Friday, December 22, 2017

የኦሮምያ ክልል በአ/ አ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም በሚመለከት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በኦህዴድ አባላት ተቃውሞ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተዛወረ።

የኦሮምያ ክልል በአ/ አ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም በሚመለከት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የህዝብ አስተያየት ለማሰባሰብ በዛሬው ዕለት የተጠራው ስብሰባ በዋንኛነት በኦህዴድ አባላት ተቃውሞ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተዛወረ።

ዛሬ ጠዋት የፓርላማው የህግና ፍትህ አስተዳደር እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቋሚ ኮምቴዎች የህዝብ አስተያየት ለማሰባሰብ የጠሩት ሲሆን አብዛኛዎቹ የኦህዴድ አባላት ህዝባችን ችግር ላይ ባለበትና ከስር ጀምሮ በቂ ውይይት ባልተደረገበት ሁኔታ ይህ ስብሰባ መጠራት የለበትም የሚል አቋም በመያዛቸው በሻይ ዕረፍት ስም ስብሰባው ከአንድ ሰዓት በላይ ተቋርጦ ለማግባባት ቢሞከርም ሳይሳካ ቀርቷል።
በስብሰባው ላይ የተገኙትና የመጀመሪያውን የተቃውሞ ደምጵ ያሰሙት የኦሮምያ ኮምኒኬሽን ጵ/ ቤት ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ባደረጉት ንግግር ከ600 ሺህ በላይ ህዝባችን በኦሮምያና ሶማሌ ግጭት በተፈናቀለበትና በየቦታው ግጭቶች በቀጠሉበት፣ ረቂቅ አዋጁም ህዝባችን ባልተወያየበት ሁኔታ ይህ ስብሰባ መጠራት እንደሌለበት በመጥቀስ ለሌላ ግዜ እንዲተላለፍ ጠይቀዋል። ይህን የአቶ አዲሱ ንግግር አብዛኛው የኦህዴድ የፓርላማ አባላት በጭብጨባ ድጋፍ ሰጥተዋል።
ከኢህአዴግ ስብሰባ አቋርጠው በድንገት የተገኙት አቶ አባዱላ ገመዳ ከአብዛኛው የኦህዴድ አባላት በተቃራኒ ስብሰባው እንዲቀጥል ሀሳብ ሰጥተዋል። ረቂቅ አዋጁ የቀረበው ለማዳበር እንጅ ለማጵደቅ አለመሆኑን፣ ሌሎች መድረኮች ወደፊት እንደሚኖሩና መወያየቱ ጥቅም እንጅ ጉዳት እንደሌለው ያደረጉት ገለጳ የአባላቱን የጉምጉምታ ተቃውሞ አስከትሎአል።
እንደአቶ አባዱላ ስብሰባ አቋርጠው የተገኙት አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት ስብሰባው ለሻይ ዕረፍት ተበትኖ ከአንድ ሰአት በላይ ቆይቷል። በዝህ ሰዓት የኦህዴድ የፓርላማ አባላት አቶ አባዱላ ባሉበት በኦሮምኛ ቋንቋ የማግባቢያ ስብሰባ የተደረገ ቢሆንም አባላቱን ሀሳባቸውን ማስቀየር አልተቻለም።
በአካሄድ ውዝግብ እስከጠዋቱ 5:30 ሰአት በመቀጠሉ ጊዜም ስለሌለ በሚል የቋሚ ኮምቴው ሰብሳቢ ወደሌላ ቀን እንዲዛወር ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ ስብሰባው ተበትኗል

