Monday, November 20, 2017

የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር አቶ ነአምን ዘለቀ ከአዲሱ የወያኔ የጸጥታ ዕቅድ ጀርባ ያለውን ሴራ አጋለጡ (ሊታይ የሚገባው) source zehabesha

(ዘ-ሐበሻ) የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር የሆኑት አቶ ነአምን ዘለቀ ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች ሾልኮ በመውጣት ለሕዝብ ስለደረሰው ከአዲሱ የወያኔ የጸጥታ ዕቅድ ሰነድ ጀርባ ያለውን ሴራ አጋለጡ:: የድርጅታቸው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ነአምን ከአርበኞች ግንቦት 7 ራድዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ሰነዱን አስታከው ሕዝብ ማወቅ አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦች በስፋት አስቀምጠውታል:: ተመልክተው ለወዳጆችዎ ያካፍሉት ዘንድ ዘ-ሐበሻ ጥሪዋን ታቀርባለች::


ጎንደር በሚገኙት የወያኔ ባለስልጣናት ላይ ጥቃት ተሰነዘረ | አዘዞ ወታደራዊ ካምፕ እና ኤርፖርት መስመር ታምሷል! source zehabesha

ለጥቃቱ በህቡእ የቆየ ድርጅት ሃላፊነት ወስዷል!
ሙሉነህ ዮሐንስ
ቅዳሜ ህዳር 9 2010 እኩለ ሌሊት ሲሆን ጎንደር አዘዞ ውስጥ በተመሳሳይ ሰአት በሁለት ቦታ በወያኔ ላይ እርምጃ መውሰዱን በህቡ ስንቀሳቀስ ቆይቻለሁ ያለ ድርጅት በላከልን መልእክት አሳወቀ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርቲ(ኢብፓ)/Ethiopian National Party የላከውን መግለጫ ዝርዝሩን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የኢብፓ ወታደራዊ ክንፍ ሁለት ፍንዳታ ነው የፈፀምኩት ያለው። አንደኛው ጥቃት አዘዞ 24ተኛ ክፍለ ጦር ካምፕ ላይ ነው። በጥቃቱ በውስጡ ምን እንደያዘ ያልታወቀ መጋዘን ጋይቷል። በወታደሩ ላይ ከፍተኛ ትርምስ ፈጥሯል። ዋናው የጥቃቱ ኢላማ የሆነው ግን ሁለተኛው ጥቃት ነው። ድርጅቱ ቀድሞ ባገኘው ጥብቅ መረጃ መሰረት ጨለማን ተገን አድርገው በእኩለ ሌሊት አዘዞ ወደ ሚገኘው ኤርፖርት በሁለት ዘመናዊ ኮብራ መኪኖች ሲጓዙ አዘዞ በሚገኝ ድልድይ አካባቢ ሲደርሱ የእጅ ቦንብ ተወርውሮባቸዋል። ተከታትሎ ተኩስ ስለተከፈተባቸው በፍጥነት ወደ ኋላ ዞረው ወደ ጎንደር ከተማ እንዲመለሱ ተገደዋል። በመኪኖቹ ውስጥ የነበሩትን የህወሃት ባለስልጣናት ማንነትና የደረሰባቸውን ጉዳት ለጊዜው መለየት አልተቻለም።
24ተኛውና 42ተኛው ክፍለ ጦሮች የሰፈሩበት ካምፕ ላይ የተጣለው የመጀመሪያው ጥቃት አቅጣጫ ማሳቻ ነበር። የደፈጣ ጥቃት የተፈፀመበት ድልድይ ወደ መተማ መስመር መገንጠያ ላይ ነው። ሃላፊነት የወሰደው ኢብፓ ጠላትን ከፍ ባለ ደረጃ ለመፋለም ያለንን ወኔና ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብሏል።
በቂ ቅድመ ዝግጅት በመደረጉ ታጋዮቹ በቀላሉ ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል። ለደሞዝ ሲል ለወያኔ አገልጋዩ ወታደር ከፍተኛ የሆነ ድንጋጤ አድሮባቸዋል። ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ አሰሳ እየተደረገ ነው። የወያኔ አመራሮች ተሸብረዋል። በአጠቃላይ ጎንደር ላይ ከፍተኛ የሆነ ውጥረት ተፈጥሯል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርቲ የወያኔን እብሪት አንታገሰውም ቀጣይና ተከታታይ እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ ማስጠንቀቂያ ልኳል።
ድርጅቱ በተለያየ አደረጃጀት በስፋት በገጠርም በከተማም ሲታገሉ የቆዩ ሃይሎችን ወደ አንድ ወጥ አደረጃጀትና አመራር ማሰባሰቡን እንዲሁም መሰል ቀጣይ ተግባራት በመላ ሃገራችን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ድርጅቱም አመራሩም ሙሉ ለሙሉ በህቡእ ሃገር ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ስለ ገለፀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርቲ አላማና ማንነት የድርጅቱ ማኒፌስቶ ስለደረሰን በቀጣይ እንዘግባለን።

