Wednesday, March 8, 2017

ዓላማውን ለሳተ ድርድር ከዚህ በላይ መንፈራገጥ ትርፉ ትዝብት ነው !!! by yidinekachew kebede

ዓላማውን ለሳተ ድርድር ከዚህ በላይ መንፈራገጥ ትርፉ ትዝብት ነው !!! yidinekachew kebede
—— ” ዋንኛ ዓላማ አድርገው የተስማሙበት ፣ የህዝብን ጥያቄ የቱንም ያህል ምላሽ የማይሰጥ ከመሆኑ ባለፈ ለአገዛዙ ሥርዓት መደላድል የሚፈጥር ነው።” ——– “አገር በድርድር ነው የሚገነባው” ለመባሉ ፋይዳው ፈርጀ ብዙ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከፍተኛ የሆነ ፓለቲካ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች ። የቀውሱ መንስኤ ከበፊት ጀምሮ የመጣ ምስቅልቅሉ የወጣ የ 26 ዓመተ ፣ የከፋፍለህ ግዛ በተኛ የአገር አንድነት ፓሊሲ መሆኑ ብዙም አስረጂ አያስፈልገውም ።ይህም በመሆኑ እሱን ተከትሎ የመጣው ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እና የህወሃት/ኢህአዴግ ደካማ አስተዳደራዊ ሥርዓት ጭምር ነው። እንዲህ አይነቱ ሥርዓት ያንገፈገፈው እና በምላሹ አስተዳድርሃለው ለሚለው አካል ቁጣውን በቻለው ሃቅም ገልፆ፤ ለቁጣው ትዕግስትን ተላብሶ በአሰተዋይነት እና በንቃት የሚሆነውን ምላሽ እየተከታተለ ይገኛል። ይህን በገደምዳሜ ቢሆንም የተረዳው፣ የአገዛዙ ሥርዓት ከሚመጣበት ህዝባዊ መሃበል እራሱን ለመሸሸግ እና እድሜውን ለማራዘም ደፋ ቀና እያለ ይገኛል። ይሁን እንጂ እንደራደራለን ወይም ለመደራደር ዝግጁ ነን በማለት ከአገዛዙ ሥርዓት ጋር በእኩሉ የሚታዩት፣በድርድሩ ላይ የአገዛዙ ሥርዓት ያህል እንኳን ባይሆንም በተረዱበት ልክ ሲጨነቁበት አለማያት ( ለእነሱ የተጨነቁበት)ለመሰላቸው የመጀመሪያው ትዝብት ነው። – በመሰረቱ ከዛሬ ስድስት ወር በፊት፣ አገራችን ከገባችብት ፓለቲካዊ ቀውስ እና እሱን ተከትሎ ለተፈጠረው ችግር በዘለቄታዊነት መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው ፤ ገደብ ሳይበጅለት በአገር ውስጥ እና በውጪ ሁሉን አቀፍ ውይይትና ድርድር ሲካሄድ ብቻ ነው ! የሚል እምነት እንዳለኝ መጠነኛ አመላካች የሆነ ሃሳቤን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ገልጪ ነበር። የሚገርመው ነገር ጋዜጣው ላይ የወጣውን ጽሁፍ ሳላነበው፣ ለሁለት ወር ያህል ለእስራት ብዳርግም። ምን ይሄ ብቻ የአስቸኳይ አዋጅ ጥሰሃል ተብዬ ከቀረበብኝ መጠይቅ ውስጥ አንዱ መሆኑ እንጂ፣ ምን አልባትም ይሄ ጽሁፍ ለንባብ ከበቃ በኋል እስሩም ሆነ ሌላው ነገር መምጫው መንገድ አይታወቅም እና የሚሆነውን መጠበቅ የተሻለ ነው። ግን ይሄም ቢሆን እንደ ትላንትናው ዛሬም ለአገሬ ቀናውን በማሰብ ነውና ለራሴ ክፉ አልመኝም። ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ ፣ የአገዛዙ ሥርዓት ወዶ ሳይሆን በግዴታ ፣ በህዝባዊ ተቃውሞ አማካኝነት እዚህም እዚያ ተፍ ተፍ እያለ ይገኛል። ለዚህም በኦሮሚያ ፣ በዐማራ እንዲሁም በደቡብ አንድ አንድ አካባቢዎች የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞና አመጽ እንዲሁም እሱን ተከትሎ የተከፈለው የህይወት መሰዋዕትነት እና እስር እንዲሁም እንግልት ጭምር ነው። ይህም በታሪክ ተመዝግቦ ወደፊት የሚዘከር ነው። የአገዛዙ ሥርዓት ከፓርቲዎች ጋር ድርድር እና ውይይት አካሂዷል ማለቱን መሠረት በማድረግ፣ ዘላቂ የሆነ ችግር ፈቺ አማራጭ ሃሳባችን በሠነድ በማዘጋጀት ፣ የድርድሩ ዋና ዓላማ ፤ ብሔራዊ እርቅ በመፍጠር የፓለቲካ እና የህሊና እስረኞችን በመፍታት፣ በአገር ውስጥ እንዲሁም ከአገር ውጪ የሚገኙ የፓለቲካ ሃይሎች ጠመንጃ ያነገብ ጭምር የሚሳተፉበት ሆኖ ፤ ህዝብን የስልጣን ባለቤት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፣ ሁሉን አቀፍ ውይይት በማካሄድ ወጤት ማምጣት ከተቻለ በሚል ቀና ሃሳብ ድርድሩን እና ውይይቱን ደግፊ ነበር ። ይሁን እንጂ በድርድሩ ቅድመ ሁኔታ እና በድርድሩ ሊመለሱ የሚገባቸው ፣ ከምንም በላይ ድርድሩ ለአገራችን ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እንዲያስገኝ ከመሻት ይልቅ በተወሰኑ ፓርቲዎች ለዛውም ህዝባዊ ተቀባይነታቸው አሻሚ የሆኑ ፣ በገደምዳሜው ቢሆንም የህዝብ ድጋፍ ያላቸው በቁጥር ከሦስት የማይበልጡ ፓርቲዎች ፤ሊሻሻሉ ወይም ሊለወጡና ሊጨመሩ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎች እና የመድበለ ፓርቲ ተሳትፎ እና መጪውን የምርጫ ወቅት ዓላማ በማድረግ፤ ለመደራደር በድርድር ሥነ-ስርዓት ላይ ዋንኛ ዓላማ አድርገው መክረው መስማማታቸው፣ ተገልፆል ።ይህ ደግሞ የተለመደው የአዙሪት ገደል ውስጥ እልም ብሎ የሚያስገባ መሆኑን ለመገንዘብ ብዙም አዳጋች አይደለም ። ይህም በመሆኑ እንደራደራለን ወይም እንከራከራለን ምን አልባትም እንወያያለን ለሚሉ ከዚህ በላይ መዳከር ተጨማሪ ትዝብት ውስጥ የሚጥላቸው ካልሆነ በስተቀር ትርፉ ፖለቲካዊ ኪሣራ ነው ። – በዚህ መሰረት ዋንኛ ዓላማ አድርገው የተስማሙበት ፣የህዝብን ጥያቄ የቱንም ያህል ምላሽ የማይሰጥ ከመሆኑ ባለፈ ለአገዛዙ ሥርዓት መደላድል የሚፈጥር ነው። ሥርዓቱም ቀደም ብሎ ይህንን አምኖ በግልጽ ፤ በፓርላማ መክፈቻ ላይ ፕሬዝዳንቱ ፣ ጉድለታችን ነው ! ልናሻሽለው ይገባል ያሉትን ዋና ዓላማ በማድረግ ፣ እንደራደራለን ብለው በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት ሳይሸራረፍ እንደ ወረደ ዓላማቸው አድርገው መቀበላቸው፤ ለህወሓት/ኢህአዴግ ትልቅ ድል