Tuesday, March 14, 2017

መንግስታዊ ቸልተኝነት እና ብሔራዊ የሐዘን ቀን! – (ይድነቃቸው ከበደ) source zhabesha


መንግስት በደረሰበት ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዲሁም ፣ በማህበራዊ ድረ ገጾች በተለያየ መንገድ ይደረግ የነበረው ቅስቀሳ ባሳደረው ግፊት፣ ብሔራዊ የሐዘን ቀን በኢትዮጵያ ሊታወጅ ችሏል።በዚህም መሰረት ፣ ከመጋቢት 3 እስከ መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ.ም ለሦስት ቀን ብሔራዊ የሃዘን ቀን እንዲሆን ተወስኖል።

በመንግስት ግዴለሽነት ምክንያት ብቻ ! በደረሰው የቆሻሻ ክምር መናድ ፣ከ75 ሰው የማያንስ ለሞት የተዳረገ ሲሆን በመቶ የሚቆጠሩ ለከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ። እንዲሁም ከ250 የማያንሱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን በጊዚያዊ መጠለያ እንዲቆዩ ተደርጓል ። በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የደረሰው አደጋ፣ የዓለማችን ታላላቅ የመገናኛ ብዙሃን በፊት ገጻቸው ሰፊ የዜና ሽፍና ሰጥተውታል ።

መንግስት አደጋው ከደረሰ ከሦስት ቀን በኋላ ፣ በደረሰበት ከፍተኛ ግፊትና ተጽዕኖ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ከማወጁ በፊት ፣ በአዲስ አበባ የጀርምን ኢምባሲ በደረሰው አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን በመግለጽ ፣ በኢምባሲው የጀርመን እና የአውሮፓ ህብረት ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ ለኢትዮጵያውያን የጀርመን መንግስት አጋርነቱን አሳይቷል ። ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት ፣በደረሰው አደጋ ማዘናቸውን በመግለጽ ፣ ለአደጋው መንስኤ መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፣የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፣ አደጋው በደረሰበት አካባቢ በመሄድ ፣ የሟች ቤተሰቦችን እያጽናኑ የሚገኝ ሲሆን፣ ከነፍስ አድን ሰራተኞች ጋር በመተባበር ፣ በቆሻሻ ክምር ውስጥ በህይወት የተረፈ እና ጉዳት የደረሰባቸውን በማፈላለግ ላይ ይገኛሉ። አደጋው በተከሰተበት ቦታ የተገኘው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም ፣ አቶ ታሪኩ ደሳለኝ (ሚኪ) በቦታው ተገኝቶ በማህበራዊ ድረ ገጹ እንደገለጸው ከሆነ ፣ “ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የሞቱት ነብስ ይማራ ለማለት ቤተሰቦቻቸውን ለማፅናናት ተገኝቻለሁ። በየአምስት ሜትሩ ድንኳን ተተክሎ ማየት ያሰደነግጣል። አንዳንዱ ጋር ለሦስት ለአራተ ሰው በአንድ ድንኳን ሀዘን ተቀምጠዋል። አሁንም ከቆሻሻው ክምር አስክሬን እየወጣ ነው። እኔ ከደረስኩበት ከ12 እስከ 3 ሰዓት ብቻ 12 አስክሬኖች ወጥተዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚናገሩት ይሄ ከላይ ያለው ናዳ ቆሻሻ ውስጥ የተገኙ ናቸው ገና የታቸኛወ ውስጥ ይቀራል ብለዋል። አሁንም ውሃ መብራት የለም።አሁንም በዙ ሰው አልወጣም ብዙዎች ያለመጠለያ ቀርተዋል።የተቻላችሁን የሀል ድግፍ እንድታደርግ “በማለት የተሰማውን ገልጸዋል ።

ሌላው የዓይን እማኝ የሆነው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ፣ በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተገኝቶ ሃሳብን እንደሚከተለው ገልጸዋል ።”50ዎቹ በደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል ። የሟቾቹ ቁጥር 65
ደርሷል። ፍለጋው እንደቀጠለ ነው። ከሟቾቹ ውስጥ የአንድ ቤት አምስት የቤተሰብ አባላት ይገኙበታል ። ኮልፌ እስላም መቃብር ሀዘንተኛው ነስሩ ሁሴን ተጠጋሁት፣ “እህቴን፣ የእህቴ ሁለት ልጆች፣ የወንድሜ ሚስት ከነልጇ ይሄው ቀበርናቸው” ኡኡታውን አቀለጠው።” በማለት የተሰማውን ሃዘን አጋርቷናል። በመንግስት ግዴለሽነት ምክንያት ብቻ በደረሰው አደጋ ፣የተለያዩ ሰዎች የተለያየ አሰተያየት እየሰጡ ይገኛል

ህይወታቸውን ላጡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር ፤ ለቤተሰቡና ለወዳጅ ዘመድ መጸናናት ፈጣሪ ይስጥልን ፤አሜን!!!

No comments:

Post a Comment