749 Shares
Share
Tweet
Pin
Email
Share

Wednesday, November 15, 2017

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በኦሮሚያ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ source zehabsha

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ትላንት በኦሮሚያ ውስጥ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ ውስጥ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በጥቃቱም ሰባት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ዛሬም በስፍራው ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የፖሊስ አባላት መሆናቸውን በዓይናቸው እንደተመለከቱ የገለጹት ነዋሪዎች፣ በቀጣይም ለደህንነታቸው እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል፡፡
File Photo
በጥቃቱ ከተገደሉ ሰዎች በተጨማሪ የቆሰሉ ሰዎች ስለሞኖራቸውም እየተነገረ ይገኛል፡፡ የክልሉ ልዩ ጦር ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ ከአካባቢው ብዙም ርቆ እንዳልሄደ የሚናገሩት የዓይን እማኞች፣ ሁለተኛ ዙር ጥቃት ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት በማኅበረሰቡ ዘንድ መፈጠሩንም ነዋሪዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ የልዩ ኃይሉ አባላት፣ ሰባት ሰዎችን ከገደሉ በኋላ አንድ ትምህርት ቤት በጥይት እንዳጋዩ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ በተጨማሪም ሁለት የመኖሪያ ቤቶች በልዩ ኃይሉ አባላት እንዲቃጠሉ መደረጉንም ነዋሪዎቹ ያክላሉ፡፡
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ከሆነ፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባለቱ ጥቃቱን የፈጸሙት በስፍራው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ባሉበት ሁኔታ ነው፡፡ ጥቃቱ ሲፈጸም የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን የዓይን እማኞቹ ይገልጻሉ፡፡ ከሟቾች መካከል አራቱ ዕደሜያቸው ገፋ ያለ ሲሆን፣ ከ60 እስከ ሰባ ዓመት ይገመታሉም ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል መካከል በተፈጠረው ግጭት፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በአሮሚያ ክልል ውስጥ በርካታ ሰዎችን መግደሉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ቆሟል ተብሎ በመንግስት እየተገለጸ ባለበት በዚህ ሰዓት፣ ልዩ ኃይሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል ዘልቆ ጥቃት የፈጸመበት ምክንያት አልታወቀም፡፡

