Wednesday, April 19, 2017

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በግብፅ ጉብኝት source zhabesha

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በግብፅ ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር የተላከው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን የሚያደርጉት ከግብፅ አቻቸው ሳሜህ ሹክሪ በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት እንደሆነ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች አንስቶ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት አወዛጋቢ ጉዳዮች እየገጠሙት ሲሆን፣ ሱዳንን ጨምሮ በግድቡ ላይ የሚካሄደው የሦስትዮሽ ምክክር አሁንም ድረስ አልተጠናቀቀም፡፡ ሚኒስትሩ ከግብፅ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንዲያደርጉ መታወቁን የማነ ናግሽ ዘግቧል፡፡

Standard (Image)

በሦስት ክልሎች በተፈጠሩ ‹‹ሁከቶች›› 669 ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋ አደረገ source mereja.com

ከሐምሌ 2008 ጀምሮ እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ‹‹ሁከቶች››፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞን ብሔርን መነሻ ባደረገ ግጭት የ669 ሲቪሎችና የፀጥታ አስከባሪዎች ሕይወት ማለፉን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋ አደረገ፡፡
ኮሚሽኑ በተጠቀሱት አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት አዘል ተቃውሞዎች በመመርመር ሪፖርቱን ማክሰኞ ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ከተጠቀሱት የሟቾች ቁጥር አብዛኛዎቹ ማለትም 495 ያህሉ ሕይወታቸው ያለፈው በኦሮሚያ በተነሳው ብጥብጥና ግጭት ነው፡፡
በኦሮሚያ በ15 ዞኖችና 91 ወረዳዎችና ከተሞች የተቀሰቀሰውን ግጭት አዘል ተቃውሞ በመመርመር ሪፖርት ያቀረቡት ኮሚሽነሩ፣ የግጭቱና የተቃውሞው መሠረታዊ መንስዔ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግርና የመብት ጥሰት፣ የሥራ አጥነት ችግር ሰፊ መሆን፣ የልማት ፕሮግራሞች መዘግየትና መታጠፍ፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ጥቅም በሕግ ተደንግጎ ተግባራዊ አለመደረግን ጠቅሰዋል፡፡ በአባባሽ ምክንያትነትም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) እና ሌሎች የሚዲያ አውታሮች የሕዝቡን ምሬት በመጠቀም፣ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ ከፍተኛ የአባባሽነት ሚና መጫወታቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ በኢሬቻ ባህላዊ በዓል ላይ የተከሰተውን አሳዛኝ የሰዎች ሕይወት ሕልፈት አጋጣሚን በመጠቀም፣ መንግሥት በተዋጊ ጄቶችና በሔሊኮፕተሮች ኦሮሞን እየጨረሰ እንደሆነ በመቀስቀስ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች አመፁ እንዲስፋፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
አመፁን በማስፋፋት ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመግባት ጥረት እንደነበረም ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከፍተኛ የትጥቅ ትግልና ውጊያ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
በምሥራቅ አርሲ፣ በባሌ፣ በምዕራብ ጉጂና በጉጂ ዞኖች በጦር መሣሪያ የተደገፈ ውጊያ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ በሶዶ፣ በአዳአ በርጋ፣ በሜታ ሮቢ፣ በደንቢ የሙሉ ቀን ውጊያ የነበረ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ ሕግን የተከተለ፣ ተመጣጣኝና ተገቢ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ምዕራብ አርሲ፣ ሻሸመኔና በአርሲ ነገሌ ተመሳሳይ ውጊያ የተካሄደባቸው በመሆናቸው የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በአዳሚ ቱሉ ማረሚያ ቤት 14 እስረኞች ሊያመልጡ ሲሞክሩ በጥበቃ ኃላፊዎች መገደላቸው ሕግን ያልተከተለ፣ አላስፈላጊና ተመጣጣኝ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ በባሌ ዞን ሮቤ ከተማና በራይቱ ወረዳ የተካሄደው ሠልፍ በጦር መሣሪያ ያልተደገፈ በመሆኑ፣ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተመጣጣኝ አልነበረም ብለዋል፡፡
በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በአወዳይ ከተማ በተወሰደው ዕርምጃ 28 ሰዎች መሞታቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹ዕርምጃው ሕግን ያልተከተለና ተመጣጣኝ ያልሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንዲሁም በምሥራቅ ወለጋ በነቀምቴ 12 ሰዎች ሕግን ባልተከተለና ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ መገደላቸውም ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ከሐምሌ 2008 እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ‹‹ሁከት›› የ462 ሲቪሎች ሲገደሉ 33 የፀጥታ አስከባሪዎችም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙንም ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ሁከትና ብጥብጥ እንደሚነሳ እየታወቀ ዕርምጃ ባልወሰዱ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ሲሉ ኮሚሽነሩ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