ነው። ከዚህ በኋል እዳው ገብስ ነው። ምክንያቱም ለአገዛዙ ምቹ የሆነ የድርድር ዓላማ ተቀምጧል ። መቼም ቢሆን በይትም ቦታ፣ ዋና ዓላማን ያልሳተ ንዑስ ዓላማ እና ይሄን መሰረት ያደረገ የመወያያ አጀንዳ መኖሩ ሣይንሳዊ እውነት ነው። ይህ እውነታ የድርድሩን ዋና ዓላማ ፈጽሞ የሚቀይረው አይደለም። ከረፈደም ቢሆን ይሄን ለማወቅ የሞከሩ አንዳንዶቹ፣ በድርድሩ አጀንዳ ላይ በዋና ዓላማ ላይ ያላስቀመጥናቸውን ሃሳቦች አንስተን እንደራደራለን ይላሉ፣ ይሄ ደግሞ የፖለቲካ ጥበብ ወይም የድርድር መሠረታዊ መርሆዎች ላይ የሚኖራቸው ግንዛቤ ብልጥጥ አድርጎ ለህዝብ አጋልጦ የሚሰጥ ተጨማሪ ትዝብ ነው። – ምን ይሄ ብቻ ! የድርድሩ ዓላማ አጥጋቢ ውጤት ለሌለው ነገር። ስንደራደር ማን ይታዘበን ፣ እነማንስ መሀል ሆነው ያደራድሩን ፤ በሚል ጠንካራ ክርክር እንደሚደረግ ተደራዳሪዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እየገለፁ ይገኛሉ። እዚህ ላይ እኔን ያስቀኛል! እንዳሁም የህወሓት/የኢህአዴግ ብልጠት የተሞላባት ጨዋታ የተጫወተው እዚህ ላይ ነው። ገዠው መንግሥት የሚፈልገውን የድርድሩ ዋና አላማ ቀድሞ ማኖ ካስነካ በኋላ፤ አደራዳሪ እና ታዛቢ ቀጥሎ እንዲሆን አስደረገ፣ እሱ በሚመቸው ነገር ላይ ማንስ ቢመጣ ምን ቸገረው። በድርድሩ ከተቃዋሚ በላይ መንግሥት እየሰራ ነው መባሉ ለምን ሆነና ?! ይህም በመሆኑ ተቃዋሚዎች የሚጠቁማቸውን ታዛቢ እና አደራዳሪ ለህዝብ ግንኙነት ሥራ እንዲረዳ የውሸት መንገጫገጭ ያሳያል ፣ ምን አልባት ሙሉ ለሙሉ ወይም ከ 75 በፐርሰንት በላይ ሊቀበል ይችላል። በዚህን ጊዜ ተቀዋሚዎች የድል ከበሮ ይደልቁ ይሆናል። ነገር ግን ለአገራቸው ቀናውን በማሰብ ፣ በአደራዳሪነት ውይም በታዛቢነት ለማገልገል ፍላጎት ያላቸው ይኖሩ ይሆናል። ግን የዚህን ጉድ በዚህ ደራጃ መሆኑ ሲገባቸው ፣ ቀኝ ወደ-ኋላ ማለታቸው አይቀሬ ነው። ይሄም ሌላኛው ትዝብት ነው። – ይዚህ ጽሁፍ አንባቢያን ፣ ከላይ የገለፅኩት በአብዛኛው ፣ በዚህ ድርድር ላይ ፍላጎት ላላቸው ገና ከጅምሩ ፣ይሄን ሃሳቤን ለማጋራት በቻልኩት አቅም ሁሉ ሞክሪያለው። ይታይ የነበረ ስእተት ወቅቱን ጠብቆ በገባኝ መጠን እርማት እንዲደረግበት ጥረት አድርጊያለው ። ከዛሬ ነገ የሚሻል ነገር ካለ ብዬ ለመታገሥ ለራሴ እድል ሰጥቻለው። ይሁን እንጂ በእኛ ሰፈር የአራዳ ቋንቋ ( ወፍ የለም)። ስለዚህም ዓላማውን ለሳተ ድርድር ከዚህ በላይ መንፈራገጥ ትርፉ ትዝብት ነው !!! በማላት የዚህ ጽሁፍ ማብቂያ ይሄ ይሁን፣ ለሌላው ደግሞ በሌላ ቀን ። አንባቢያን ከአክብሮት ጋር የምጠይቀው ይህ የግል ሃሳቤ እንጂ የይትኛው ፓርቲ አቋም የሚመለከት አይደለም።(ይድነቃቸው ከበደ) – ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!!

No comments:

Post a Comment