካት አብዝቷል፡፡ አገሪቱን ከጎበኙ 700 ሺሕ ያህል የውጭ ዜጎች፣ እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ያስገኘው የቱሪዝም ዘርፍ፣ በእንዲህ ያለው ጊዜ ከሌሎች ኢንዱስሪዎች ሁሉ በጣም የሚረበሽና ለማገገምም ጊዜ የሚወስድበት ስለመሆኑ፣ የኢትዮጵያ አስጎብኝዎች ማኅበር ፕሬዚዳትንት አቶ ያዕቆብ መላኩ ይገልጻሉ፡፡ እየታዩ ያሉት ችግሮች በተለይ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ከፍተኛ ቱሪስቶችን የሚያስተናግው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ሥጋት አሳድረዋል፡፡ ከፍተኛ ውጥረት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜኑ ክፍል ከፍተኛ ጎብኝዎች የሚጎርፉበት በመሆኑ፣ ነገሮች ወደ ነበሩበት ቦታ ቢመለሱ እንኳ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ወዲያውኑ ሊስተካከል እንደማይችል አስግቷል፡፡
አሜሪካ ያወጣችው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ለሰባት ወራት የሚቆይና ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የሚከለክል ነው፡፡ እንግሊዝና ጀርመንም የጉዞ ማስጠንቀቂያ በማውጣት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች እንዲሰርዙ እያስገደዱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የቱሪዝም ዘርፉ በአፋጣኝ ያገግማል ተብሎ ባይጠበቅም፣ አሁን ያሉትን ነገሮች መቀልበስ የሚቻልባቸው አካሄዶች እንዳሉ አቶ ያዕቆብ ይገልጻሉ፡፡
አንደኛው ሰሞኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድ በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው አንዱ ማሳያ ነው ያሉት አቶ ያዕቆብ፣ በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገር ውስጥ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትን በመጥራት ስለወቅቱ ሁኔታ ማብራሪያ መስጠቱ አንዱ እየወጡ ያሉ የጉዞ እገዳዎችን የማስቀልበሻ መንገድ እንደሚሆን አቶ ያዕቆብ ያምናሉ፡፡
ምንም እንኳ የአዲስ አበባ ትልልቅ ሆቴሎች እስካሁን ይህ ነው የሚባል የስብሰባ መሰረዝም ሆነ የተሳታፊዎች መቅረት ባያጋጥማቸውም፣ ነገሮች እየተባባሱ ከቀጠሉ ግን ጉዳዩ የኢንዱስትሪው ብቻም ሳይሆን የአገር ህልውና ስለሚሆን፣ መንግሥት ነገሮችን በተቻለው አቅም ሁሉ ቀድሞ ወደነበሩበት የተረጋጋና ሰላማዊ ሥርዓት ማስፈን እንደሚጠበቅበት ሆቴሎች ይገልጻሉ፡፡
መንግሥት ከቱሪዝም ዘርፍ ከሚያገኘው ቢሊዮን ዶላሮች የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሻገር፣ በያመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኝዎችና ቱሪስቶችም እንዳይቀሩ የማድረግ ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡
አገሮች በአሸባሪዎች ጥቃትም ሆነ በእርስ በርስ ግጭት ሳቢያ በሚያጋጥማቸው አለመረጋጋት ሳቢያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪያቸውን ከአደጋ ለመከላከል በርካታ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሲገደዱ ይስተዋላሉ፡፡ በኬንያ የዌስትጌት የገበያ ሥፍራ ላይ የደረሰው የሽብር ጥቃትም ሆነ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተሰነዘረው ጭፍጨፋ፣ መላ አገሪቱ ላይ የተንሰራፋ ችግር እንዳልሆነ በማግባባት ቱሪዝም ዘርፉ የቁልቁል እንዳይጓዝ ለመታደግ ሲጣጣር ታይቷል፡፡ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ቱኒዝያና ሌሎችም አገሮች በዚህ መንገድ የቱሪዝም ኢንዱስትሪያቸውን ለመታደግ ሲሞክሩ እንደነበር አቶ ያዕቆብ አብራርተዋል፡፡
