Friday, October 14, 2016

የኢትዮጵያ ጀግና የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ ቆንጅት ስጦታው  




ሶማሊያ ኢትዮጵያን በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ግንባሮች በወረረችበት ወቅት (1969-1970) በተዋጊ ጄት አብራሪነት ወደር የሌለው ጀግንነት በመፈጸማቸው ከቀድሞው መንግሥት ‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ›› እና የ‹‹የካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን›› ተሸላሚ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡
Teddy Habesha's photo.
በሥርዓተ ቀብራቸው በተነበበው የሕይወት ታሪክ እንደተገለጸው፣ ከሶማሊያ ጋር በ1969 ዓ.ም. በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር ኃይል በምዕራፍ አንድ ዘመቻው ጄኔራል ለገሠና ጓዶቻቸውን አሰማርቶ ከሐምሌ 17 ቀን እስከ ነሐሴ 28 ቀን 1969 ዓ.ም. ድረስ በተናጠልና በቡድን ሆነው ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር ባካሄዱት የአየር ለአየር ውጊያ የጠላትን 12 ሚግ 21 እና 13 ሚግ 17 በድምሩ 25 ተዋጊ አውሮፕላኖች ከአየር ላይ በማራገፍ አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ጄኔራል ለገሠ በደቡብ ግንባር መስከረም 11 ቀን 1970 ዓ.ም. በነበረው ውጊያ አውሮፕላናቸው በመመታቱ በፓራሹት በመውረድ ቢተርፉም በሶማሊያ ሠራዊት እጅ በመውደቃቸው ለ11 ዓመት በጦር እስረኝነት ሶማሊያ ውስጥ ቆይተዋል፡፡ ከአባታቸው ከአቶ ተፈራ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ ተናኜ ተክለ ወልድ፣ ነሐሴ 13 ቀን 1934 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ሾላ ላም በረት አካባቢ የተወለዱት ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ፣ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደጃዝማች ወንድይራድና በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል፡፡
Teddy Habesha's photo.
አገራቸውን በውትድርና ሙያ ለማገልገል በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ፣ ጥቅምት 1 ቀን 1956 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሐረር ጦር አካዴሚ የ7ኛ ጊዜ ተወዳዳሪ ዕጩ መኮንን በመሆን፣ አንጋፋውን የምድር ጦር ሠራዊት ሲቀላቀሉ፣ በሐረር አካዴሚ የአዛዥነትን ትምህርት ሲያጠናቅቁም ወደ አየር ኃይል ተዛውረዋል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የነበሩትና በ75 ዓመታቸው ያረፉት ጄኔራል ለገሠ ሥርዓተ ቀብር በኢትዮጵያ አየር ኃይል እግረኛ ወታደር ታላቅ አጀብና የማርሽ ባንድ የሐዘን ዜማ ታጅቦ ሲፈጸም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፣ የቀድሞዎቹ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍሥሐ ደስታና ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን ጨምሮ የቀድሞ መንግሥት ከፍተኛ መንግሥታዊና ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዲሁም ወዳጅ ዘመድ ተገኝተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment