Monday, March 20, 2017

የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነት (የጉዞ ማስታወሻ) አዲሱ አረጋ ቂጤሳ source mereja.com

የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነት (የጉዞ ማስታወሻ)
አዲሱ አረጋ ቂጤሳ
FB_IMG_1490016477525
================================
እነሆ ወደ ቦረና እየተጓዝኩ ነዉ…
ቦረና የምሄደዉ የዴሞክራሲ መሰረት የሆነዉን አስደናቂዉን የገዳ ስርዓት ምንነት ለማወቅና ለመመርመር አይደለም፡፡ ቦረና የምሄደዉ ለጉብኝት አይደለም፡፡ የቦረና ኦሮሞን የስነ ክዋክብትና ሌሎች ሀገር በቀል ዕዉቀቶችን ለመቅሰም አይደለም፡፡
……………………………………………………………………………………………………………………
ዛሬ የቦረና ላይ ሰማዩ ጨክኗል፡፡ ዝናብ የለም፡፡ ከብቶች የሚግጡት የላቸዉም፡፡ ወተት የለም፡፡ የህጻናት ቡረቃና ፈንጠዝያ የለም፡፡ የብዙ ዕሴቶችና እዉቀቶች ባለቤት የሆነዉን የቦረናን ኦሮሞ ድርቁ ጎድቶታል፡፡ የከብቶቹ መክሳትና የመሞት ስጋት፣ የልጆቹና የቤተሰቦቹ ዕጣ ፈንታ የቦረናን አባ ወራ የኦሮሞነት ኩራቱን ፈተና ዉስጥ ከትቶታል፡፡ ጭንቀት ወጥሮታል፡፡ በነገራችን ላይ በቦረና ኦሮሞ ባህል፣ እጅ ሲያጥር፣ ድርቅ ሲከሰት በእርዳታም የተገኘ ቢሆን አባ ወራ በቅድሚያ የተገኘዉን ሁሉ ህጻናትን ይመግባል፡፡ ቀጥሎም ሴቶችን… ከተረፈ ራሱ ይመገባል፡፡ ካልተረፈ በረሃብ የመጨረሻዋን እስትንፋስ ይተነፍሳታል እንጂ ምንም ቢራብ ከህጻናት ልጆቹ እና ከሴቶች አስቀድሞ አንዲት ጉርሻ እንኳ አይጎርስም፡፡ በረሃብ የመጨረሻዋን እስትንፋስ ተንፍሶ ይሞታታል እንጂ! ይህ የቦረናነት፣ የኦሮሞነት ህግ ነዉ!!
……………………………………………………………………………………………………………………
እነሆ ወደ ቦረና እየተጓዝኩ ነዉ…
ቦረና በድርቅ ምክንያት ለድርቅ በመጋለጡ፣ የሀረር ፣ የባሌ እና የጉጂ ቆላማ ቦታዎች ለድርቅ ተጋልጠዉ ወገኖቼ ለረሃብ በማጋለጠቸዉ ቅስሜ ተሰብሯል፡፡ ወገኖቼን ድርቅ ከሚያስከትለዉ ረሃብ መታደግ ያልቻልኩ “እኔ እንደ ፖለቲካ አመራር ሚናዬ ምንድ ነዉ?” የሚል ሀሳብ እየሞገተኝ እንቅልፍ ይነሳኛል፡፡ ከዉስጤ የሚሰማኝ ድምጽ “አንተን ብሎ አመራር i፣ አንተን ብሎ ፖለቲከኛ! ኦሮሚያን የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር ዕምቅ የዉሃ ሀብት ተጠቅማችሁ ህዝቡን ከድርቅ ስጋት ማላቀቅ ያልቻላችሁ፣ ወንዝ ዉስጥ ቆማችሁ የምትጠሙ ትዉልዶች!” የሚል ስላቅ በጆሮዬ ሹክ እያለ ያስጨነቀኛል፡፡ እንቅልፍ ይነሳኛል፡፡ የተጠያቂነት መንፈስ ይጠዘጥዘኛል፡፡ በሳርና በዉሃ እጥረት የከሱ ከብቶች፣ የከሱ ህጻናት በአይነ ህሊናዬ እየመጡ ህሊናዬ ዕረፍት ያጣል፡፡ የእልህና የቁጭት ዕንባ በአይኔ ሞልቶ ይፈሳል፡፡
……………………………………………………………………………………………………………………