Friday, November 10, 2017

ንግስት ይርጋ በክሷ ምክንያት በደል እየደረሰባት እንደሆነ ተገለፀ source zehabesha

(በጌታቸው ሺፈራው)
የ”ሽብር” ክስ የተመሰረተባት ንግስት ይርጋ በክሷ ምክንያት ማረሚያ ቤት ውስጥ በደል እየደረሰባት መሆኑን ጠበቃዋ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። ንግስት ይርጋ በቤተሰብ ጥየቃ ገደብ እየተደረገባት መሆኑን ለፍርድ ቤት አቤቱታ ባቀረበችው መሰረት ፍርድ ቤቱ ምንም ገደብ ሳይደረግባት እንድትጠየቅ ቢወስንም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ሳያከብር ቀርቷል።
ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ለምን እንዳላከበረ በችሎት እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ቢልክም ማረሚያ ቤቱ በሁለት ቀጠሮች ቀርቦ አላስረዳም። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ለ3ኛ ጊዜ በሰጠው ትዕዛዝ ዛሬ ህዳር 1/2010 ሁለት ኃላፊዎች ቀርበዋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የፍትህ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አስቻለው መኮንን የማረሚያ ቤቱን እና የታራሚውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ንግስት ተለይታ እንደምትጠየቅ፣ እንዲሁም ሁሉን እስረኛ በተመሳሳይ ሰዓት ማስተናገድ ስለማይቻል የንግስት ጥየቃ ሰዓት ከሌሎች እስረኞች የተለየ መሆኑን እና ባስመዘገበችው የቤተሰብ አባላት እየተጠየቀች መሆኑን አስረድተዋል።
ንግስት ይርጋ በበኩሏ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስትገባ የሚጠይቋትን አስመዝግቢ መባሏንና ከተመዘገቡት ውጭ ያሉና 720 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ሊጠይቋት የሚመጡ ዘመድና ወዳጆቿ አልተመዘገባችሁም እየተባሉ እንደሚመለሱ ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በአቤቱታ አቅርባ ገደብ እንዳይደረግባት ብይን ቢሰጥም ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝን አለማክበሩን አስታውሳለች። ማረሚያ ቤቱ ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደማያከብር በጠየቀችበት ወቅትም የሴቶች ጥበቃ እና ማረፊያ አስተዳደር ኃላፊ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አለም ጥላሁን “ይህን ትዕዛዝ የሰጠው ዳኛ ማን ነው? ማወቅ እፈልጋለሁ።” እንዳሏትና እኚህ ኃላፊ ችሎት ውስጥ እንደሚገኙ ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ችሎት ውስጥ የነበሩትን ኃለፊ ለምን ይህን እንዳሉ መልስ እንዲሰጡ ሳይጠይቃቸው ቀርቷል። ማረሚያ ቤቱ ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ በሰጠው መልስ ላይ የፈረሙት የሴቶች ጥበቃና ማረፊያ አስተዳደር ጥበቃና ደኅንነት ስራ ዘርፍ ኃላፊ ለተ እግዜር ገ/ መድኅን ናቸው። ሆኖም ትዕዛዙን ለፍርድ ቤት ያደረሱትና በቃል መልስ የሰጡት የለተ እግዜር ኃላፊ ናቸው የተባሉት ዋና ሱፐር አለም ናቸው።
ማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ከሰጡት መልስ በተቃራኒ ገደብ እየተደረገባት መሆኑን ንግስት ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። በሀገራችን ባህል የታመመ እና የታሰረ ሰው ማንም እንደሚጠይቀው ያስታወሰችው ንግስት ይርጋ ጠያቂዎቿ መታወቂያ እስከያዙ እና ጠያቂና እሷን የሚቆጣጠሩ ፖሊሶች እስካሉ ድረስ በማንኛውም ሰው መጠየቅ መብቷ እንደሆነ ገልፃለች።
“ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ነፃ ሆኖ የመገመት መብት አለው” ያሉት ጠበቃ ሄኖክ አክሉሉ በበኩላቸው፣ ማረሚያ ቤቱ ንግስት ይርጋን በክሷ ምክንያት በደል እየፈፀመባት እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤቱ ተወካይ ከገለፁት በተቃራኒ ሌሎች እስረኞች ከ3 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ሲጠየቁ ንግስት ይርጋ ከ6 እስከ 7 ሰዓት ባለው አንድ ሰዓት ብቻ እንደምትጠየቅ ገልፀውም ማረሚያ ቤቱ የሚያደርሰውን አድሎ አስረድተዋል። ካስመዘገብሽው ውጭ አትጠየቂም የሚለው የማረሚያ ቤቱ አሰራርም ህገ መንግስታዊ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
የንግስት ይርጋ ሌላኛው ጠበቃ አቶ አለልኝ ምህረቱ ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት መልስ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ መልስ ለመስጠት የመጡት የእስረኞችን የዕለት ተዕለት ጉዳይ የማይከታተሉ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኃላፊ መሆናቸው ጉዳዩን በደንብ እንደማያውቁት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ባስመዘገበቻቸው ዘመድና ጓደኛ እየተጠየቀች ነው ያለ ሲሆን አቶ አለልኝ በበኩላቸው ህገ መንግስቱ የቅርብ ዘመድ እና ጓደኛ ሲል ወሰን እንደሌለው፣ ከዚህ መለስ ተብሎ ሊገደብ እንደማይገባ አብራርተዋል።
በንግስት አቤቱታ ጉዳይ ቀጠሮ የተሰጠው ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበረ ቀርቦ እንዲያስረዳ ለማዳመጥ የነበር ቢሆንም ዛሬም የሁለቱን ክርክር አዳምጦ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ንግስት ይርጋ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 21 መሰረት ገደብ ሳይደረግባት እንድትጠየቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ንግስት ይርጋ የማይገባ ጭቅጭቅ ማድረጓን ባይገልፁም ፍርድ ቤቱ ” ተከሳሽም የማይገባ ጭቅጭቅ ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ ያድርጉ፣ ህጉን ለይተው አውቀው ይጠቀሙ” ብሏዋል። ከችሎት ውጭ ያነጋገርኳቸው የንግስት ጠበቆች ንግስት መሰል ባህሪ አሳይታለች ባልተባለበት ፍርድ ቤቱ ያልተነሳ ነገር ላይ ለተከሳሽ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል። በሌላ በኩል ንግስት ይርጋ ጥርሷን ታማ መድሃኒት ቢታዘዝላትም መድሃኒቱ በታዘዘላት ሰዓት እየተሰጣት እንዳልሆነ አቤቱታ አቅርባለች።
የማረሚያ ቤቱን መልስ ከመስማት በተጨማሪ እነ ንግስት ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ተቀጥረው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ “መዝገቡ ተመርምሯል።ጊዜ አግኝተን ማጠቃለል አልቻልንም” ብሎ ለህዳር 5/2010ዓ•ም ለብይን ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Saturday, November 4, 2017