እንደ ግብፅ ያሉ አገሮች በደረሰባቸው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ሳቢያ በከፍተኛ የቱሪዝም መዳረሻነታቸው የሚታወቁ ከተሞቻቸው ሰው ዝር የማይልባቸው እስከመሆን ደርሰው ቆይተዋል፡፡ ለአብነት ሻርም ኤል ሼክ በግብፅ ከሚገኙ የሪዞርት ከተሞች መካከል በሰፊው የምትጠቀስ፣ በአውሮፓውያን የምትጥለቀለቅ ከተማ ነች፡፡ ሆኖም በሩስያ የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ በደረሰ ጥቃት ምክንያት ወደዚያች ከተማ ዝር የሚሉ አውሮፓውያን ታጥተዋል፡፡ ቀስ በቀስ በቁሟ ማንቀላፋት ለጀመረችውና ብቸኛ የኢኮኖሚዋ ዋልታ የሆነውን ቱሪዝም ለመታደግ፣ የግብፅ መንግሥት ልዩ ልዩ ስበሰባዎችን ስፖንሰር እያደረገ ወደ ከተማዋ የመውሰድ ዘመቻ ጀምሯል፡፡
ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው በመለስ በሌሎች ኢኮኖሚው ዋልታዎች ላይም የሚታዩ ጫናዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ የምርት ሒደትና አቅርቦት መቀዛቀዝ፣ የዋጋ መናር፣ ከፍተኛ የምርት ማጓጓዣ ችግሮች መበራከት በአገሪቱ እየታዩ፣ ኢኮኖሚውን ጫና ውስጥ ሊከቱ የተቃረቡ አንኳር ችግሮች ሆነው ታይተዋል፡፡
የሸቀጥ ዕቃዎች ዋጋ ቀስ በቀስ በማሻቀብ ላይ መሆኑም ለመንግሥት ራስ ምታት በመሆን በያቅጣጫቸው የሚፈታተኑ ችግሮች መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ ለአብነትም አንድ ኩንታል ጤፍ፣ ማኛው በ1,900 ብር ይገበይባቸው የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ገበያዎች፣ በአሁኑ ወቅት ከ2,500 ብር በላይ እየጠየቁ፣ በርካቶችም በሥጋት ምክንያት ከወትሮው የፍጆታ ኮታቸው በላይ የምግብ ሸቀጦችን ሲሸምቱ መታየት ጀምረዋል፡፡
ይህ ሁሉ ክስተት ቀስ በቀስ ጫናው እየጎላ የሕዝቡም ሆነ የውጭ ዲፕሎማቶችን መተማመን ሥጋት ላይ እየጣለ ቢገኝም፣ መንግሥት ግን አሁንም ቢሆን ነገሮች ከቁጥጥሩ ውጭ እንዳልሆኑ እየገለጸ ይገኛል፡፡ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡም ይህንኑ በማሳወቅ ተደምጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰበሰቡት የቱሪዝም ምክር ቤትም ነገሮች ከመንግሥት አቅም በላይ አለመሆናቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለጹ ይታወሳል፡፡
አገሮች በየጊዜው የሚያወጧቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያዎችና እገዳዎችም ቢሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቀለበሱ ሲደረግ መቆየቱን የገለጹበት ጊዜ ግን ያለፈ ይመስላል፡፡ በስብሰባው ወቅት ‹‹ነገሮች ኮሽ ባሉ ወቅት የጉዞ ማስጠንቀቂያ የሚያወጡ አገሮች 48 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲያነሱ እያደረግን ነው፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ግን ከ48 ሰዓትም በላይ ለሰባት ወራት የሚቆይ ማስጠንቀቂያ አውጥተዋል፡፡ ሌሎችም እየተከተሉ ነው፡፡
ነገሮች በሚባሉት አቅጣጫ ብቻም ሳይሆን እየተባባሱ ባሉበት ወቅት ስለ ንግድ ተቋማት እንቅስቃሴ አለያም ስለኢንቨስትመንት ከማውራት፣ ቀድሞ ስለ አገርና ስለ ሰዎች ሕልውና መነጋገሩ ቀዳሚ መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥትንና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት የሚማጸኑም አልታጡም፡፡

No comments:

Post a Comment