በአዳሚ ቱሉ ማረሚያ ቤት 14 ታራሚዎችን የገደሉ የጥበቃ ሠራተኞች በወንጀል ክስ እንዲመሠረትባቸው ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ኦነግና ተባባሪዎቹ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራርና አባላት ሊጠየቁ እንደሚገባ በተመሳሳይ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
በጌዴኦ ዞን አራት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በተቀሰቀሰ ብሔር ተኮር ግጭት 34 ሰዎች መግደላቸውን ገልጸዋል፡፡ የዚሁ ግጭት መንስዔ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ከእኩል ተጠቃሚነት ጋር የተገናኘ መሆኑን፣ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በዲላ ጊምቦ የገበያ ቦታ ለሳሪንደን አክሲዮን ማኅበር እንዲሰጥ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ብይን የዞኑ አስተዳደር ለመቀበል አለመፈለጉና ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ከጌዴኦ ውጪ ያሉ ብሔሮች ዞኑን ለቀው እንዲወጡ ሲካሄድ የነበረ ቅስቀሳ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሞቱት በተጨማሪ 178 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን፣ ከጌዴኦ ወጪ ያሉ 8,450 የተለያዩ ብሔሮች አባላት መፈናቀላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ግጭትና ሕይወት መጥፋት፣ እንዲሁም አካል መጉደል በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ የጌዴኦ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የዞኑ የአመራር አካላትና ፖሊሶች በነበራቸው የመቀስቀስና የማደራጀት ሚና በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች በነበረው ተቃውሞና ግጭት 110 ሲቪሎች ሲገደሉ፣ 30 የፀጥታ ኃይሎች ተመሳሳይ ዕጣ እንደገጠማቸው በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡ የአካል ጉዳትን በተመለከተም 276 ሲቪሎችና 100 የፀጥታ አስከባሪዎች መጎዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአማራ የተከሰተው ግጭትና ተቃውሞ መንስዔም በተመሳሳይ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ፍትሕ ማጣት፣ የቦታ አሰጣጥ ችግር፣ ኢፍትሐዊ ግብር አጣጣልና የኑሮ ውድነት መሆኑን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡
አባባሽ ሁኔታዎች በሚል ያቀረቧቸው ደግሞ የወልቃይት ጉዳይ በጊዜ መልስ ሊያገኝ አለመቻሉ፣ የአማራ መሬት ለሱዳን ተሰጥቷል የሚል ቅስቀሳ መኖሩ፣ በሲቪክ የትምህርት መጽሐፍ ላይ ያልታረመው የክልሎች ካርታ ተጠቅሰዋል፡፡
ተመጣጣኝ ያልሆኑ ግድያዎች በአማራ ክልል መፈጸመቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ በጎንደር አዘዞ፣ በደንቢያ፣ በወንበራ፣ በደባርቅ፣ በደብረ ታቦር፣ በስማዳ፣ በእንጅባራ እንዲሁም በዳንግላ ተመጣጣኝ ያልሆኑ ግድያዎች ተፈጽመዋል ብለዋል፡፡
በጎንደር ማራኪ በሚባለው ቦታ የፌዴራል ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በወሰደው ዕርምጃ 12 የፀጥታ ኃላፊዎችና አራት ሲቪሎች መገደላቸውን፣ በማረሚያ ቤት የተወሰደው ዕርምጃም ሕግን የተከተለ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በአማራ ክልል ብሔር ተኮር ጥቃት በመካሄዱ 11,678 የትግራይ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ በሰጡት ምክረ ሐሳብም በተፈጠረው ረብሻና ብጥብጥ ለተከሰተው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም አጥፊዎች ተለይተው ለሕግ እንዲቀርቡ ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ምክር ቤቱ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ፓርላማው ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች መነሻ ምክንያትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በገለልተኛ አጣሪ እንዲመረመር ለኢትዮጵያ መንግሥት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ማክሰኞ ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ምርመራውን በራሷ ተቋም የማካሄድ አቅም አላት፤›› በማለት የተመድን ጥያቄ እንዳልተቀበሉት ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በገለልተኝነት እንደሚሠራ ለቢቢሲ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተቋሙ የአቅም ውስንነት አለበት ብለዋል፡፡ 
Standard (Image)