ወደ ቦረና እየተጓዝኩ ያለሁት ከአማራ ክልል ከመጡ ጓዶቼ ጋር ነዉ፡፡ ወደ ቦረና እየተጓዝኩ ያለሁት የአማራ ክልል ህዝብ እና መንግስትን ድጋፍ ይዘዉልን ከመጡት ከወዳጆቼ ንጉሱ ጥላሁን (የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ዋና ዳይሬክተር) አቶ አሰፋ በላይ (የአማራ ክልዊ መንግስት አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ)ጋር በመሆን ነዉ፡፡ ከኦሮሚያ ክልል አቶ መኮንን ሌንጂሶ ( የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር) አቶ ወርቁ ጫላ (የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ) አብረዉኝ አሉ፡፡
ዛሬ፣ ሰማዩ በመጨከኑ፣ የኦሮሞ ህዝብ እና የሁላችን ኢትዮጵያዉያን የኩራት ምንጭ ሆነዉን የገዳ ስርዓትን ሳይበረዝ ጠብቀዉ ያኖሩልን የቦረና ኦሮሞዎች የዕለት ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ መሆኑን በሰሙ ጊዜ የአማራ ህዝብ ወንድሞቻችን፣ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አቅም የፈቀደዉን ድጋፍ ይዘዉ ከኛ ጋር ወደ ቦረና እየተጓዙ ነዉ፡፡
ወንድም ህዝብ የሆነዉ የአማራ ህዝብ፣ የዓላማ አጋራችን የሆነዉ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኦሮሚያ ክልል ቆላማ ቦታዎች ዝናብ ባለመዝነቡ ድርቅ በመከሰቱ በሰዎች እና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የፌዴራል መንግስት እና የተራድኦ ድርጅቶች እያደረጉ ያሉትን ሰብዓዊ የድጋፍ እንቅስቃሴ ለመደገፍ የልዑካን ቡድኑ ከባህርዳር ተነስቶ የክልሉ ህዝብና መንግስት የለገሱትን ድጋፍ ለምዕራብ ጉጂ እና ለቦረና ዞን የድርቅ ተጠቂዎች ለማድረስ አብረን በጉዞ ላይ እንገኛለን፡፡
……………………………………………………………………………………………………………………
የአማራ ክልል ወንድም ህዝብ እና መንግስት ያበረከቱትን 5000 ኩንታል የድጋፍ እህል በአስራ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች አስጭነዉ፣ ለተረጂዎች፣ ለሰዎች እና ለእንስሳት ዉሃ መመላሻ ይሆኑ ዘንድ የለገሱት ሁለት የዉሃ ማመላሻ ቦቴዎች ከኛ ቀድመዉ በ9/7/09 አመሻሽ ዲላ ከተማ ደርሰዋል፡፡ እኔ እና ጓደኛዬ ንጉሱ ጥላሁን ከስራ ባልደረቦቻችን ጋር በመሆን ወደ ቦረና ለምናደርገዉ ጉዞ አዳራችንን ሻሸመኔ አድርገናል፡፡ እራት እየተመገበን ስለሁለቱ ህዝቦች ወዳጅነት እያወጋን እየተጫወትን አመሸን፡፡ የጨዋታችን ጭብጥ የሚከተለዉ ነዉ፡፡
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድርቅ ላጠቃቸዉ አካባቢዎች የአማራ ክልል ህዝብና መንግስት ከ20 በላይ የጤና ባለሙያዎችንና የዉሃ ቦቴዎችን አሰማርቶ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ንጉሱ ጥላሁን አጫዉቶኛል፡፡ የሚመሰገን ተግባር ነዉ!
የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ ትናንትም ሆነ ዛሬ የኢትዮጵያ አንድነት ምሰሶ እንደሆኑ እያነሳን አዉግተናል፡፡ በርግጥ ባለፉት ስርዓቶች የነበሩት ገዢ መደቦች የኦሮሞ እና የአማራ ወንድም ህዝቦችን ግንኙነት ለማዛባት ያልተገቡ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ ዛሬም የፖለቲካ አኪቲቪስት ነን ባዮች በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለዉን ወንድማዊ ግንኙነት ለማበላሸት ሌት ተቀን እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የሁለቱ ህዝቦች ወንድማዊ ግንኙነት ትናንትም ሆነ ዛሬ ከነበሩት ገዢ መደቦችም ሆነ ዛሬ ካሉት የፖለቲካ አክቲቪስቶች ፍላጎት በጣም የተሻገረ እና በፍቅር እና በፍጹም ወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ነዉ፡፡
……………………………………………………………………………………………………………………
ትናንት የነበሩት የገዢ መደቦች በህዝብ ስም በመነገድ ጥቅማቸዉን ለማስከበር ሲሉ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት ለማዛባት የተቻላቸዉን ጥረት ብያደርጉም አልተሳካላቸዉም፡፡ ዛሬም አንዳንድ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ አኪትቪስት ነን ባዮች ህዝቦችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲወተረተሩ ማየት የተለመደ የሰርክ ተግባር ሆኗል፡፡ ሁለቱ ህዝቦች የትናንት የገዢ መደቦች ሆነ የዛሬ ፖለቲከኛ የፖለቲካ አክቲቪስቶችን ነን ባዮች ፍላጎቶችን ወደ ጎን በመተዉ ፍቅራቸዉን አጽንተዋ፡፡ ተጋብተዉ ተዋልዳወል፡፡ አንዱ የሌላዉን ቋንቋ ይናገራል፡፡ በነገራችን ላይ በአማራ ብሄራዊ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር እና በሌሎች አካባቢዎች በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች በሰላምና በፍቅር በአብሮነት ይኖራሉ፡፡ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች (የንጉሱ ጥላሁንንቤተሰቦች ጨምሮ)
በኦሮሚያ ክልል በሰላምና በፍቅር በአብሮነት ይኖራሉ፡ ወንድሜ ንጉሱ ጥላሁን አርሲ ተወልዶ ያደገ በመሆኑ አፋን ኦሮሞን አንደኔዉ አቀላጥፎ ይናገራል፡፡ እኔም በአማርኛ ቋንቋ ክህሎት፣ ሳልስና ሳድስን ኣዛብቶ ከመጠቀም በስተቀር ብዙም አልታማም፡፡ ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ኢትዮጵያ ሀገራችን በባዕድ ሃይሎች ስትወረር ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔረር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በጋራ ዘምተዉ አኩሪ ገድል ፈጽመዋል፡፡ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በተደረጉ ዉጊያዎች ደማቸዉ ተቀላቅሎ በአንድ ላይ ፈሷል፡፡ የመስዋዕትነት አጽማቸዉ በአንድ ጉድጓድ ተቀብሯል፡፡ በከፈሉት መስዋዕትነትም ልዕልናዋ የተጠበቀ በቅኝ ያልተገዛች ኩሩ ሀገርን አስረክበዉናል፡
ወጋችን ቀጥሏል…
እራት እየተመገበን ስለሁለቱ ህዝቦች ወዳጅነት እያወጋን እየተጫወትን ነዉ፡፡
……………………………………………………………………………………………………………………
