Thursday, December 1, 2016

በታሪክ ዓላማውን ሳያውቅ ታግሎ ያሸነፈ ድርጅትም ግለሰብም የለም! – Muluken Tesfaw



በታሪክ ዓላማውን ሳያውቅ ታግሎ ያሸነፈ ድርጅትም ግለሰብም የለም!Muluken Tesfaw
የዐማራ ወጣቶች በወያኔ ፋሽስታዊ ሥርዓት በሰላም እንዲኖሩ ባለመፈቀዱ ምክንያት ለነጻነት ሕይወታቸውን እየገበሩ ይገኛል፤ በደማቸው ሊያኖሩን ለሚተጉ የእኛ ወንድሞች በዕውነት ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ለነጻነት የምናደርገው መንገድ ፈታኝ ቢሆንም በድል እንደምንወጣው ምንም ጥርጥር የለንም፡፡ የምታደርጉት ፍልሚያ የዓለም ሕዝብ በሚገባ እያወቀው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ይህን ሊያደርግ የሚችል መገናኛ ብዙሃንም ገና አልመሠረትንም፤ ለዚህም እንታገላለን፡፡
ወደ ጽሑፌ ዋናው ዓላማ ልግባ፡፡ የዐማራ ወጣቶች በኢትዮጵያ ውስጥ የሥርዓት ለውጥ እናመጣለን ብለው ለሚታገሉ ድርጅቶች ሁሉ የዐማራን ሕዝብ በተመለከተ ያላቸውን አቋም በግልጽ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የምንሰዋበት ዓላማ ግልጽ ነው፡፡ እነ ንግሥት ይርጋ፣ ቀለብ ስዩም፣ አዲሱ ሰረበ፣ ኮ/ል ደመቀ፣ ጄ/ል ተፈራና እልፍ ዐማሮች የታሠሩበትን ዓላማ መዘንጋት የለብንም፡፡ ሁልጊዜም አንድን ድርጅት ስንደግፍ ወይም ስንቃወም፤
1. የወልቃይት ጠገዴ፣ የራያ አላማጣ፣ የመተከል ብሎም አጠቃላይ የዐማራውን ሕዝብ ጉዳይ በድርጅታችሁ የሰጣችሁት ቦታ ምንድን ነው? ነው ወይስ ወልቃይት የትስ ብትሆን ነው የምትሉን እንደ አረናዎችና ዴሕምት?
2. ምን ዓይነት ፌደራሊዝም ትከተላላችሁ? በቋንቋ ወይስ በጂኦግራፊ መቀራረብ? በቋንቋ ከሆነ አሁን ያለው የዐማራ ሕዝብ ሳይወከልበት የጸደቀው ፌደራሊዝም ይጸናል?
3. ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌደራሊዝም ከሆነ በመጀመሪያው የሕዝብ ቆጠራ ወቅት አብዛኛው ዐማራ የሆነባቸው ግን ደግሞ ከዐማራ ክልል ውጭ የተካለሉ አካባቢዎችን ምን ታደርጓዋላችሁ?
4. ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በዐማራው ላይ የደረሰውን የዘር ማጽዳትና ማጥፋት ወንጀል እውቅና ትሰጣላችሁ? በዚህ ላይ ያላችሁ አቋም ምንድን ነው? በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባሉ የዐማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን በደል በተመለከተ ይህን ለማስቀረት ምን እየሠራችሁ ነው?
በትንሹ ለእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባችሁ፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የማይሰጥ ድርጅት በዐማራን ሕዝብ ሕይወት እየቆመረ እንጅ እየታገለ አይደለም፡፡ የዐማራ ሕዝብ ጥያቄ ግልጽ ነው፡፡ ወደ ኋላ ወደፊት የለም፡፡
ዓላማውን ሳያውቅ ታግሎ ያሸነፈ ድርጅትም ግለሰብም የለም፡፡ ከላይ የቀረቡት ጥያቄዎች የዐማራ ሕዝብ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የዐማራ ሕዝብ ተገቢውን ምላሽ የሚፈልግላቸው ናቸው፡፡ ማንም አሊ ሊል አይችልም፡፡ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ አታላይ ዛፌ፣ ጌታቸው አደመ፣ አዲሱ ሰረበ፣ ንግስት ይርጋ….. ለምን ታሠሩ? በጎጃምና በጎንደር በሁለት ወራት ብቻ ከ300 በላይ ዐማሮች ለምን ተጨፈጨፉ? እነ ሞላ አጃው፣ ቃቁ .. ለምን ተሰው? እነ ጎቤ ለምን በርሃ ገቡ? 20 ሺህ ዐማሮች ለምን በብር ሸለቆና በተለያዩ እስር ቤቶች ታጎሩ?
መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች መፍትሔ ፈልገው ነው፤ ለጥያቄዎቻችን መልስ እነርሱ ተሰው፡፡ በእርሱ ደም መጨዎት ታሪክ ይቅር የማይለው ክሕደት ነው፡፡ አፈ ጮሌዎች ትግላችሁን በሌላ ዓላማቸው ሊያዳፍኑት ይሞክሩ ይሆናል፤ ግን እመኑኝ እናሸንፋለን!!

No comments:

Post a Comment