Tuesday, April 11, 2017

በእነጉርሜሳ አያኖ መዝገብ የድምፅ ከምስል ማስረጃዎች በድጋሚ ሊታዩ ነው | “የኛ ጉዳይ ዝም ብለው ታስረው ይቆዩልን አይነት ነገር ነው” በቀለ ገርባ

“ፍ/ቤቱ ሌሎች አማራጮችን ይጠቀም።” ኢብኮ
“አስተርጓሚዎች ቀርበው ማስረጃው በችሎት እየታየ እንዲተረጎም ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጥ።” አቃቤ ህግ
“የኛ ጉዳይ ዝም ብለው ታስረው ይቆዩልን አይነት ነገር ነው።” በቀለ ገርባ

የእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ለሚያዚያ 2, 2009 ተቀጥሮ የነበረው አቃቤ ህግ በማስረጃነት ያቀረባቸው በኦሮምኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተሰሙ የድምፅ ከምስል ማስረጃዎችን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በፍርድ ቤቱ የስራ ቋንቋ ተርጉሞ እንዲያቀርብ ነው። ሆኖም እንዲተረጎሙ የተላኩትን 3ት ሲዲዎች ለመተርጎም ሰፊ ጊዜ የሚወስዱ በመሆናቸው እና ባለሙያዎች የስራ መደራረብ ስላለባቸው ፍ/ቤቱ ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ የሚገልፅ በ29/7/2009 ከኢብኮ የተፃፈ ደብዳቤ መቅረቡን ዳኞች ተናግረዋል። በተጨማሪም ለትርጉም ስራ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ከኢብኮ የተላከው ደብዳቤ ይጠቁማል።
አቃቤ ህግ በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተያየት ሲጠየቅ፤ የእንግሊዘኛ እና የኦሮምኛ አስተርጓሚ ተፈልጎ ማስረጃው በድጋሚ በችሎት እየታየ እንዲተረጎም ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የትርጉም ስራውን በተመለከተ ተደጋጋሚ ቀጠሮ እየተሰጠ መሆኑ ገልፀው፤ ከሳሽ አቃቤ ህግ ሃላፊነቱን እንዳልተወጣ እና ማስረጃዎቹን በፍ/ቤቱ የስራ ቋንቋ ተርጉሞ ማቅረብ እንዳልተፈለገ ተቆጥሮ ማስረጃው ውድቅ እንዲደረግ እና በቀረቡ ማስረጃዎች ብይን እንዲሰጥ ያመለከቱ ሲሆን ዘንድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የቻይንኛ ትርጉም እንኳን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሁለት የቪዲዮ ማስረጃዎች የቀረቡባቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር በቀለ ገርባ “እቤት ያሉ ሰዎች ንፁሃን ሰዎችን እስር ቤት ወርውረው እንደ ትልቅ ጀብድ ነው ሚያዩት። በሰው ስቃይ የመደሰት ነገር ነው የማየው። ከሳሼ ያቀረበውን ማስረጃ ትርጉሙን ሳያውቅ፤ ይዘቱ ምን እንደሆነ ሳያውቅ ነው እንዴ የከሰሰኝ? ትርጉሙን ሳያውቅ እንዴት ወንጀል ነው ብሎ ትርጉሙን በማያውቀው ማስረጃ ክስ ይመሰርታል? በእውነቱ በሃገራችን የፍርድ ሂደት አዘንን፤ እኛስ ትንሽ ነን በዚህ አይነት ስንት ሚሊዮኖች ናቸው መከራቸውን የሚያዩት? የኛ ጉዳይ ዝም ብለው ታስረው ይቆዩልን አይነት ነገር ነው። እቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቁጭ ብለው በኛ ስቃይ እና መከራ ይደሰታሉ። ማስረጃው እንደሚባለው ተተርጉሞ ቢቀርብ ለኔ ይጠቅመኝ ነበር። የኔን ንፅህና ነበር የሚያስረዳው። ጉዳዩ ከሚንጓተት ይቅርና በተሰሙት ማስረጃዎች ውሳኔ እንዲሳጥ ነው የምጠይቀው።” የሚል አስተያየታቸውን አቅርበዋል።
