Tuesday, March 7, 2017

የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ትናንት የጀመረውን ስብሰባ ዛሬም ቀጥሏል | የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ውሳኔ ሊተላለፍ ይችላል

(ቢቢኤን) የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በትናንትናው ዕለት መደበኛ ስብሰባውን መጀመሩ ተገለጸ፡፡ የአራት ፓርቲዎች ውህድ የሆነው ፓርቲው በሚኖረው የሶስት ቀናት ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል፡፡ ፓርቲው ውሳኔ ያሳልፍባቸዋል ተብሎ ከተያዙ ጉዳዮች መካከል አንዱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሚሆን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በመጪው መጋቢት 28 ቀን 2009 ስድስተኛ ወሩን የሚይዘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ ይነሳ ወይስ ይቀጥል በሚለው ጉዳይ ላይ መንግስት ወጥ አቋም ሳይዝ ቆይቷል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው የኢህአዴግ ባለስልጣናት በአስቸኳይ አዋጁ ዙሪያ የተለያየ አቋም መያዛቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አብዛኞቹ የህወሓት ባለስልጣናት አዋጁ ከስድስት ወርም በላይ እንዲቆይ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፣ ከፊሎቹ ደግሞ የውጭ ለጋሾችን ተፅዕኖ በመፍራት አዋጁ ከስድስት ወር በላይ ባይቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው ምንጮች ይገልጻሉ፡፡
አዋጁ እንደ አጠቃላይ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሲታይ ደግሞ፣ አዋጁ ይፋ ሲደረግ የተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ባይቀጥል የሚል በላጭ አመለካከት እንዳለም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ሀገሪቱ ‹‹መረጋጋቷን›› ሲገልጹ የሚደመጡት የኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ሀገሪቱ መረጋጋቷን ለውጭ ዲፕሎማቶች እና ለጋሽ ሀገራት ለማሳየት አዋጁን የማንሳት ፍላጎታቸው አመዝኗል ተብሏል፡፡ ሆኖም በፓርቲው ውስጥ ያለው ወጥ ያልሆነ አቋም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ በቀጣይ የስብሰባ ቀናት ምን ዓይነት ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚችል ከወዲሁ ለመገመት አዳጋች ሆኗል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይፋ ከተደረገ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸው እና በርካቶችም ሀገር ጥለው መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment