Sunday, November 6, 2016

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፣ በአፈሳም ሆነ በሌላ መልክ የተያዙ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ ተገለጸ፡፡


ከመስከረም 28 ቀን 2009 ጀምሮ መተግበር የጀመረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፣ በአፈሳም ሆነ በሌላ መልክ የተያዙ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ ተገለጸ፡፡ መንግስትም ቢሆን የተያዙ ሰዎችን ሁኔታ እናገራለሁ ከማለት ውጪ እስካሁን ድረስ ይፋ ያደረገው መረጃ አለመኖሩ ታውቋል፡፡ አንድ ወሩን ሊደፍን የአንድ ቀን ዕድሜ የቀረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ለበርካታ ሰዎች መታሰር፣ መገደል እና አካል መጉደል ምክንያት መሆኑ ይታወቃል፡፡
አዋጁን በበላይነት እንደሚያስፈጽም የተነገረለትን ኮማንድ ፖስት በዋና ጸሐፊነት ይመሩታል የተባሉት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በተደጋጋሚ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የታሰሩ ሰዎችን ኣያያዝ በይፋ ለመናገር አልደፈሩም፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ አባላት ናቸው ከተባሉ ሰዎች ጋር ስለተያዙ ሰዎች አያያዝ ተመካክረዋል ቢባልም፣ በውይይታቸው ወቅት ስለ ታሰሩ ሰዎች ወቅታዊ ሁኔታ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
አዋጁ መተግበር ከጀመረ አንስቶ ባሉት ቀናቶች ውስጥ በተለይም ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአፈሳ መልክ መያዛቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ ዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋቾች ጭምር ያወገዙትን አዋጅ የሚያስፈጽሙ በተለይ አጋዚ ወታደሮች በርካታ ዜጎችን ሲገድሉ፣ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ሰዎችንም ማሰራቸው ይታወቃል፡፡ ሴቶችን መድፈርም የኮማንድ ፖስቱ አንዱ አካል ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሰዎች፣ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙባቸው የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ –  ( BBN )

No comments:

Post a Comment