Sunday, October 9, 2016

በሳምንት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ከ130 በላይ ኩባንያዎች ወደሙ ቆንጅት ስጦታው


በሳምንት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ከ130 በላይ ኩባንያዎች ወደሙ
ካለፈው ሳምንት ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል እንደገና ባገረሸው ተቃውሞ፣ እስካሁን ከ130 በላይ ግዙፍና መለስተኛ ኢንቨስትመንቶችን ማውደሙ ተገለጸ፡፡
በተለይ ከአዲስ አበባ ከተማ በ100 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፣ የኤሌክትሪክና የኮሙዩኒኬሽን ኬብሎች ፋብሪካ፣ የፕላስቲክ ታንከር ፋብሪካ፣ የጠጠር ማምረቻ ፋብሪካ፣ የአበባና የተለያዩ እርሻዎች፣ ሎጆች፣ ወዘተ. ሙሉ ለሙሉና በከፊል ወድመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የሕዝብ ማመላለሻ፣ ከባድ የጭነትና የግልና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ወድመዋል፡፡
እንዲሁም የቀበሌ አስተዳደር ሕንፃዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ የአርሶ አደሮች ማሠልጠኛ፣ የጤና ኬላዎች ተቃጥለዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይል የሌለ እስኪመስል ድረስ በጉትጎታ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የውጭ ኩባንያዎች፣ አገር በቀል ኩባንያዎች፣ የግለሰብ ቤቶችና ንብረቶች ተዘርፈዋል፤ በእሳት ጋይተዋል፡፡
ከሰኞ መስከረም 23 ጀምሮ እስከ ዓርብ መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ባሉት አምስት ቀናት ብቻ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታና ቱሉ ቦሎ አካባቢ 11 ፋብሪካዎችና አራት የአበባ እርሻዎች ወድመዋል፡፡ 62 ከባድ የሕዝብና የጭነት ተሽከርካሪዎች ወድመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግዙፉ የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሳይገን ዲማ፣ ሱፐር ፋይቨር ሮቶ ታንከር ፋብሪካ፣ ቱቱ እና ቤተሰቧ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ ቢኤምኢቲ ኬብል ፋብሪካ፣ ዳስ ትሬዲንግና ሰላም ባልትና ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ለ40 ሺሕ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡
በምዕራብ አርሲ ጎልጀታ አካባቢ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢኮ ሎጅ የሆነው ቢሻንጋሪ ሙሉ ለሙሉ ሲወድም፣ በዚሁ አካባቢ የሚገኝ የእህል መጋዘንና የፖሊስ ጣቢያም ጋይተዋል፡፡
በምዕራብና በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በምዕራብ ወለጋ ደምቢዶሎ፣ ቀደም ሲል አገረ ማርያም አሁን ቡሌ ሆራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ በምዕራብ አርሲ (ነገሌ፣ አሳሳ፣ ዶዶላ) ውድመቱና ደም አፋሳሽ ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግጭቱ ያስከተለውን ውድመት በትክክለኛው መረጃ ለማወቅ ከተለያዩ ቦታዎች ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡ ነገር ግን የክልሉ መንግሥት ሪፖርቶቹን ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ከገመገመ በኋላ በይፋ እንደሚገልጽ ጠቁመው፣ ለጊዜው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ድርጅቶች አንዱ ቢሻንጋሪ ሎጅ ነው፡፡ የባገርሽ ቢዝነስ ግሩፕ እህት ኩባንያ ኢኮ ሎጅ እ.ኤ.አ. በ1998 የተመሠረተ ነው፡፡ ኩባንያው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ጎልጀታ አካባቢ 100 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቦ ግንባታ ካካሄደ በኋላ፣ እ.ኤ.አ. በ2002 ዓ.ም. ታዋቂውን ቢሻንጋሪ ኢኮ ሎጅ ለኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ደንበኞችን መቀበል ጀመረ፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኢኮ ሎጅ ሆኖ የተመሠረተው ቢሻንጋሪ በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን፣ 60 ሠራተኞች አሉት፡፡ ኩባንያው ሙሉ ለሙሉ የሥራ ዕድል የፈጠረው ለአካባቢው ነዋሪዎች ሲሆን፣ ለአካባቢውም ነዋሪዎች 17 የቢዝነስ ሐሳቦችን በማመንጨት በዶሮ እርባታ፣ በዕደ ጥበብና በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩ እገዛ በማድረግ ምርታቸውን ከመረከቡም በላይ፣ በሎጁ ውስጥም መደብር ተከፍቶ ለተጠቃሚዎች እንደሚሸጥ አስታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለአካባቢው ትምህርት ቤት ውኃ አውጥቶ ከመስጠት ጀምሮ፣ የተለያዩ እገዛዎች ያደርግ እንደነበር የኩባንያው መሥራችና ባለቤት አቶ ኡመር ባገርሽ ባለፈው ዓርብ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
የቢሻንጋሪ ሎጅ ኦፕሬሽን ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ ዘለዓለም ቤኩማ፣ ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት 3፡00 ሰዓት ላይ በሎጁ ጀርባ የተወሰኑ ሰዎች መግባታቸውን፣ የሎጁ የጥበቃ ሠራተኛ ሰብረው ከገቡት መሀል አንዱን በመያዝ ለአካባቢው ሽማግሌዎች በደንቡ መሠረት አሳልፈው መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ሽምግልናው ሳይሠራ የተያዘው ሰው ተለቀቀ ይላሉ፡፡ ማክሰኞ ደግሞ የተደራጁ 60 የሚሆኑ ወጣቶች እየዘፈኑ ዋናውን በር ሰብረው ገቡ፡፡ ከአካባቢው ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ወጣቶችን በመለመን እንደመለሷቸው አቶ ዘለዓለም ተናግረዋል፡፡ በተደጋጋሚ የተደረገው የማግባባት ሥራ በመጨረሻ ውጤት ማስገኘት ግን አልቻለም፡፡
ረቡዕ ምሽት 5፡00 ሰዓት ላይ ወጣቶቹ በተደራጀ መንገድ የሰው ኃይል ጨምረው ገቡ፡፡ ‹‹አሁን ከሽማግሌዎችም ሆነ ከሎጁ ሠራተኞች አቅም በላይ ስለነበር ወጣቶቹ ዘረፋ ጀመሩ፤›› ሲሉ አቶ ዘለዓለም ሁኔታውን ያስረዳሉ፡፡ ወጣቶቹ የቻሉትን ያህል ከዘረፉ በኋላ ሎጁ ላይ እሳት ለኩሰው እንደሄዱ አስረድተዋል፡፡
‹‹ለአርሲ ነገሌ ፖሊስ ሁኔታውን ብናስረዳም ፖሊስ ጣቢያው ድልድዮች በመሰበራቸው መምጣት እንደማይችሉ፣ ይልቁኑም እኛ ራሳችን ተደራድረን ችግሩን እንድንፈታ ገልጸውልናል፤›› ሲሉ አቶ ዘለዓለም ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ላለፉት 14 ዓመታት በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን ሲያስተናግድ የቆየው ቢሻንጋሪ ሎጅ ሙሉ ለሙሉ መውደሙን፣ በአሁኑ ወቅትም ከቃጠሎ የተረፈው ንብረትም መዘረፉን ገልጸዋል፡፡
‹‹ልጄ የሞተብኝ ያህል ነው ያዘንኩት፤›› ሲሉ የቢሻንጋሪ ሎጅ መሥራችና ባለቤት አቶ ኡመር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቱሪስት እና ሰላም አይነጣጠሉም፡፡ ቢሻንጋሪን ዳግም የመገንባት ዕቅድ የለኝም፤›› ሲሉ አቶ ኡመር ተስፋ በቆረጠ አንደበት ገልጸዋል፡፡ ከቢሻንጋሪ ሎጅ ባሻገር የሚገኘው የቀድሞ በቀለ ሞላ ሆቴሎች ሥር ይተዳደር የነበረው የአሁኑ ሲምቦ ቢች ሪዞርት ባለፈው ዓርብ በከፊል ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡
የሲምቦ ቢች ሪዞርት ሎጅ ኩባንያ መሥራች አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ሎጃቸው በከፊል የቃጠሎ አደጋ ደርሶበታል፡፡ ነገር ግን የውድመቱን መጠን ለማወቅ መረጃ ተጠናቅሮ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል፡፡
ሱፐር ፋይቨር ኩባንያም ከባድ ውድመት አጋጥሞታል፡፡ ይህ ኩባንያ በሰበታ ከተማ በ13 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የፕላስቲክ ታንከር ፋብሪካ ከፍቶ ላለፉት አሥር ዓመታት ምርቱን ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