ዛሬም ቢሆን የአማራ እና የኦሮሞ ወንድማማች ህዝቦች አንዲሁም ሌሎች የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች የህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓታችን ምሶሶና ዋስትና እንደሆኑ እያስተማሩን ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት በህዝብ ፍላጎት ጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ መሆኑን እያሳዩን ነዉ፡፡ ፖለቲከኛ ፈለገ አልፈለገ፣ አፍራሽ የፖለቲካ አክቲቪስት ቀሰቀሰ አልቀሰቀሰ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የአንዱ መጠቃትና መከራ የሌላዉ መጠቃትና መከራ አንደሆነ፤የአንዱ መደሰት የሌላዉ ህዝብ መደሰት እንደሆነ በተግባር እያሳዩን ነዉ፡፡
ለዚህ ነዉ የቦረና ኦሮሞ በድርቅ መራብና መጠማት፣ የአማራዉ ህዝብ እና መንግስት መራብና መጠማት መሆኑ ተሰምቷቸዉ በዚህች ቀዉጢ ቀን ከጎናችን የቆሙት፡፡
ከዉይይታችን አንድ ጨብጥ ላይ ተግባባን፡፡ ባለፉት ስርዓቶች የነበሩት ገዢ መደቦች በሁለቱ ወንድም ህዝቦች ላይ አስከፊ ጭቆና እያደረሱም ቢሆን የሁለቱ ወንድማማቾች ህዝቦች ፍቅር እና አንድነት የገዢ መደቦችን ከፋፋይ ፍላጎት አሸንፎ ዘልቋል፡፡ ዛሬም የፖሊተካ አክቲቪስት ነን ባዮች የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነትና ፍቅር ጥላሸት ለመቀባት ቢጥሩም ህዝቡ ሳይቀበላቸዉ ቀርቷል፡፡ በመሆኑም የህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓታችን በማይናወጥ መሰረት ላይ መቆሙን፣ በህዝቦች ወንድማማችነትና አብሮ የመኖር ፍላጎት ጽኑ መሰረት ላይ መቆሙን ተግባባን፡፡ ከዚህ በኋላ ማንኛዉም ፖለቲከኛ ሆነ አክቲቪሰት ነኝ ባይ የፈለገዉን ቢመኝ፣ የፖለቲካ አክቲቪስት በፈለገዉ መንገድ ቢቀሰቀስ፣ የህብረብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓታችን በህዝቦች በፍቅር፣ በእኩልነት በወንድማማችነት እና በዴሞክራሲያዊ አንድነት ጽኑ መሰረት መቆሙ ላይ ተግባባን!!
……………………………………………………………………………………………………………………
በቀዉጢ ቀን የደገፉንን ወንድም የአማራ ወንድም ህዝብ እና መንግስትን እጅግ አድርገን እናመግናለን፡፡ መቼም ቢሆን አንረሳቸሁምም!! የችግር ቀን ባለዉለታችን ናችሁና!!
……………………………………………………………………………………………………………………
ከወንድሜ ከንጉሱ ጥላሁን አና ከባልደረቦቹ ጋር በኦሮሚያ ክልል በተለይ በቦረና ይህ ቀን አልፎ አንደገና ብንገናኝ ደስ ይለኛል፡፡ ሆኖም ንጉሱ የድጋፍ እህልና የዉሃ ማጓጓዣ ቦቴዎችን ይዞልን አንዲመጣ አልመኝም፡፡ እኔ አስጎብኚ ሆኜ የኦሮሞ ባህል የሆነዉ እና በየስምንት አመቱ ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ርክክብ የሚደረግበት፣ በዓለም ወካይ ቅርስነት የተመዘገበዉን የገዳ ስርዓትን ባስጎበኘዉ፣አሊያም የቦረና የዉሃ ኔትዎርክ ፕሮጀክት ተጠናቆ ወገኖቼ ድርቅ ከሚያስከትለዉ ስጋት ተላቀዉ ቀየአቸዉ ጥጋብና አማን ሆኖ ባስጎበኘዉ ምኞቴ ነዉ፡፡ ዛሬ በድርቁ ምክንያት ከስተዉ ሞት አፋፍ ላይ የሚገኙት የቦረና ከብቶች አገግመዉ የቦረና ከብት ዝርያ ኮርማ ብሸልመዉ ደስ ይለኛል፡፡
እንዲሁም ከወንድሜ ከንጉሱ ጥላሁን አና ከባልደረቦቹ ጋር በአማራ ክልል በሌላ ፕሮግራም ብንገናኝ ደስ ይለኛል፡፡ የአማራ ክልል ወንድም ህዝብ ከችግር ተላቆና በልጽጎ፣ ህዝቡ ከችግር የተላቀቀበትን ሚስጥር ንጉሱ ጥላሁን አስጎብኚ ሆኖ በአማርኛና አፋን ኦሮሞን በመጠቀም መግለጫ እየሰጠ ቢያስጎበኘኝ ምኞቴ ነዉ፡፡
በመጨረሻም በግሌ አንድ ነገር ተገነዘብኩ፡፡ ስርዓቶች ይመጣሉ ያልፋሉ፡፡ በመከራም ሆነ በመልካሙ ጊዜ ግን የህዝቦች ፍቅር እና ወንድማማችነት ለዘመናት ይዘልቃል፡፡
የኦሮሞ እና አማራ ህዝቦች ፍቅርና ወንድማማችነት ለዘለዓለም ይኑር!
ቸር እንሰንብት!!

No comments:

Post a Comment