Thursday, August 25, 2016

እስካላገኘ ድረስ ጉዳዮን እስከ አለምአቀፍ የአትሌቲክስ ፊዴሬሽን(IAAF) ድረስ ለመውሰድ እንገደዳለን



“ይሁንታ አግኝተን ከተመረጥን ለመምራት ዝግጁ ነን፡፡”- አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ

by

image
በዳዊት ፀሀዬ|ነሀሴ 19፣2008
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ ከሰአት በብሔራዊ ሆቴል ተካሄደ፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫውን ላይ የተገኙት ጋዜጣዊ መግለጫውን የጠራውን የኢትዮጵያ አትሌቶች ጊዜያዊ ኮሜቴን በመወከል አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ፣አትሌት ገብረግዜአብሔር ገብረማርያም ፣አትሌት ገዛኸኝ አበራ ሲሆኑ ከነሱ በተጨማሪ እንዲሁ አሰልጣኞችን በመወከል ደግሞ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ እና የኦሜድላው አሰልጣኝ ኮማንደር አበበ በስፍራው በመገኘት ጋዜጣዊ መግለጫውን ሰጥተዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል ከነዚህም መካከል ስለ ኢትዮጲያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሰራር ፣ዶፒንግ፣ከአትሌቶች አሰለጣጠን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በዋናነት አፅንኦት ተሰጥቶባቸው በስፋት ሀሳብ ተንሸራሽሮባቸዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከተሰነዘሩት ሀሳቦች ውስጥ
ስለ ጋዜጣዊው መግለጫ አላማ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ሲናገር
“በዛሬው እለት እዚህ የተገናኘነው ስለሀገራችን ኢትዮጵያ ወቅታዊ የአትሌቲክስ ሁኔታና እና ስለወደፊቱ የአትሌቲክሳችን እጣ ፈንታ ለማውራት እንጂ እከሌን ከስልጣኑ ለማውረድ ወይም ለመፈጥፈጥ አይደለም ፤ ስፖርቱ በሽፍንፍኖሽ የሚታለፍ አይደለም እንዳለፈው የሪዮ 2016 ኦሎምፒክ እንጋለጣለን ምክንያቱም አትሌቲክስ በሚሊዮኖች ፊት የምኖረጠው  ከሀይማኖት እና ፓለቲካ የፀዳ ስፖርት ስለሆነ፤ ስለዚህ እንደኔ ሀሳብ የዛሬው ውይይታችን ሁሉንም ስፖርት ሊታደግ ይችላል በሚል እምነት የተጠራ ነው፡፡” ሲል ገልጿል፡፡
አትሌት ሀይሌ ይቀጥላል
“የዶፒንግ ጉዳይ በአፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘቱ የተነሳ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል፤ ጉዳዩ ሊያስቀጣን ይችል ነበር እዚህ ጋር አለመቀጣታችንን አትዩ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የአለም አቀፍ ፀረ አበረታች መድሀኒት ኤጀንሲ(ዋዳ) በራሱ ከአትሌቶቻችን ናሙና እየወሰደ ይመረምር ነበር አሁን ግን ራሳችንን በአንድ ናሙና እስከ 500የአሜሪካን ዶላር እየከፈልን ናሙናዎችን ወደ ኳታር እየላክን እናስመረምራለን፡፡ የዚህ የዶፒንግ ጉዳይ መዘዝ እስከ ሪዮ ኦሎምፒክ ድረስ ተከትሎን ሄዷል ፤አትሌት አልማዝ በ10ሺህ ሜትር በጥረቷ እና በላቧ ያመጣችውን ውጤት ጥርጣሬ ውስጥ እስከመክተት ድረስ ደርሷል፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡
ስለ ሪዮ ኦሎምፒክ አትሌቶች የምልመላ ሂደት አትሌቱ ሲናገር
“ስለ አትሌቶቹ ምልመላ ከዚህ ቀደም እጅግ በርካታ ጊዜ አውርተናል፤ መስፈርቱ የወጣው በርካታ አትሌቶች ውድድሮቻቸውን ሮጠው ከጨረሱ በኃላ ስለነበር ነው ከዚህ ቀደም ከኦሎምፒኩ በፊት እንደዚያ ስንቧቀስ የነበረው፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡
በሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ ሰንደቅ አላማውን ስለ ያዘው ግለሰብ ሀይሌ ሲናገር
“ባንዲራ ስለያዘው ሰው ጥቂት ሰው ነው የሚያውቀው ፤ቀነኒሳ በቀለ እና ደራርቱ ቱሉ ሲይዙ እና አንድ ሌላ ሰው ሲይዝ በጣም ልዮነት አለው፤ለምሳሌ ስለ ቀነኒሳ ገድሎች ኮሜንታተሩ ሲያወራ የአለም ህዝብ ሰፍ ብሎ ያያል ይህም በተዘዋዋሪ ሀገሪቷን በደንብ ያስተዋውቃል፡፡”በማለት መልሷል፡፡
በመጨረሻም ሀይሌ እንዲህ ሲል ተደምጧል
“በአትሌቲክሳችን ውጤት ማጣት እናንተ ከሚሰማችሁ ስሜት በብዙ እጥፍ ተባዝቶ እኛን ይሰማናል፤ ስፖርታችን አደጋ ላይ ነው ሙያተኛው ከሌለ ሙያው አይመራም ፤በኛ በኩል ያለው አቋም እስከመጨረሻው ገፍተን እንሄዳለን የሚል ነው ፤ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጠርቶ ክልሎች የሚልኩት በስፖርቱ ያለፈ እና ለቀጣይ የሀገሪቱ አትሌቲክስ ተገቢ የሆነ ሰው እስኪሆን ድረስ ትግላችን ይቀጥላል ፤ ይህንን ስንል ግን እኛ ሙያተኞች ሆነን አይደለም፤ ነገርግን ጥያቄያችን ምላሽ እስካላገኘ ድረስ ጉዳዮን እስከ አለምአቀፍ የአትሌቲክስ ፊዴሬሽን(IAAF) ድረስ ለመውሰድ እንገደዳለን ነገርግን ጉዳዮን ወደዛ መውሰዱ ብዙ መዘዞች ስላሉት እኛ እዛ ደረጃ ድረስ እንደርሳለን ብዬ እንኳ አላስብም ከዛ በፊት በመግባባት ሊፈታ ይችላል ብለን እንጠብቃለን ፡፡የኛ ሀሳብ አሁንም ችግሩ ያለው አሠራሩ ላይ ሳይሆን ሂደቱ ላይ ነው፡፡” ሲል ተናግሯል፡፡
በመጨረሻም ሀይሌ ገብረስላሴ ከተለያዩ ጋዜጠኞች የተነሱለትን ጥያቄዎች መልሷል፡፡
ከነዚህም መካከል ከአንድ ጋዜጠኛ የአሁኑ ፌዴሬሽን እንዳላችሁት ስልጣኑን ቢለቅ አትሌቶች ለመምራት ዝግጁ ናችሁ ወይ ተብሎ ለቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ
“ይሁንታ አግኝተን ከተመረጥን ለመምራት ዝግጁ ነን፤ በኛ በኩል እንደነ አትሌት ሚሊዮን ወልዴ እና አሰፋ መዝገቡ የመሳሰሉ ባለሙያዎችን ለቦታው ብቁ ናቸው ብለን እናስባለን፡፡ “ሲል ተደምጧል፡፡

No comments:

Post a Comment