Monday, October 24, 2016

የህዝብን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ተቀራርቦ በመነጋገር እና በመወያየት ሃገራዊ ማኒፌስቶ በማምጣት የጋራ ሃገራዊ አጀንዳ በመቅረጽ ለለውጥ መትጋት ግዴታ ነው::ምንሊክሳልሳዊ



የህዝብን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ተቀራርቦ በመነጋገር እና በመወያየት ሃገራዊ ማኒፌስቶ በማምጣት የጋራ ሃገራዊ አጀንዳ በመቅረጽ ለለውጥ መትጋት ግዴታ ነው::
 
Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል።የሕዝቡ ብሶት ገንፍሎ ኣደባባይ በመውጣት የወያኔን ዘረኛ ኣገዛዝ እየተፋለመ ያለውም ለዚሁ ለለውጥ ያለው ፍላጎት ነው። ለውጥ ሳይታለም የተፈታ እና የሁሉም የነጻነት ፈላጊ ሃይሎች ጥያቄ ነው። በሃገር ውስጥ ያሉትን ፓርቲዎች መዋቅሮቻቸውን በማጠናከር የውስጥ ድክመቶቻቸውን በመቅረፍ እንዲጠነክሩ የማድረግ ግዴታ ከለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ይጠበቃል። መመካከር መተራረም ግድ ይላል። በውጪው አለም የሚገኙ የነጻነት እና የለውጥ ሃይሎች እንዲጠናከሩ እና ከጥልፍልፎሽ ፖለቲካ ወተው ጠንካራ ሃይል እንዲሆኑ የዲያስፖራው ሃይል ከበፊቱ በበለጠ መልኩ ሊሰራ ግድ ይለዋል። የወያኔ የጎን ውጋት እና የራስ ምታት የሆነው ዲያስፖራው የጀመረውን የትግል ስልት እና ትጋት በማስፋት ሚዲያዎችን በማጠናከር እና የነጻ አውጪ ፓርቲዎችን በመርዳት በማግባባት ጠንካራ ሰንሰለት ከሃገር ቤት ጋር በመፍጠር ሕዝብን ከጨቋኞች ነጻ ማውጣት አለበት።ዲያስፖራው በየቀኑ ወያኔ የሚፈጥረውን ተራ የቤት ስራ እና የማደናገሪያ ማዘናጊያ አሉባልታ ፊት ሳይሰጠው በለውጡ ጉዳይ ላይ በማተኮር በሃገር ቤት ያለው ሃይል እንዲስማማ የፖለቲካ ጡዘቶች ክፍተት እንዳይኖር ተቀራርቦ እንዲሰራ ትልቁን ሚና መጫወት አለበት::
 
የሚዲያ ተቋማት እና የድህረገጽ ውጤቶች ሕዝብን በማስተማር ሕዝብን መብቱን እና ነጻነቱን አውቆ ለሌላው እንዲያስተምር በማድረግ ረገድ አስፈላጊውን ወቅታዊ መረጃ እና መነሳሳትን በማስረጽ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል። ያለፉ እና የከሰሙ ወሬዎችን እና አሉባልታዎችን ከመርጨት የወያኔ የፈጠራ አደናባሪ እና አዘናጊ አጀንዳዎችን እኝኝ በማለት ከማውራት ብሄር ተኮር ክፋፋይ ሃሳቦችን ከማርከፍከፍ አዛኝ መሳይ መርዝ ሃሳቦችን ከመናገር ተቆጥበን ሕዝቡን ስለመብቱ እና ነጻነቱን በማስተማር ረገድ መትጋት ከተያዘ ለውጥ የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም። ትችትን እና ሂስን ላለመዋጥ እውነትን ላለመቀበል የሚደረጉ ሩጫዎች ታጥቦ ጭቃ እንጂ የትም እንደማያደርሱ እንዲሁም ፓርቲዎችን እና ሰዎችን መፈረጅ እና መወንጀል ሃሳቦችን ማጣጣል ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ካለፈው ተምረናል ። ያሳልፍነው የትግል ሂደት ከጭብጨባ እና ስብሰባ ያለፈ ፋይዳ እንዳሌለው ተገንዝበን የወሬ እና ሆይሆይ ትግል ስለማያዋጣ ጥንካሬን እና ለውጥን የምናመጣበትን የትግል ስልት በመመካከር እና በመወያየት ሃሳብን በማቻቻል መረጃ በመለዋወጥ ሃገራዊ የጋራ አጀንዳ ሊኖረን ይገባል እላለሁ። #ምንሊክሳልሳዊ

No comments:

Post a Comment