የኢትዮጵያውያን ህይወት ዋጋ ምን ያህል ወርዷል? – ከአንተነህ መርዕድ source zhabesha

በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ሰው ህይወት ክቡር ነው። ከዚያም አልፎ ህይወት ያለውን ነገር ሁሉ በከንቱ አለማጥፋት በተፈጥሮ ህሊናችን ውስጥ ህግ ሆኖ ስለተቀመጠም ነው የሰው ብቻ ሳይሆን የሌላም ፍጥረት ህይወቱ አለአግባብ በጭካኔ ሲቀጠፍ የሚዘገንነን። የሰውን ህይወት ለማጥፋት መጀመርያ የራስን ህሊና ፍርድ መጣስና ማቆሸሽን ይጠይቃል። ዛሬ በኢትዮጵያ በየቀኑ በጭካኔ የሚቀጠፉ ለጋ ወጣቶች፣ ማምለጥ የማይችሉ ህፃናት፣ አዛውንት አባቶችና እናቶችን ለሚመመለከት፣ ብሎም ለሚያስብ ንፁህ ህሊና ላለው እረፍት የሚነሳ ነው።
በተለይ ባለፉት አምሳ ዓመታት በግፍ የጠፋው ኢትዮጵያውያን ህይወት እጅግ የሚዘገንን ነው። አዎ አባቶቻችን የውጭ ወራሪን ለመከላከልና በነፃነት ለመኖር ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል። አምባገነን የሆኑ የየአካባቢው መሳፍንት ግዛታቸውንና ሃብታቸውን ለማስፋት በሚያደርጉት ጦርነት የብዙ ኢትዮጵያውያን ህይወት ተቀጥፏል፣ ለእድገት ይውል የነበረ ጉልበትና ሃብት ባክኗል። በያዝነው አምሳ ዓመት ግን ሶማልያ ጋር በተደረገው ጦርነት ካለቁት ወገኖቻችን ውጭ በብዙ መቶ ሺህ ያለቁት ለጋ ዜጎች ምክንያት የምናደርገው የእርስ በርስ ፍጅት ውጤት ነው። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሰዎች ብቻ ሳይሆን የእንስሳትም ህይወት በህግ በሚከበርበት ዓለም እነሆ በዚች ደቂቃ ብዙ የኢትዮጵያውያን ህይወት በራሳችን ግፈኞች ይቀጠፋሉ። አባቶቻችን ያስጠበቁት ዳር ድንበር ፈርሶ የድንበር ጦርነቱ በሱማልያና በኦሮሞ፣ በአፋርና በአማራ፣ በትግራይና በአማራ በሚል “መከላከያ ሰራዊት” በመሃል የዕብድ ገለጋይ ሆኖ ህዝቡን እየጨረሰና እያጫረሰ ነው።
በ1966 አብዮት ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጭቆናን አስወግደው ዴሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባት አገር እንድትሆን ያደረጉት ምኞትና ትግል ለስልጣን በቋመጡ ቡድኖች ብሩህ ልጆቿ በግፍ ተጨፈጨፉ። ብርቅ ልጆቿን የገደሉና ያስገደሉ የደርግ ባለስልጣናት ሆኑ በተቃዋሚነት ተሰልፈው የነበሩ መካን ፖለቲከኞች በድርጊታቸው መፀፀት ቀርቶ ከደሙ ንፁህ ነኝ የሚል መጽሃፍ እያሳተሙ፣ ግድያውን በሌላ እያላከኩ የተቃዋሚነት ካባ ደርበው ህሊና አጥተው፣አሁንም በፖለቲካው መድረክ አለን ሲሉ ይዘገንናል። ከደርግ ውድቀት ማግስት ሌላ ተስፋ ይኖር ይሆን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ካለፉት የባሰው ዘረኛና ጨካኝ አገዛዝ ገጥሞት አሁንም አገሪቱ የልጆቿ ደም እንደ ጅረት እየፈሰሰ ነው። የኢትዮጵያውያን ህይወት ወደ ቁጥር ተቀይሮ ይህን ያህል ሰው ሞተ የሚል ዜና መስማት ከመልመዳችን የተነሳ ቁጭት መፍጠሩ ቀርቷል።