የሱፐር ፋይቨር ኩባንያ ባለድርሻ ወ/ሮ ትዕግሥት ጌትነት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡30 ላይ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ በርካታ ወጣቶች መጡ፡፡ ወጣቶቹ በጀሪካን ነዳጅና ተቀጣጣይ ጎማ ይዘው በመግባት የጥሬ ዕቃ ማከማቻና ያለቀለት ምርት ማቆያ መጋዘን ላይ እሳት መልቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ ትዕግሥት እንዳሉት እሳቱ ወደ ፋብሪካው ባይዘመትም፣ የተከማቸ ጥሬ ዕቃና ያለቀለት ምርት ሙሉ ለሙሉ ወድሟል፡፡ ቢያንስ የወደመው ንብረት 35 ሚሊዮን ብር ግምት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹1,500 ሠራተኞች ነበሩን፡፡ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ሥራ አቁመናል፡፡ ይህ ፋብሪካ የእኛ ብቻ ሳይሆን የሕዝብም ጭምር ነበር፤›› ሲሉ የገለጹት ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ፋብሪካቸው ለአካባቢው ማኅበረሰብ ከጉድጓድ ውኃ አውጥቶ ይሰጥ የነበረ ቢሆንም የውኃ ማጠራቀሚያውን ጭምር እንዳጠፉት አስረድተዋል፡፡
‹‹አጥፊዎቹ የሽምቅ ተዋጊ ዓይነት ባህሪ አላቸው፡፡ የፀጥታ ኃይሎች እንዳይገቡ መንገድ እየዘጉ ነው ይህንን እኩይ ተግባር የሚፈጽሙበት፤›› ሲሉ የተናገሩት ወ/ሮ ትዕግሥት፣ መንግሥት በተቻለው አቅም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ሱፐር ፋይቨርን ጨምሮ በሰበታ ከተማ ከተቃጠሉት 11 ፋብሪካዎች መካከል ቢኤምኢቲ ኢነርጂ ቴሌኮም ኢንዱስትሪ ኤንድ ትሬድ የተባለው ኩባንያ ይገኝበታል፡፡ ይህ የቱርክ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ2012 በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ የሆነውን የኤሌክትሪክና የኮሙዩኒኬሽን ኬብሎች ማምረቻ ፋብሪካ ገምብቶ ወደ ምርት ገብቷል፡፡
ኩባንያው ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ወደዚህ ሥራ ቢገባም፣ ምርት ከጀመረ ከአራት ዓመት በኋላ ያላሰበውና ያልገመተው ውድመት ገጥሞታል፡፡
የኩባንያው የሰው ኃይልና የፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ ደሳለኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ብዛት ያላቸው ወጣቶች ወደ ግቢው ዘልቀው በመግባት ዋና መሥሪያ ቤቱን አቃጥለዋል፡፡ በቢሮው ውስጥ የሚገኙ ሰነዶችና ኮምፒውተሮች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡
‹‹ከባዶ ነው የምንነሳው፤›› በማለት ፋብሪካው ያለ ሰነድ መቅረቱን አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡ የኬብል ፋብሪካው ባይነካም ቢሮው ከነሰነዱና ከጂቡቲ ዕቃ ጭነው የገቡ አራት ከባድ ተሽከርካሪዎች ከያዙት ዕቃ ጋር ነደዋል፡፡
‹‹አጥፊዎቹ ብዛት ስላላቸው በወቅቱ የሚያስቆማቸው ኃይል አልነበረም፤›› በማለት የገለጹት አቶ ደረጀ፣ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል ፖሊስ ግቢውን እንደተቆጣጠረ ገልጸዋል፡፡ የወደመው ንብረት መጠን እስካሁን አለመታወቁንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ሌላኛው የጥቃቱ ሰለባ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ታዋቂ እየሆነ የመጣው አሰር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ይገኝበታል፡፡
አሰር ኮንስትራክሽን ከአዲስ አበባ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቢሾፍቱ – አዱላላ-መቂ ያለውን 55 ኪሎ ሜትር አቋራጭ መንገድ በ700 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተረክቧል፡፡
አሰር ኮንስትራክሽን ለመንገድ ግንባታ ያሰማራቸው ዘጠኝ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች በዚህ ሳምንት በተለያዩ ቀናት ውስጥ እንደወደሙበት ታውቋል፡፡
ከአሰር ኮንስትራክሽን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በአካባቢው ንብረቶችን የሚያወድሙ አካላት ካምፑን ለማውደም በሚዘጋጁበት ወቅት የመከላከያ ሠራዊት ደርሶ ከቃጠሎ አድኖታል፡፡ አሰር ኮንስትራክሽን የዚህን መንገድ ግንባታ 70 በመቶ ያህል አጠናቆ እንደነበር መረዳት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ እንደገና ሥር እየሰደደ በነበረው ተቃውሞ ሰፊ ቦታ የሚሸፍን በመሆኑ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ፌዴራል ፖሊስ ሊቆጣጠሩት እንዳልቻሉ እየተነገረ ነው፡፡
ተቃውሞው እየተካሄደ ያለው የፀጥታ ኃይሎች እንዳይደርሱ መንገድ እየተዘጋ ጭምር በመሆኑ፣ አመጹም ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ስለሆነ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መጠን ንብረት እየወደመ ነው፡፡
እየወደሙ ከሚገኙት ንብረቶች መካከል ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎች፣ የቱሪስት ማረፊያ ሎጆችና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
የኦሮሚያ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱና የፌዴራል ፖሊስ ምንጮች ፖሊስ አመፁን እየተቆጣጠረ መሆኑን ቢገልጹም፣ ከኦሮሚያ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ግን ክልሉን ቃጠሎ እየበላው መሆኑን የሚገልጹ ናቸው፡፡
አመጹ የትራንስፖርት እንቅስቃሴንም የገታ ሲሆን፣ ለአብነት በወዲያኛው ሳምንት ቅዳሜና እሑድ በምዕራብ አርሲ በሚገኙ የገበያ ሥፍራዎች ለንግድ የተጓጓዙ ነጋዴዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች እስካለፈው ዓርብ ወደ ቀዬአቸው አልተመለሱም፡፡ ከሐረር ወደ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ወደ አምቦና ነቀምት የሚደረጉ ጉዞዎች እንዲሁ ችግር እንደገጠማቸው መንገደኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተለይ በምዕራብ አርሲ የቀበሌ አስተዳደር አካላትን በማስወገድ በጎበዝ አለቃ ለመተዳደር እየተሞከረ መሆኑ ታውቋል፡፡
እየወደሙ ያሉ ንብረቶች የባንክ ብድር ያለባቸውና የኢንሹራንስ ሽፋን ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ ክስተት በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል ተሠግቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ዋስትና ሰጥቶ ያስገባቸው ኩባንያዎችም እንደመሆናቸው፣ ይህ ያልተጠበቀ ክስተት መንግሥትን በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ካሳ ሊያስከፍለው እንደሚችል ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡
በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መሠረት በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ከ350 በላይ ወረዳዎች ዳግም ባገረሸው ተቃውሞ ጉዳት የደረሰው በ50 ወረዳዎች ነው፡፡ ባለፈው ዓርብ ግን በአብዛኞቹ ሥፍራዎች መረጋጋት መፈጠሩን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡ በምዕራብና በምሥራቅ አርሲ ከሚገኙ ሁለት ወረዳዎችና ከነገሌ ቦረና በስተቀር ሰላማዊ ድባብ መፈጠሩን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ስብሰባ አዲስ አበባ የመጡት የ31 ዓመቷ አሜሪካዊት የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ሻሮን ግሬይ ቡራዩ አካባቢ በተወረወረ ድንጋይ ተመተው ሞተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተገደሉት አሜሪካዊ አስከሬን ወደ አገራቸው ተሸኝቷል፡፡

No comments:

Post a Comment