Sunday, August 28, 2016

የሰማያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ በኦዲት ኮሚሽኑ ተበተነ

  


የሰማያዊ ፓርቲ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን በተነ፡፡ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ለመምረጥና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መስከረም 2009 ዓ.ም. እንደሚያደርግ፣ የፓርቲው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው ነሐሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የሥራ አስፈጻሚው ጉዳይ ተነስቶ ውይይት መደረጉን ያስታወሱት አቶ አበራ፣ ‹‹ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በቁጥር የተጓደለ  ነው፡፡ በተጓደሉ አባላት ምትክ መርጦ ማሟላት አልቻለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ የማስፈጸም አቅም አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ኮሚሽኑ ሥራ አስፈጻሚውን በትኖ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ወስኗል፤›› በማለት አክለው አስረድተዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው እስከሚሰበሰብ ድረስ የፓርቲው እንቅስቃሴና የዕለት ተዕለት ሥራው አይታጐልም ወይ በሚል ከሪፖርተር ለቀረበ ጥያቄ፣ ‹‹አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የተጠራበት አንደኛው ምክንያት ይኼ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ምክትል ፕሬዚዳንቱ እየሠሩ ይቆያሉ፡፡ በዚህ አሠራር ሙሉ በሙሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን ሥራ ሸፍኖ መሥራት እንደማይቻል የታወቀ ነው፡፡ ይህ የራሱ የሆኑ እንቅፋትና ችግሮች አሉት፡፡ እስከዚያው ድረስ የሚሸፈኑ ነገሮች ካሉ ይሸፈናሉ፡፡ መሸፈን የማይችሉት ነገሮች ደግሞ እንቅፋት እንደሆኑ ይቀጥላሉ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ነገሠ ተፈረደኝ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መበተኑን ለሪፖርተር ያረጋገጡ ሲሆን፣ ቀጣይ ጠቅላላ ጉባዔ እስከሚሰበሰብ ድረስ የፓርቲውን ሥራ እያከናወኑ እንደሚቆዩ አስረድተዋል፡፡
በሰማያዊ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ 11 አባላት እንደሚኖሩት ይገልጻል፡፡
ነገር ግን ባለፈው መስከረም በተካሄደው የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ፕሬዚዳንቱ ካቀረቧቸው ዕጩዎች መካከል፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ሦስቱን አለመቀበሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ስምንት ሆነው ሥራ መጀመራቸውን የሚያስታውሱት አቶ ነገሠ፣ ‹‹ከስምንታችን በልዩ ምክንያት እንደገና አንድ አባል ጐደለ፡፡ ሰባት ሆነን በምንሠራበት ወቅት በፓርቲው ውስጥ የተለያዩ አለመግባባቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ ስለሆነም ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ተወስኖ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይከናወን ቀረ፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ከሰባቱ አባላት መካከል ሁለቱ በተለያዩ ምክንያት ሳይገኙ ቆዩ፡፡ ሊቀመንበሩ [ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት] ደግሞ ወደ ካናዳ ከሄዱ ሁለት ወር ሊሆናቸው ነው፤›› በማለት የውሳኔውን ምክንያት አስረድተዋል፡፡
‹‹በአራት ሥራ አስፈጻሚዎች የአሥራ አንድ ሰዎች ሥራ መሥራትና ምልዓተ ጉባዔ ማሟላት ያስቸግራል፤›› ሲሉም አሁን በፓርቲው ውስጥ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡
የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የፓርቲው ፕሬዚዳንት በማይኖርበት ወቅት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ተክቶ ይሠራል ስለሚል፣ እስከሚቀጥለው ጉባዔ ድረስ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የፓርቲውን ሥራዎች እያከናወኑ ይቆያሉ፡፡

No comments:

Post a Comment