ዛሬ የንፁሃን ደም በከፍተኛ ሁኔታ በሚፈስበት ሰዓት ከወደ ዘ ሄግ (The Hague)ብዙ ለጋ ወጣቶችን የጨፈጨፈውና ያስጨፈፀፈው  መቶ አለቃ እሸቱ የእድሜልክ እስራት እንደተፈረደበት ሰምተናል። ወንጀሉ በተፈፀመ በአርባ ዓመቱ ቢያንስ በአንድ ሰው ላይ ፍትህ ተበይኗል። መቶ አለቃ እሸቱ ወንጅሉን አልፈፀምሁም ብሎ እንደጓደኞቹ ክዷል። ለበርካታ ዓመታት በብርቱ ጥንቃቄ ምርመራውን ሲያካሂዱ የነበሩት የሆላንድ ፖሊሶችና የህግ ባለሙያዎች የማያጠራጥር መረጃ በፊቱ አቅርበው፣ ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው በሚገባ መስክረውበትም በወንጀሉ አልተፀፀተም። እሱ ጠበቃ ቆሞለት እምነትና ክህደቱን እንኳ እንዲያቀርብ ሲፈቀድለት እሱ በግፍ የጨፈጨፋቸው ወጣቶች ግን በገመድ እየታነቁ አንድ ጉድጓድ ውስጥ ነው የተጣሉት። ቤተሰቦቻቸው እርም ለማውጣት እድል አላገኙም። ብዙዎቹ የተገደሉት በእኔ እድሜ ዙርያ ያሉ አንዳንዶችንም በሚገባ የማውቃቸው ለጋ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በጊዜው በቦታው ባለመገኘቴ ብተርፍም ደብረ ማርቆስ ወህኒ ቤት ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጓሮ የጅምላ መቃብራቸውን ለሁለት ዓመት ተኩል በየቀኑ አይቼዋለሁ። በጊዜው ወህኒ ቤት የነበሩ ጓደኞቼና የተገደሉትን እንዲቀብሩ የተደረጉት ነጋ መሃመድና ሁለት የሻንቅላ (ጉሙዝ) ብሄረሰብ አባላት ሰጠኝ ማንጓና ቡሃ ቀኜ የነገሩንን ላካፍላችሁ። እለቱ ነሃሴ 8 ቀን 1970 ዓ ም ነው። ቀን በደብረማርቆስ ወህኒ ቤት ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ አንድ ሰፊ ጉድጓድ ሲቆፈር ዋለ። ሁኔታውን በተጠራጠሩ እስረኞች ገፅታ ላይ የሃዘን ድባብ አጥልቷል። ከቀኑ አስር ሰዓት እስረኛው ሁሉ ወደ ክፍሉ እንዲገባ ተደረገ። ሁሉም ጀሮውን አቅንቶ ይጠባበቅ ጀመር። ከምሽቱ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን አንድ ፖሊስ የበር መክፈቻ ቁልፎችን ሌላው ደግሞ ሶስት ሜትር እርዝመት ያላቸው ጠንካራ ገመዶች ይዘው በመከታተል ወደ እስረኛ ክፍሎች አመሩ። የብረት ፍርግርግ ባለው መስኮት ፖሊሱ ተጠግቶ የእስረኛውን ስም ይጠራና ለካቦው(በክፍሉ ወስጣ ላለ የእስረኞች አለቃ) ገመድ አቀብሎ የኋሊት እንዲያስረው ያዝዛል። ስማቸው የሚጠራ ለጋ ወጣቶች ሲወጡ ስርዓቱን የሚያወግዝ፣ ቀሪ ጓዶቻቸውን የሚያጽናና መፈክርና መዝሙር ሲያሰሙ አንዳች ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። እንዲህ እያደረጉ ከየክፍሉ በጠቅላላው 75 ወጣቶችን ጉድጓዱ ጥግ ወስደው በገመድ በማነቅ ማጅራታቸውን እየመቱ ጣሏቸው። እሸቱ ዓለሙ ረጂም ጥቁር ካፖርት ለብሶ እያንዳንዱ ላይ እርምጃ መወሰዱን ቆሞ ያረጋግጥ ነበር። ብዙዎቹ ወደገደል ሲጨመሩ ሳይሞቱ ከነህይወታቸው ነበር።በተለይ ሲያምረኝ ደረሰ የተባለው እስረኛ ግዙፍም ስለነበር አልሞት ብሎ እየተናገረ ወደ ጉድጓዱ መወርወሩን ቀባሪዎቹ በምሬ ይገልፁ ነበር። በሁኔታው ዘግናኝነት የተረበሹት ቀባሪዎች ለበርካታ ቀናት እህል መብላት ሆነ ከሰው መነጋገር ከብዷቸው ሰነበቱ። ታደለ ያዴታና ትኩዬ ልጅዓለም የተባሉ እስረኞች በነጋታው “ፍርድ አልተሰጠንም እኮ” ብለው ሲያመለክቱ “ ኑ ፍርድ እንስጣችሁ” ብለው ወስደው ገደሉዋቸው። ከተፈታሁ በኋላ የእነዚያን ጓደኞቼንና ዘመዶቼን ደጋፊ የሌላቸው ወላጆች የማፅናናበት ቃል አልነበረኝም። ዐይን ውሃቸው የሃዘናቸውን ጥልቀት አድምቆ ያሳየኝ ነበርና።
