Friday, November 18, 2016

ወያኔ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሕልሙ ቅዥት ሆነ ናሆም ግርማ/ከኖርዌይ Nahome Girma



ወያኔ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሕልሙ ቅዥት ሆነ
የወያኔ ፍላጎት የሚሞላው በኢትዮጵያ መፈራረስ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያኖች እየገደለንም ቢሆን ዛሬ የመውደቂያው ዋዜማ ላይ እንገኛለን። ለእኛ ለዜጎች ደግሞ እየሞትንም እያዘንም ከፊታችን ያለውን ነፃነት እያየን አለን። የወያኔ መንግስት ዛሬ ከስልጣን ተሰናበተ የሚለው ዜና ቅርብ እንደሆነ ብዙ አመላካች ነገሮችን እያየን ነው። በሌላ በኩል ወያኔ በአምቦ፣ በወለጋ፣ በሻሸመኔ፣ በአላባ፣ በጎንደር፣ በደብረታቦር፣ በጋይንት፣ በባህርዳር፣ በፍኖተሰላም ወዘተ….. የተነሳበት የህዝብ ተቃውሞ ምላሹ በጥይት ግድያና ጭፍጨፋ መሆኑ እያየነውና እየተመለከትነው እንገኛለን። ወያኔ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለማኮላሸት የሚወስዳቸው የጭፍጨፋ ተግባራት የተለየ ሽፋን ለመስጠት ምን ምን ዘዴዎችን ይጠቀማል የሚሉትን ከተጨባጭ የወያኔ ተግባራት በመነሳት የሚከተሉትን ማየት ይጠቅማል።
ወያኔ በሚወስዳቸው ግድያና አፈና ጭፍጨፋዎች ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት የህዝብ ጥያቄና የህዝብ ግፊት ነው በማለት ሰሚ ያጡ የመገናኛ ብዙሃኖችንና በስም የግል የሆነ በተግባር ግን ወያኔ የሆኑ የግል ሚዲያዎችን ይጠቀማል። ሁሉም የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዝን ሌሎችም የግል ሚዲያዎችን የግል መሳይ ጋዜጦችን ወዘተ… ሁሉም የወያኔ የእምባ አባሾች ናቸው። ስለዚህ በማንኛውም ጊዜና ሰዓት የፈለገውን የፕሮፓጋንዳ ስራ ለመስራት ይጠቀምባቸዋል። እንዲሁም ለተለያዩ የስብሰባ አዳራሾች በሚጠሩ የወያኔ ስብሰባዎች ይህንኑ የሽፍን ተግባር ያንፀባርቃሉ።
ሌላው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በንቃት ሊከታተለው የሚገባ ጉዳይ አለ። በመከታተል ብቻ ሳይሆን ለመርጃ የተደገፈ ምዝገባዎችን እያደረገ የማስቀመጥ ስራን መፈፀም፣ በቴሌቪዝን በራዲዮ እየቀረቡ ለኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት የህዝብ ተቃውሞዎችን የሚወነጅሉ፣ የሚያንቋሽሹ ወዘተ… እንደዚህ አይነት ግለሰቦች በህግ የሚጠየቁበት ጊዜ ይመጣል። እያንዳንዱ ዜጋ ደግሞ እንደነዚህ ያሉ ከሃዲዎችን እየመዘገቡ መያዝ ትልቅ  ግዴታ የመወጣት አካል ስለሆነ በጥንቃቄ ሊሰራ ይገባል። በኋላ የቁርጥ ቀን ሲመጣ ተገድጄ ነው ካለማወቅ ነው… ወዘተ ያደረኩት የሚሉ ተልካሻ ምክንያቶች ከተጠያቂነት የሚያድን አለመሆኑ ማወቅ ይገባል።
እርጅና ጓዙን ጠቅልሎ የመጣባቸው የወያኔ መሪዎች የሚሰሩትን ካለማወቃቸው የተነሳ የማይወዳቸውንና የማይወዱትን ህዝብ የሞት እስራት የግድያ የቶርች ተግባራቸውን እየፈፀሙ በተጠናከረ መልኩ ቀጥለዋል። የህዝባችንን ደህንነት፣ አንድነት የማይፈልገውና የማይጠብቀው ወያኔ በአሁኑ ሰዓት የመከፋፈልን ቁማር ሲከተልና አማራጭ ከማጣትና  የሚሰራውን ስለማያውቅ ሙሉ ለሙሉ ባለማወቅ ሙሉ በሙሉ ወደዘር ጭፍጨፋ ፊቱን አዙሯል።
ሕዝብ ዛሬ ላይ የሚፈልገው ከወያኔ ስርአት መላቀቅ ብቻ ነው። በዜጎች በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በተለያዩ አመለካከት ምክንያት ፍትህ የማያዛባ መንግስት እንዲመሰረት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ነው። ሕዝቡን ሁሉ በእኩል ስልጣን የሚገዛ አድሎ የሌለበት የዳርድንበር የሚጠይቅ የሃገርፍቅር የሚያንገበግበው መሪ ይህ አይነቱን ሰው ማስቀመጥ የሁሉም ሰው ሀላፊነት ነው። ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ሰአት ካረጁት የወያኔ ባለስልጣናት ማናቸውን ስለመፈለግ አልፈው በሕግ ከለሳ ስር ሆነው ለ25 ዓመታት ውስጥ በፈፀሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲጠየቁ አቋም ነው። እነዚህ ያረጁ የወያኔ ባለስልጣናት በዘመናዊ አመለካከት ዝግ ሆነው ዘርና ጎሳን እየቆጠሩ ለሀገራችን ኢይትዮጵያ ላይ የአንድ ዘር የበላይነት ገኖ እንዲወጣ በፓለቲካውም በኢኮኖሚውም ለ25 ዓመታት ሲሰሩበት ከርመዋል። ዘር ላይ የተፃፈ ታሪክ ደግሞ ከልማት ይልቅ ጥፋት፣ ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ጎታችነቱ ያመዝናል።
ወያኔዎች ስልጣንን ሊገለገሉበት እንጂ ህዝቡን ሊያገለግሉበት እንደተቀበሉት ያልገባቸው ደንቆሮዎች ናቸው። በኢትዮጵያ ላይ ህዝብን ደስ የሚያሰኝ መሪ ሊመጣ የግድ ነው። በአዲሱ ትውልድ ለአዲሱ አስተሳሰብ የዳበረና የሰለጠነ ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ሁሉን ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የሚያደርግ ራእይ ያለው መሪ አስፈላጊ ነው።
ድል ለኢትዮያ ህዝብ
ናሆም ግርማ/ከኖርዌይ

No comments:

Post a Comment