በኢትዮጵያ የጥቅምት ወር የዋጋ ግሽበት አስደንጋጭ ጭማሪ አሳየ source zehabsha

ቢቢኤን) በኢትዮጵያ በጥቅምት ወር ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ተመዘገበ፡፡ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እየተገባደደ በሚገኘው የጥቅምት ወር የግብይት ስርዓት ላይ ጥናት ያደረገ ሲሆን፣ ጥናቱም በወሩ ከፍተኛ ግሽበት መመዝገቡን አመላክቷል፡፡ ባለፈው መስከረም ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 10 ነጥብ 8 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ እየተጠናቀቀ በሚገኘው በዚህኛው የጥቅምት ወር ደግሞ የ12 ነጥብ 2 በመቶ የዋጋ ግሽበት ተከስቷል፡፡ ሁኔታው አስደንጋጭ መሆኑን የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ የዋጋ ግሽበቱ በየወሩ እየተከሰተ መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ይገልጻሉ፡፡

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እንደገለጸው በዚህኛው ወር ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከታየባቸው ምርቶች መካከል፣ ፍራፍሬዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ሙዝና አቮካዶ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች ከፍተኛ የዋጋ ንረት ታይቶባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስኳር እና ቡና በዚህ ወር አስደንጋጭ የዋጋ ንረት አስመዝግበዋል፡፡ በተለይ ስኳር እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የተደረገበት ሲሆን፣ አንድ ኪሎ ስኳርም እስከ መቶ ብር ድረስ መሸጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንዲሁም ቡናም በተመሳሳይ ሁኔታ በጥቅምት ወር አሳሳቢ የዋጋ ንረት አስመዝግቧል፡፡
ከአትክልት ደግሞ ቲማቲም፣ ካሮት እና ድንች የሚፋጅ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአትክልት ተራ፣ በመርካቶ እና በሌሎች የአዲስ አበባ ትላልቅ የገበያ ስፍራዎች በአትክልት ዋጋ ላይ አስደንጋጭ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ከጥራጥሬ እህሎች ደግሞ በጤፍ፣ ስንዴ እና በቆሎ ላይ መጠነኛ ጭማሪ መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ለደሃው ብቻ ሳይሆን፣ አለው ለሚባለው የህብረተሰብ ክፍልም እጅግ ፈታኝ ደረጃ ላይ መድረሱ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ በፍጆታ ምርቶች ላይ በየወሩ እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀሳብ ላይ ጥሎታል- እንደ መረጃዎች ገለጻ!