በጊዜው አገሪቷ ውስጥ ከተካሄደው ጭፍጨፋ አንፃር የመቶ አለቃ  እሸቱን ድርሻ አቃልሎ የሚያይ ካለ ተሳስቷል። በጀርመን ለብዙ ሚሊዮን ሰዎች እልቂት ምክንያት የሆነው መሪው ሂትለር ቢሆንም እሱ ሞቶ ተባባሪዎቹ ዛሬ በየአሉበት እየተፈለጉ ዘጠና ዓመት ሞልቷቸው አንኳ ከፍርድ አላመለጡም። ለዛሬ የዘረኝነት ጭፍጨፋ ተዋናይ መሪው መለስ ዜናዊ ቢሞትም የንፁሃን ደም እጃቸው ላይ ያለው የመለስ ተከታዮችና የራዕዩ አስፈፃሚዎች እስከ እለተ ሞታቸው እየተሳደዱ ከፍርድ አያመልጡም።
እሸቱና ጓደኞቻቸው የገደሏቸው ወጣቶች ቢተርፉ ኖሮ ለወላጆቻቸው ሆነ ለአገራቸው ምን ያህል ይጠቅሙ እንደነበር ለመገመት ያንን የመከራ ጊዜ በተለያየ አጋጣሚ ተርፈው የተገኙ በርካታ አገር የጠቀሙ ኢትዮጵያውያንን በምሳሌነት ማቅረብ ቀላል ነው። መቶ አለቃ እሸቱና ጓደኞቹ ሊገድሏቸው ካወጧቸው ውስጥ የሶስት ጓደኖቼን ሁኔታ ባብራራ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ሁለቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። ባህርዳር ሆስፒታል አካባቢ በድሮ አጠራር ሽምብጥ ከሚባል ሰፈር ተከራይተው የሚማሩበት ቤት ሲፈተሽ የኢህአፓ ወረቀት ስለተገኘ በጥርጣሬ ተያዙ። ስለኢህአፓ የሚያውቁትነገር  አልነበራቸውም። ሌላው ባህርዳር ጥጥ ፋብሪካ ወዝ አደር ሲሆን ለሠራተኛው መብት ተቆርቋሪና ንቁ ተሳታፊ ስለሆነ ብቻ የታሰረ ነው። ደብረማርቆስና በየአውራጃው ዋና ከተሞች ግድያው የሚፈፀም ወቅትበንዱ ቀን ከባህርዳር ወህኒ ቤት በለሊቱ የሚገደሉት ወጣቶች ስም እየተጠራ የኋሊት እየታሰሩ መኪና ውስጥ ሲገቡ ሶስቱ ጓደኞቼም በአንድ መኪና ተጨመሩ። ሌሎችን እየጠሩ እያሰሩ ወደ ሌላ መኪና በሚያስገቡበት ጌዜ “እርስ በርሳችን እንፈታታና ለማምለጥ እንሞክር” የሚል ሃሳብ አንዱ ሲያቀርብ ሁሉም በጥሞና ሰምተው መተባበር አልተባበሩም። አብዛኞቹ በድንጋጤ ምክንያት ለመወሰን አልቻሉም። ጎን ለጎን የነበሩት ወዝ አደሩና ሌላው ጓደኛዬ ተፈታቱ። ፊት ለፊት ወንበር የነበረው ጓደኛዬ የሚተባበረው አጥቶ የኋሊት እንደታሰረ ተቀምጧል። አንድ ካድሬ ሽጉጡን አቀባብሎ መሃላቸው ሲቀመጥ ጋቤና ውስጥ ሾፌሩና ሌላው ገዳይ ክላሽ ይዘው ገቡ። እስረኞችን የያዙ መኪኖች ከወህኒ ቤቱ ወጥተው ወደ አባይ ማዶ አቀኑ። ድልድዩን ከተሻገሩ በኋላ መግደያው ቦታ ደርሰው የፊተኛው መኪና ሲቆም ሁሉም ቆሙ። እጁ የተፈታው ጓደኛዬ የታሰረ መስሎ ከቆየ በኋላ በቅፅበት ካድሬውን በቦክስ መትቶ ሽጉጡን ለመያዝ ተናነቀው። ካድሬው በደመነፍስ መተኮስ ሲጀምር ጓደኛዬ ተመትቶ ወደቀ። በዚህ መካከል ወዛደሩና ሌላው ጓደኛዬ ከመኪናው ወጥተው በየፊናቸው በጨለማ ወደ አባይ አፋፍ ሲሮጡ ጥይት በላያቸው ቢዘንብም በተዓምር ተረፉ። ተመትቶ የነበረው ጓደኛዬ ሲነቃ ከሌሎች መኪኖች ያሉ እስረኛ ጓደኞቹ እየተረሸኑ ነበር። ቀስ ብሎ ሳይታይ ከመኪናው በመውጣት አመለጠ።
