Saturday, August 13, 2016

በከሚሴ መሣሪያ እየተነጠቀ ነው • በአርማጭሆ ከፍተኛ መጠን ያለው ጦር ገብቷል ነገ የተጋድሎ ሰልፍ ይጠበቃል



AmharaResistance;
ዐማራ እንዴት ዋለ? ነሃሴ 7 ቀን 2008 ዓ/ም
በደ/ማርቆስ ከ1000 በላይ ዐማሮች ታስረዋል፤ ነገም የተጋድሎ ሰልፍ ይኖራል
• በከሚሴ መሣሪያ እየተነጠቀ ነው
• በአርማጭሆ ከፍተኛ መጠን ያለው ጦር ገብቷል
• በወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሞጣ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ደብረ ብርሃንና ሌሎች ከተሞች ነገ የተጋድሎ ሰልፍ ይጠበቃል
• የሚታሰሩ ዐማሮች ቁጥር ጨምሯል፣ ገበሬዎች ወደ ከተማ እንዳይገቡ እየታገዱ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ በደብረ ማርቆስ ከተማ በርካታ የአጋዚ ወታደሮች ከተማዋን ወረዋት ቢዉሉም ሞትን የማይፈሩት የበላይ ዘለቀ ልጆች ለተጋድሎ ሰልፍ ወጥተዋል፡፡ ከጠዋቱ 4፡30 አካባቢ የተጀመረው የተጋድሎ ሰልፍ እስከ 8፡00 እንደቆየ ለማወቅ ችለናል፡፡ ከከተማዋ ሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች የነበረውን ሰልፍ ለመበተን ጥረት ተደርጓል፡፡ በሰልፉ ሁለት ዐማሮች የተሰው ሲሆን ቁጥሩ ወደ አራትም ሊያሻቅብ እንደሚችል ተገልጧል፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ ከሕዝብ ጎን ተሰልፏል የተባለ አንድ የዐማራ ፖሊስም በአጋዚ ጦር መገደሉን ከቦታው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በደብረ ማርቆስ በአጋዚ የተገደሉት ዐማሮች በድብደባ እንደሆነ ነው መረጃ ያቀበሉን ሰዎች የገለጹት፡፡ በጥይት በርካታ ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ከሰአት በኋላ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ የማርቆስ ወጣቶች በቀበሌ 03 አስተዳደር ጽ/ቤት መታሰራቸው ታውቆ ነበር፡፡ ከመሸ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማዋ የታሰሩ ሰዎች ብዛት ከ1000 እንደሚበልጥና የፖሊስ ጣቢያዎችና የቀበሌ ጽ/ቤቶች ሁሉ በመጥበቡ ምክንያት ሲኒማ አዳራሽ ተዘግተዋል ተብሏል፡፡
በደብረ ማርቆስ ነገም የተጋድሎ ሰልፍ እንደሚኖር የሚጠበቅ ሲሆን ዛሬ ከተሰሙት መፈክሮች ‹‹እንኳን ለወልቃይት ለባድመስ ታግለን አይደል!›› የሚለው የማኅበራዊ ሚዲያውን ተቆጣጥሮ ውሏል፡፡
ከሚሴ፤ በከሚሴ ያሉ ዐማሮች መሣሪያቸውን እየተገፈፉ እንደሆነ በጠዋት ነው መረጃው የደረሰን፡፡ የተጋድሎ ሰልፉን ያስተባብራሉ የሚባሉትን ወጣቶች እንደታሰሩም ለማወቅ ችለናል፡፡
አብደራፊ/አብራጂራ፤ ወደ ምዕራብ አርማጭሆ አብደራፊና አብራጂራ ከተሞች ከሦስት አቅጣጫዎች የመከላከያ ሠራዊት ከነሙሉ ትጥቁ ሲገባ መሰንበቱን ለማወቅ ችለናል፡፡ በሶረቃ በኩል የገባው የመከላከያ ሠራዊትና ትጥቅ 8 ኦራል እና 5 ዘመናዊ ታንኮች ሲሆን በመተማና በኹመራ በኩል የገባው የጦር መጠን ከዚህ የዘለለ ነው ተብሏል፡፡ ለምን ዓላማና እንዴት እንደገባ ለጠየቅናቸው ጥያቄ ‹‹በቄስና በመነኩሴ እያስገዘቱ ለይቅርታ ነው የመጣነው ቢሉም አሁን ላይ ግን ዐማሮችን ማደን ይዘዋል›› ሲሉ ገለጸዋል፡፡
አጠቃላይ፤ በወልድያ፣ ደሴና ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደጀን፣ ሞጣ፣ ብቸና፣ ፍኖተ ሰላም ከተሞች ወጣቶች በብዛት እየታሰሩ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚደርሱን፡፡ በወልድያ የሰሜን ወሎ የብአዴን ኃላፊ አቶ አበባው ሲሳይና የቅጥረኛ ካቢኔዎቹ በርካታ ወጣቶችን ፒያሳና አዳጎ በሚባሉ ሰፈሮች እንዳሳሰሩ ለማወቅ ችለናል፡፡ በግል ቢዚነስ የሚንቀሳቀሱ ብሎም የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ይገኙበታል፡፡ በደሴና በኮምቦልቻ ከተማዎች ለነገ ሠልፍ ይኖራል በሚል የፈሰሰው የአጋዚ ጦር መጠን ብዛት አለው ተብሏል፡፡
በደሴ ከተማ በቀን ሥራና በሊስትሮነት የተሠማሩ ልጆችን ፖሊሶች በመዞር እያስፈረሙና እየመዘገቡ ነገ ሰልፉ ላይ ብትገኙ ወዮላችሁ ስማችሁን መዝግበናል እያሉ ውለዋል፡፡ በኮምቦልቻ ከተማ ደግሞ የቀን ሠራተኞችንና የኔ ቢጤዎችን እስከ ቅዳሜ ድረስ ሠርታችሁ ከተማ መገኘት የለባችሁም፤ ቦርከና ወንዝ ልብስ ስታጥቡ ዋሉ ተብለዋል፡፡
በምስራቅ ጎጃሟ የብቸና ከተማ ዛሬ ማንኛውም ዓይነት የንግድ እንቅስቃሴ ባንክን ጨምሮ ዝግ ሆኖ ውሏል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚመጡ አርሶ አደሮች እንዳይገቡም ተከልክለዋል፡፡ የዐማራን ሕዝብ ለመግደል የተመደቡት የአጋዚ ጦር አባላት የሚመገቡት በከተመዋ ከሚገኘው ‹‹ጽጌረዳ ሆቴል›› እንደሆነ ነው የተነገረን፡፡ በሞጣ፣ በደጀን፣ በዕድውኃ፣ በፍኖተ ሰላም ከገጠር የሚመጡ ገበሬዎች እንዳይገቡ መከልከላቸው ተሰምቷል፡፡
ከመንዝ ላሎ እና ማማ ምድር ወደ ደብረ ብርሃን የሚመጡ ገበሬዎች ላይ ከፍተኛ ፍተሻና ወከባ እንዳለም ለማወቅ ችለናል፡፡

ይህ ሁሉ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው//
Image may contain: outdoor and one or more people

No comments:

Post a Comment