Wednesday, September 28, 2016

ጸረ ነፍጠኛ ግንባር?! (የነስብሐት ነጋ የጥፋት ድግስ!)



ጸረ ነፍጠኛ ግንባር?!
(የነስብሐት ነጋ የጥፋት ድግስ!) Image result for sebhat nega



አንድ የማከብራቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ወያኔ በአማራ ሕዝብ እምቢተኝነትና አይበገሬነት ስለተርበተበተ፣ ይህን ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለመነጠል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው በማለት በቅርቡ የታዘቡትን አጫውተውኛል፡፡ እኚህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኅብረትና ለአገራችን አንድነት ፍጹም ቀናኢ የሆኑ የፖለቲካ ሰው እንደገለጹልኝ፣ ሰው በላው ስብሐት ነጋና ሌሎች የወያኔ መሪዎች የተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያና የኦሮሞ ፖለቲከኞችን እየቀረቡ፣ ከአማራ ውጪ ያሉት ሕዝቦች ጸረ ነፍጠኛ ግንባር ካልፈጠሩና የአማራውን እንቅስቃሴ ካልመከቱት በስተቀር የድሮው ሥርዓት ተመልሶ አስፈሪ መልክ ይዞ እየመጣ ነው በማለት እየቀሰቀሱ ነው፡፡ እነስብሐት ነጋ ጸረ ነፍጠኛ ሲሉ ጸረ አማራ ማለታቸው መሆኑን ማንም ይስተዋል ብለን አናምንም፡፡ ስለሆነም እነዚህ ነብሰ ገዳዮች ጸረ አማራ ግንባር ለመፍጠር ላይ ታች እያሉ ነው!!!
እንደሚታወሰው ወያኔ በምርጫ 97 አስደንጋጭ ሽንፈት በገጠመው ማግስት፣ ትምክህተኛው አንሰራርቶ ተነስቷል፤ ይህ ኃይል ሥልጣን ከያዘ አገራችን ወደትርምስ ትገባለች፤ በሕዝቦች መካከል የለየለት መተራረድ ይከሰታል ወዘተ. በማለት ከአማራ ውጪ ያሉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በተለይ ደግሞ ወያኔና የኦሮሞ ድርጅቶች ጸረ ነፍጠኛ ግንባር ሊፈጥሩ እንደሚገባ ለነዶ/ር መረራ ጉዲና ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ መረራ በመጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት በቅርቡ የሞተው ፕሮፌሰር ዓለም ሀብቱ (የታላቋ ትግራይ ፕሮጀክት አራማጅ) እና ዘላለሙን የአማራ ሕዝብ ጠላት ሆኖ የኖረው አብዱል መሐመድ (ወርጂ) ወያኔንና እነዶ/ር መረራን ለማግባባት ሞክረው ነበር፡፡ እነመለስ በተለመደ ከሃዲነታቸው ‹‹ጸረ ነፍጠኛ ግንባር ፈጥረን፣ የተደቀነብንን ፈተና ካስወገድን በኋላ፣ እኛ ለአምስት ዓመታት ብቻ መርተን ለእናንተ እንለቅላችኋለን›› ወዘተ. የሚል ከንቱ ሙከራ ማድረጋቸውንና እነዶ/ር መረራ ይህንን የነመለስ መሰሪ አካሔድ ተረድተው ጥሪውን ውድቅ ማድረጋቸውን ሰምተናል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡
ዋናው ነገር፣ የወያኔ መሪዎች በሥልጣን ላይ ለመቆየት የማያደርጉት ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ጸረ ሕዝቦች፣ ወያኔን በሥልጣን ላይ እስካቆየ ድረስ እንኳን ከኢትዮጵያውያን ከባዕዳን ጋርም መተባበራቸው አይቀርም፡፡ ባለፉት 25 የግፍ ዓመታት በግልጽ እንደታየው፣ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ ሕዝብ ይጨፈጭፋሉ፤ በገፍ እያሰሩ ዘግናኝ ቶርቸር ይፈጽማሉ፤ እጅግ ርካሽ በሆነ መልኩ ሴት ፖለቲከኞች እንዳይኖሩ፣ ተስፋ የሚጣልባቸውን ሴት ፖለቲከኞችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች አስረው ይጫወቱባቸዋል፤ ወንዶች ብልታቸውን እየተቀጠቀጡ ከሰው ተራ እንዲወጡ ይደረጋል፤ እሳት እየጫሩ አንዱን ሕዝብ ከሌላው ጋር ያጋጩና ገላጋይና ዳኛ መስለው ይገባሉ፤ አሁን በቅርቡ በአማራ  መተማ  ውስጥ በግልጽ እንደታየው ጽረ ሕዝብ በሆነው የደኅንነት ተቋማቸው አቀነባባሪነት ትግሬዎችን እስከነጓዛቸው ጭነው አስወጥተውና የቀሩ አማሮችን አርደው ሲያበቁ፣ ትግሬ ተባረረ፣ በትግሬ ላይ ያነጣጠረ የዘር ጥቃት ተፈጸመ ብለው የትግራይ ሕዝብና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከጎናቸው እንዲሰለፍ ለማድረግ የፋሽስት ተግባር ይፈጽማሉ፤ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው የገበያ አዳራሾችና በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ ቦንብ ጥለው በሌሎች ላይ ያሳብባሉ፤ ግለሰቦችን በገቡበት ሁሉ እየገቡ እየተከታተሉ ያሸማቅቃሉ፤ ያስፈራራሉ፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከፍለው የሎቢ ቡድን ቀጥረው የዲፕሎማሲ ሥራ ይሠራሉ፤ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ባልደረቦች ገንዘብ ይከፍላሉ ወዘተ. ወዘተ.፡፡ እኩይ ተግባራቸው ማለቂያ የለውም፡፡ ተግባራቸው ሁሉ አገር ከሚመራ ድርጅት ሳይሆን ከማፊያዎች የሚጠበቅ የተራ ዱርዬና የማጅራት መቺ ተግባር ነው!! እንብላ ብቻ ሳይሆን ስንበላ አትዩን፣ ከዚያም አልፈው ሌላው አይብላ የሚሉ፣ ያዩትን ሁሉ በብቸኝነት ለማግበስበስ የሚጣደፉ ስግብግቦችና ጸረ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ደግነቱ ሁሉን እንብላ፣ ያየነው ሁሉ አይቅረን ሲሉ የያዙትንም የሚተፉበት ጊዜ መጥቶባቸዋል!!!
እንግዲህ፣ የአማራ ሕዝብ እየተደገሰለት ያለውን የወያኔ መሪዎች የጥፋት ድግስ ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ እየተሞከረ ያለው ጸረ አማራ ግንባር ምን ውጤት እንደሚያስከትል እና ሕዝባችን ከሚደገስለት የሞት ወጥመድ ራሱን ለማዳን ምን ማድረግ እንደሚገባው መወያየት ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ እኚህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ የቆዩ ምሁርና ፖለቲከኛ እንደነገሩኝ ከሆነ፣ ሁሉም ድርጅቶች ለዚህ የወያኔ የጸረ አማራ ግንባር ጥሪ ያላቸው ምላሽ አሉታዊ ነው፡፡ ዛሬ ማንም የፖለቲካ ሀ ሁ የሚያውቅ ሰውና የድርጅት መሪ ወያኔ እንዳበቃለት ይገነዘባልና የዚህ የወያኔ የጥፋት ግንባር ተባባሪ የሚሆን አካል ይገኛል ማለት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም ይህ በአማራ ሕዝብ ላይ የተደገሰ የጥፋት ግንባር ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል የመነመነ ነው፡፡ ሆኖም ዕድሉ የመነመነ ቢሆንም ዜሮ ነው ማለት ግን አይቻልም፡፡ ሁልጊዜም ግንባር ቀደም ጠላታችን የሆነው ወያኔ የሚደግስልንን የሞት ወጥመድ ነቅተን መከታተልና ማክሸፍ ይኖርብናል፡፡ የወያኔና የእኛ ግንኙነት የአጥፊና ጠፊ ግንኙነት ነውና ወያኔ እንዲጠፋ ያለእረፍት መሥራት፣ ያለእረፍት መታገልም ግዴታችን ነው፡፡ ወያኔ እስካለ ድረስ እኛ ሰላም አናገኝም፡፡ ለእኛ፣ ሰላም ማለት ከወያኔ ነጻ መሆን ማለት ነው!!!!
ወዳጄ የነገሩኝን ነጥብ ጠቅሼ ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ ምሁሩና ፖለቲከኛው አዛውንት፣ ‹‹በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ነፍጠኛም ትምክህተኛም ጠባብም ራሱ ወያኔ ነው፡፡ ስለሆነም የወያኔ መሪዎች የሚሉት ጸረ ነፍጠኛም በለው ጸረ ትምክህተኛ ወይም ጸረ ጠባብ ግንባር ጸረ ወያኔ ግንባር በመሆኑ፣ የዚህ ዓይነት ግንባር ከተመሠረተ ከመሥራች አባላት ውስጥ ወያኔ መኖር የለበትም፡፡ ግንባሩ ጸረ ወያኔ ነውና፡፡ ይህን ሐቅ ከያዝን በኋላ፣ ጸረ ነፍጠኛም በለው ጸረ ትምክህተኛ ወይም ጸረ ጠባብ ግንባር መመሥረት አለበት በሚለው ነጥብ ላይ መስማማት ይቻላል፤ እየተመሠረተም ነው›› በማለት አስደምመውኛል፡፡ የነስብሐት ነጋ ቀን መጨለሙን አያመለክትም ትላላችሁ? ለእኔ እንደዚያ ነው የሚታየኝ!

No comments:

Post a Comment