ከዚያ ጭፍጨፋ የተረፉት ሁለቱ አገራቸው ውስጥ ትልቅ ሥራ እየሠሩ ናቸው። ሶስተኛው አሜሪካ ይኖራል። ሶስቱም ተርፈው የወላጆቻቸውን እንባ አብሰዋል፣ ጡረዋል፤ ወንድምና እህቶቻቸውን አስተምረዋል፣ ዘመዶቻቸውን ረድተዋል። ለብዙዎች አርአያ በመሆን አገራቸውን ጠቅመዋል። ይታያችሁ! ያ ሁሉ ወጣት ባይጨፈጨፍ፤ ህዝባችንና አገራችን አሁን ባሉበት አይገኙም ነበር። መቶ አለቃ እሸቱ ሆነ መላኩ ተፈራን የመሰሉ ጨካኝ ግለሰቦች አገሪቷን በብዙ ጎድተዋታል። ኢትዮጵያ በእኛ እድሜ ያጣቻቸውን ወጣቶቿን አንድ ጊዜ በዐይነ ህሊናችን እናስብ!
  • በደርግና በድርጅቶች የእርስ በርስ መጫረስ መቶ ሺዎች ሞተዋል፤
  • በኤርትራ ጦርነት ብዙ መቶ ሺዎች በረሃ ላይ ቀርተዋል፤
  • በትግራይ ተራራና ሸንተረር ሮጠው ያልጠገቡ ወጣቶችና ጎልማሶች ለብኩን ዓላማ ተጨፋጭፈዋል፤
  • በባድሜ ጦርነት ከሁለቱም ወገን መቶ ሺዎች አልቀዋል፤
  • ወያኔ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ዘረኛ ፍላጎቱን ለማሟላትና ለመዝረፍ ሺዎችን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በጠራራ ፀሃይ ሲገድል፣ ሲያጋድል እናቶቻችን ከል ከመልበስ አልወጡም። ከዚያም አልፎ በልጆቻቸው ሬሳ ላይ እንዲቀመጡ የሚያደርግ ከናዚዎች ያልተናነሰ ዘረኛ ቡድን ነግሶባቸዋል።
  • በኢትዮጵያ ታሪክ ሆኖ የማያውቀው ዜጎች ከኖሩበት ቀዬ በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል። ይህንንም ወያኔ በዋናነት የሚያከናውነው ተግባር ሆኗል።
  • ወታደሩ የአገሩን ድንበር ለሱዳን አስረክቦ መሃል አገር ወንድሞቹን ለመግደል በጥዋቱ በየዜጎቹ በር ዘብ የቆመበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ባለፉት አምሳ ዓመታት አገር የሚገነቡ ሚሊዮን ልጆቿን በጨካኞች ግድያ ያጣች፤ ሺህ ሆስፒታል፣ ሺህ ዩኒቨርስቲ፣ ሺህ ግድብ፣ መቶ ሺህ ኪሎሜትሮች የመኪና መንገድና የባቡር ሃዲድ መገንባት የሚያስችል ሃብቷን ልጆቿ ለሚገደሉበት ጦር መሳርያ መግዣ አውላለች። ዘራፊ አምባገነን ገዥዎቿ የምዕራቡን ባንክ በገንዘቧ እስኪያጨናንቁ ተዘርፋለች። ቀሪ ዜጎቿም የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ሞትን እንኳ በሰላም መጠባበቅ ተነፍገው ሲፈናቀሉ፣ ሲሰደዱ፣ ሲታሰሩ፣ ሲገረፉ፤ ሞትን እየተመኙና የምፅዐትን ቀን እየጠበቁ ይኖራሉ።
መቶ አለቃ እሸቱ ወንጀሉን በፈጸመ በአርባ ዓመቱ ፍርዱን አግኝቷል። በሱ ጊዜ ትውልድ ላይ የፈረዱ ሁሉ ይዘገያል እንጂ ፍርዳቸውን ያገኛሉ። ጨካኝነትን በከፋ መልኩ እየተገበሩ ያሉ የአሁኖቹ ወያኔዎችና ተባባሪዎቻቸው በምንም ዓይነት ከፍርድ አያመልጡም። የዘመኑ ቴክኖሎጅ ምስጋና ይግባውና እያንዳንዷ ድርጊታቸው ተመዝግባ ተይዛለች። መሰላቸው እንጂ ዘርፈውና ገድለው የሚደበቁበት የዓለም ክፍል አይኖርም። እነሱ ያሰደዱት ኢትዮጵያዊ በሄዱበት ሁሉ አሳድዶ ለፍርድ ያቀርባቸዋል።