የኦፌኮ አመራር እና 2ኛ ተከሳሽ የሆነው ደጀኔ ጣፋም “የአቃቤ ህግን ማስረጃ ፍ/ቤት ያሰባስብ የሚል ህግ የለም። ፍ/ቤት እያደረገ ያለው ማረጃ የማሰባሰብ ነገር ነው። ማስረጃዎቹ በፍ/ቤት የስራ ቋንቋ ተተርጉመው መቅረብ የነበረባቸው ከክሱ ጋር ነው። የአቃቤ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ክስ በቅንንነት መቅረብ እንዳለበት ይጠቅሳል። ማስረጃዎች የሚጎሉ ከሆነ ክሱን አለማቅረብ ይቻል ነበር። ተተርጉሞ እንዲቀርብ ፍ/ቤት ካዘዘ ቆይቷል። አቃቤ ህግም በባለፈው ቀጠሮ ማስረጃዎቹን ኢብኮ እንዲተረጉም መላኩን ተናግሯል። በሃገሪቷ የተቋም አለመታዘዝ አለ። የአቃቤ ህጉንም እጅ የጠመዘዘ እጅ አለ ማለት ነው። ጉልበቱ እና አቅሙ ካላችሁ ያንን እጅ ሰብስቡልን።” ብሏል።
አቃቤህግ በማስረጃ አቀራረብ ሂደት ያሳየው ቸልተኝነት እንዳልነበረ ጠቅሶ ተደጋጋሚ ቀጠሮ መሰጠቱን በዚህም ተከሳሾች መንገላታታቸው የማይካድ መሆኑን ተናግሯል። ከክሱ ጋር የተያያዙ የሰነድ ማስረጃዎችን በተመለከተ በፍ/ቤቱ የስራ ቋንቋ ተተርጉመው ለተከሳሾች መድረሳቸውን ጠቅሶ የድምፅ ከምስል ማስረጃዎች ግን ከዚህ ቀደም በፍ/ቤቱ የተለመደው አሰራር በችሎት በሚታይበት ወቅት ከአስተርጓሚ ጋር የሚቀርብ እንደሚሆን ገልፇል። በዚህ መዝገብም የድምፅ ከምስል ማስረጃ በሚሰማበት ወቅት አስተርጓሚ እንዲቀርብ አድርጎ የነበረ መሆኑን አቃቤ ህግ አስታውሶ፤ በእለቱ ችሎቱ ማስረጃው ከተሰማ በኋላ ተተርጉሞ ቢቀርብ ይሻላል ብሎ በመወሰኑ እየተተረጎመ የመሰማት ሂደቱ እንደቀረ ተናግሯል። በመሆኑም ሌላ ቀጠሮ እንዲሰጥ እና ማስረጃው በችሎት እየታየ አስተርጓሚዎችም ቀርበው በችሎት እንዲተረጎም አቃቤ ህግ ጠይቋል።
ዳኞች የግራ እና የቀኙን ክርክር ከሰሙ በኋላ የነሱን አስተያየት እና ትእዛዝ ሰጥተዋል። አቃቤ ህግ ክስ ሲመሰርት የሰነድ ማስረጃዎችን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ማስረጃ በፍ/ቤቱ የስራ ቋንቋ አስተርጉሞ ማቅረብ እንደነበረበት፣ ፍ/ቤቱ እየሰራ ያለው መረጃ ማሰባሰብ ሳይሆን የፍትህ ስርአቱን የማገዝ ስራ እንደሆነ እንዲሁም ኢብኮም የፍትህ ስርአቱን የመተባበር ግዴታ እንዳለበት ገልፀዋል። በዚህም መሰረት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የሚመለከተው ሃላፊ ሁለት አስተርጓሚዎችን(አንድ የኦሮምኛ እና አንድ የእንግሊዘኛ ቋንቋ) ይዞ በመጪው ሃሙስ (ሚያዚያ 5, 2009) እንዲቀርብ ጥብቅ ትእዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል— ዳኞች። በተጨማሪም ተርጓሚዎቹ በቀጠሮው እለት ሲቀርቡ የትርጉም ስራውን በተቀላጠፈ እና በፍጥነት እንዲሰሩት የድምፅ ከምስል ማስረጃዎቹ ከቀጠሮው ቀደም ብሎ እንዲደርሳቸው ታዟል።

