Monday, September 26, 2016

በኦስሎ በአገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሰፊ ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ


በሁለት ተቋማ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ እና በጋራ የምክክር መድረክ አዘጋጅነት በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ሰፊ ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ። ውይይቱ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት የትግል ስልት ከመጨረሻው ግብ ለማድረስ የተያዘው የነጻነት ትግል ለውጤት እንዲበቃ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ትልቅ አጀንዳ በመያዝ ሁሉም ለኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲ መስፈን፣ ዲሞክራሲያዊና ሰባዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ህዝባዊ ተቋማትና የእያንዳንዳችን እንደግለሰብ ልናበረክት የሚገባን አስተዋጾ ላይ በሰፊው መክሯል። \
በተጋባዥ እንግዶችም እጅግ ጠቃሚ ነጥቦችንና ሃሳቦችን አቅርበዋል። የመጀመርያ ተናጋሪ የነበረው ዶ/ር ሙሉዓለም አ...ዳም አጠቃላይ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ እዚህ ደረጃ እንዴት እንደደረሰ፣ ያሁን ላይ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ እና ወደፊት ሊደረግ የሚገባውን የትግል አቅጣጫ በሰፊው አሳይተዋል፤ በመቀጠልም ወጣት ኤልሳቤጥ ግርማ በነጻነት ትግሉ የወጣቶች ተሳ ትፎ በሚል ርዕስ ሰፊ ገለጻ አድርጋለች፤ ወጣቷ በገለጻዋም የወጣቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በአጼ ኃይለስላሴና ደርግ ዘምን ፣ በወያኔ ዘመንና የወቅቱን አጠቃላይ የወጣቶች እንቅስቃሴ በማሳየት እንዲሁም ተግዳሮቶቹን በመጠቆም በተቀጣጠለው የለውጥ እንቅስቃሴ ወጣቱን ለበለጠ ትግል እንዴት ማነሳሳት እንደሚቻል በሰፊው አብራርታለች። ሦስተኛው ተጋባዥ ዶ/ር ተክሉ አባተ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ህዝባዊ ተቋማት በተጀመረው የነጻነት ትግል ላይ ሊያበረክቱት የሚገባቸውን ከፍተኛ ሚና በዝርዝር አስረድተዋል፤ በግለሰብ ከእያንዳንዳችንም የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በግልፅ አሳይተዋል።
በአጠቃላይ ህዝባዊ ውይይቱ እጅግ ጠቃሚ ወቅታዊ ጉዳዮችና የመፍትሄ ሃሳቦች የተነሱበት፣ ከፍተኛ የትግል መነቃቃትና አብሮነት የተንጸባረቀበት ነበረ። የተጀመረው ህዝባዊ እምቢተኝነት ከጫፍ ደርሶ አረመኔያዊ አገዛዝ ከህዝባችን ጫንቃ አውርደን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ሁለገብ እንቅስቃሴ አስፈላጊ እንደሆነ በመድረኩ ከቀረቡ የውይይት ርዕሶች፣ ነጥቦችና በተሳታፊዎች ከተሰጡ አስተያየቶችና የሃሳብ ልውውጦች በቂ ግንዛቤ ላይ ተደርሷል።
በመጨረሻም ኢትዮጵያውያ አገራችን ከገባችበት አስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ በማውጣት እውነተኛ ሰላም፣ ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩላችንን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ እና በውይይቱ የተሰጡትን የመፍትሄ ሃሳቦች፣ አቅጣጫዎችና የትግል ስልቶች በሚገባ ተረድቶ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንዳለብን አጽንኦት ተሰጦ የአቋም መግለጫ በማውጣት ስብሰባው ተጠናቋል።

See More

No comments:

Post a Comment