የትግራይ ህዝብና ልሂቃን ደጋግማችሁ ማሰብ ያለባችሁ ጉዳይ ቢኖር ህወሃት በትግራይ ህዝብ ስም ወንጀል የሚፈፅም መሆኑን ነው። እንዲሁም ተጠያቂዎቹ በድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑት ዘራፊና ጨፍጫፊዎች ከፍርድ የማያመልጡ ቢሆንም የትግራይን ህዝብ እንደከለላ በመጠቀማቸው ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እየነጠሉት መሆኑንም ነው። ስለዚህ ይህን ዕውነት አሁን በግልፅ ማየት ከተሳናችሁና ሆነ ብላችሁም የህወሃትን ወንጀል መቃወም ካልቻላችሁ አደጋው ሰፊ ነው። የትግራይ ህዝብ ህወሃት ከመኖሩ በፊት ኢትይጵያዊ ነው። ወያኔ ከወደቀ በኋላም ኢትዮጵያዊ ሆኖ ይቀጥላል። ከሚወድቅ ስርዓት ጋር ማበር ግን ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል። በወያኔ የምትጠፋው ኢትዮጵያ የናንተም መሆኗን አትዘንጉ። ጉዳቷም እንደሚጎዳችሁ እወቁ።
ኢትዮጵያዊ ሆነህ ሃቅም ያለህ ዜጋ መገደል፣ መታሰር፣ መገረፍ፣ መዘረፍ፣ መዋረድ እንዲበቃ ከፈለግህ እርስ በርስ መጎነታተሉን፣ ወያኔ በሰፋልህ የዘር ቀረጢት ለመግባት መሽቀዳደሙንና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳሕን ተውና የሃገርም የአንተም ጠላት የሆነ አምባገነን ስርዓትን ለመጣል ከወንድሞችህ ጋር ሆነህ ታገል። ለዚች አገር ውድቀትና በዚህ ደረጃ መገኘት አምባገነን ገዥዎቿ ብቻ ሳይሆኑ ለእነሱ አሳልፈን የሰጠናትና እስካሁን እንዲፈነጩ የፈቀድን እኛም በመሆናችን ተጠያቂነት አለብን። ከሃጤያቱ ነፃ መሆን የምንችለው አምባገነን ስርዓትን ለመጣል የተግባር አስተዋፆ ስናደርግ ብቻ ነው። ጊዜህን በወሬና በምሬት ከምታሳልፍ በተግባር ተሳተፍ። ለልጅህ የምታስረክበው ሃገር ሆነ በጎ ታሪክ የለህም። ሃገርህንም ታሪክህንም በጥሩ መጠበቅ የምትችለው ራስህ ብቻ ነህ።
ከተፈጥሮ ሞት ውጭ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሞት በፍጥነት መቆም አለበት። በዝምታችን፣ በስንፍናችን፣ በክፍፍላችን፣ በትምክህታችን፣ በዘረኝነታችን ምክንያት የኢትዮጵያውያን ህይወት በየቀኑ እየተቀጠፈ ነው። ኢትዮጵያዊ ላይ ሲደርስ የሰው ህይወት ዋጋ ረክሷል። እኛ ስላረከስነው ዓለምም እንስሳ የሞተ ያህል አላየውም። “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም” እንደተባለው እኛ ባለቤቶቹ ለህይወታችን ክብር አልሰጠነውም። እኛ ስናከብረው ሌላውም ያከብረዋል። ሶማሌው ሲገደል ሶማሌ በመጮህ፣ አማራው ሲገደል አማራው በመሰለፍ፣ ኦሮሞው ሲገደል ኦሮሞው በማመፅ፣ ትግሬው ሲገደል ትግሬው ደም በመመለስ የሰውን ክቡር ህይወት ለፖለቲካ ፍጆታ አርክሰን ከማውረዳችን በላይ ወያኔን ዘረኛ ብለን ለመኮነን የሞራል ብቃት አሳጥቶናል። ለሰው ልጅ ክቡር ህይወት በተለይም ለኢትዮጵያዊ  ህይወት ክብር ሳንሰጥ፤ ራሳችንን የለውጥ አካል ማድረግ ጨርሶ ቀልድ ነው። ወንጀልም ነው። ከጨፍጫፊው ወያኔና ከነመቶ አለቃ እሸቱ የተሻለ ልዕልና ለመጎናፀፍ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ህይወት ሊቆጨንና ሊያነሳሳን ይገባል። በዚህን ጊዜ ነው የኢትዮጵያውያን ህይወት ክቡር የሚሆነውና ግድያ የሚቆመው።