Source: የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት

በወላይታ የኃይለማርያም ደሳለኝ የትውልድ ቦታ ትልቅ የገበያ ማዕከል በእሳት ወደመ

(ዘ-ሐበሻ) መነሻው ባልታወቀ ሁኔታ አንድ ትልቅ የገበያ ማዕከል በደቡብ ክልል በወላይታ አረካ ከተማ ውስጥ መውደሙ ተሰማ:: ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው መንግስት የአንድን ወገን የሚጠቅም ኢኮኖሚና አስተዳደር በአካባቢው በማስፈኑ ሕዝቡ በንዴት ሳያነዳው እንዳልቀረ ነው::
የአካባቢው ነዋሪዎች ለዘ-ሐበሻ በላኩት መረጃ እንደገለጹት ዛሬ በአረካ የወደመው ትልቅ የገበያ ማዕከል በደህዴን ካድሬዎችና በሕወሓት ደጋፊዎች የተያዙ ናቸው::
የ እሳት መነሻው ከመንግስት በኩል የተሰጠ ምንም ዓይነት ምክንያት ባይኖርም ንግድ ድርጅቶቹ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ እንደወደሙ መረጃዎች ጠቁመዋል:: ኃይለማርያም ደሳለኝ በሕወሓት መንግስት ምርጫ ወቅት በዚሁ አረካ ከተማ 100% አሸንፈዋል መባሉ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ እርሳቸውን በሚቃወሙ ሰዎች ይህ የገበያ ማዕከል ወደመ መባሉ የፖለቲካውን ኪሳራ ያሳያል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ:: የአረካ ነዋሪዎች የበይ ተመልካች ሆንን በማለት ደህዴንን እና ኃይለማርያም ደሳለኝን እንደሚያማርሩ ጨምሮ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል::

Sunday, April 9, 2017

አርበኞች ግንቦት 7 በፈጸመው ጥቃት በጥበቃ ሥራ ላይ የነበረ ምክትል ጋንታ መገደሉ ተዘገበ

ትንሳኤ ራድዮ እንደዘገበው መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር እና በደቡብ ጎንደር መሀከል በምትገኘው ልዩ ቦታው ግም ውሃ ከተባለው ሥፍራ ላይ ከለሊት 6፡ ሰዓት ሲሆን በጥበቃ ላይ በነበሩ የወያኔ ወታደሮች ላይ የአርበኞች ግንቦት ታጋዬች ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀም በዕለቱ በጥበቃ ሥራ ላይ የነበረ ምክትል ጋንታ መሪን መግደላቸው ተገልጾአል።
File Photo
በዚህ ጥቃት ህይወቱ ሊያልፍ የቻለው ጋንታ መሪ ስም ሳጅን ደረጀ አማረ የሚባል ሲሆን ሟች በጥይት ከተመታ ቦኋላ ህይወቱን ለማትረፍ ወደ ጎን ሆስፒታል ተወስዶ የነበረና ነገር ግን በደረሰበት ከፍተኛ ምት ሂይወቱ ሆስፒታል እንደደረሰ ማ ተገልጾአል። የሳጂን ደረጀ አማረ አስከሬን ትናንት መጋቢት 29 ቀን ወደ ትውልድ ቦታው ፎገራ ወረዳ ወረታ ተወስዶ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ተፈጽሟል ተብሏል። አርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች በወሰደው በዚህ ጥቃት ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የደረሰበት አወቀ የተባለ የሚሊሺያ ኮማንደር ሁለት እግሮቹን ተመቶ ጎንደር ሆስፒታል ተኝቶ በመታከም ላይ እንደሚገኝ ታውቆአል።

Friday, April 7, 2017

አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከድርድሩ ራሱን ስላገለለው መድረክ ተናገሩ – “መድረክ ‘ኢህአዴግ ከኔ ጋር ለብቻው ነው መደራደር ያለበት’ ብሏል”

ከአውስትራሊያ የሚሰራጨው ኤስቢኤስ ራድዮ ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት የዲሞራክሲ ሥርዓት ግንባታ ዋና አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ሺፈራው ሽጉጤን በኢሕአዲግ እና 21 ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ ስላለው የቅድመ ብሔራዊ ድርድር አነጋግሯቸዋል:: አቶ ሽፈራው ከድርድሩ ራሱን ስላገለለው መድረክም ተናግረዋል – ያድምጡትና አስተያየትዎን ይስጡ

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጃዋር መሃመድ በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ተወሰነ | ዶ/ር መረራ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ዶ/ር መረራ ጉዲና ፍ/ቤት ቀርበው ነበር (መጋቢት 29/2009)
*ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ጃዋር መሃመድ፣ ኢሳት እና ኦኤምኤን በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ተወስኗል።
ባለፈው በነበረው ቀጠሮ በእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና መዝገብ ከሃገር ውጪ የሚገኙ ተከሳሾች ቀርበው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ የሚያደርግ ማስታወቂያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲወጣ እና የወጣውን ማስታወቂያ ለማየት ለዛሬ መጋቢት 29/2009 ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር።
ዛሬ መጋቢት 29/2009 በዋለው ችሎት መጋቢት 15/2009 የታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ገፅ 7 ላይ ከሃገር ውጪ የሚገኙት 2ኛ (ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ)፣ 3ኛ (አቶ ጃዋር መሃመድ) ፣ 4ኛ (ኢሳት) እና 5ኛ (ኦኤምኤን) ተከሳሾች ቀርበው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ የሚያደርግ ማስታወቂያ መታተሙን እና በመዝገቡም ላይ ኮፒው መያያዙን ዳኞች ያሳወቁ ሲሆን፤ የአቃቤ ህግን አስተያየት ጠይቀዋል። አቃቤ ህግም ተከሳሾቹ በጥሪው መሰረት ስላልቀረቡ ክሱ በሌሉበት እንዲታይ ጠይቋል። ዳኞችም፤ አቃቤ ህግ ሌላ ሃሳብ እስኪያመጣ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስረአት አንቀፅ 161 እና 163 መሰረት ተከሳሾቹ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ወስነዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና በዛሬው ችሎት ከማእከላዊ ቀርበው የነበረ ሲሆን ለሚያዚያ 16/2009 በሳቸው ላይ የቀረበውን ክስ መቃወሚያ ለመስማት የተያዘው ቀጠሮ እንደተጠበቀ መሆኑ ተገልፇል።

በተያያዘ ጉዳይ ዶ/ር መረራ የዋስትናውን ጉዳይ በተመለከተ ይግባኝ ብለው ዛሬ መጋቢት 26/2009 ከሰአት ጠቅላይ ፍ/ቤት ቀርበው ነበር። የይግባኙን ፍሬ ሃሳብ ወክለዋቸው የቀረቡት ጠበቆች አቶ ወንድሙ ኢብሳ፣ አቶ አለሙ ጎቤቦ እና አቶ ደሳለኝ ቀነኢ ለችሎት ያስረዱ ሲሆን፤ ዝርዝር ሃሳቡንም በፅሁፍ አስገብተዋል። የስር ፍ/ቤት በዶ/ር መረራ ላይ የቀረበው የመጀመሪያ ክስ ከእድሜ ልክ እስከ ሞት ያስቀጣል የተባለውን እንደሚቃወሙ የገለፁት ጠበቆቹ፤ በመጀመሪያው ክስ የተጠቀሰው አንቀፅ 238 (1) መነሻ ቅጣት 3ት አመት ከፍተኛው ደግሞ 25ት አመት መሆኑን ጠቅሰው የጥፋተኝነት ብይኑ እርግጠኛ ባልተኮነበት ሁኔታ ከፍተኛው መያዝ እንደሌለበት ተናግረዋል። በመጀመሪያው ክስ የተጠቀሰው ሌላው አንቀፅ 238(2) ን በተመለከተ ደግሞ ብቻውን መታየት እንደሌለበት ከአንቀፅ 238(1) ጋር አብሮ መያያዝ እንደሚኖርበት ገልፀዋል—ጠበቆች።
ዳኞቹም በጠበቆቹ በኩል የቀረበውን የይግባኝ ቅሬታ ከሰሙ በኋላ፤ ያስቀርባል አያስቀርብም የሚለውን ውሳኔ ከመጪው ሰኞ (ሚያዚያ 2/2009) በኋላ ጠበቆች ማረጋገጥ እንደሚችሉ እና የሚያስቀርብ ከሆነ ለክርክር በሚሰጠው ቀጠሮ ዶ/ር መረራ እንደሚቀርቡ ገልፀዋል።
ዶ/ር መረራ “ከክሴ ጋር የተያያዙት ማስረጃዎች ባለፉት 25 አመታት በፓርላማ ያረኳቸው ንግግሮች እና በተለያየ ጊዜ የፃፍኳቸው ሃሳቦች ናቸው። ጉዳዩ የፓለቲካ መሆኑን ያሳያል። ክሱ የፓለቲካ ነው። በዚህ በኩል እንድታዩት ነው።” የሚል አስተያየታቸውን ለዳኞች ተናግረዋል።
ዶ/ር መረራ ዋስትናውን በተመለከተ የይግባኙ ቅሬታ እና በአዲስ ዘመን የወጣው ማስታወቂያ ከዚህ ፅሁፍ ጋር ተያይዟል።
ዜናው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት ነው
Related Story
  1  120  121