Monday, December 18, 2017

የሶማሌ ክልል ር/መስተዳድር ለተፈናቃዮች ያደረጉት ጥሪ Deutsche Welle (DW) amharic news

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከወራት በፊት አንስቶ ግጭት ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል። በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው ወሰን በትክክል ባለመለታየቱ በተነሳው ግጭት በሁለቱም ክልሎች በመቶዎች የሚገመቱ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም መፈናቀላችው ይታወቃል።

«ይህ ሁሉ ሰው ሲፈናቀል የፌዴራል መንግሥት የት ነበር?»

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ከጥቂት ቀናት በፊት ጥሪ አቅርበዋል። ተፈናቃዮች ወደ ሶማሌ ክልል እንዲመለሱ የቀረበው ጥሪ በርግጥ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው አይደለም፣ እንዲመለሱ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አሉ የሉም ፣ እነዚህ ጥያቄዎች ብዙ እያነጋገሩ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ እኛም ውይይት አካሂደንበታል።
አርያም ተክሌ
ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አበራ የማነአብ – ከመኢሶን እስከ 17 የወያኔ እስር ቤት ስቃይ | አሁንስ? | ያልተነገሩ ታሪኮችን የያዘ ልዩ ቃለምልልስ – አያምልጥዎ source zhabesha


 
 e

  
l
hare

አበራ የማነአብ – ከመኢሶን እስከ 17 የወያኔ እስር ቤት ስቃይ | አሁንስ? | ያልተነገሩ ታሪኮችን የያዘ ልዩ ቃለምልልስ – አያምልጥዎ