Monday, December 19, 2016

ሕወሓት በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ ላይ አስከ ሞት የሚያስቀጣ ክስ መሰረተባቸው።ቆንጅት ስጦታው



ሕወሓት በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ ላይ አስከ ሞት የሚያስቀጣ ክስ መሰረተባቸው።
–  ከ202 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ንብረቶች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል ተብሏል
Reporter  የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በሚባል ሽፋን በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ መሪነት በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጎንደር በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች፣ ታኅሳስ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የመሠረተባቸው የሰሜን ጎንደር ከተማ ነዋሪዎች አቶ መብራህቱ ጌታሁን፣ ጌታቸው አደመ፣ አታላይ ዛፌና አለነ ሻማ ናቸው፡፡ ከትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን የሰቲት ሁመራ ነዋሪ አቶ ነጋ ባንተይሁንም በክሱ ተካተዋል፡፡
ተከሳሾቹ የአርበኞች ግንቦት ሰባትን የሽብር ተልዕኮ ለማስፈጸም ‹‹የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ›› በማለት ራሳቸውን አባልና አመራር ብለው ከሰየሙ በኋላ፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን የፕሮፓጋንዳ ኃላፊ አድርገው መሾማቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳብራራው ተከሳሾቹ የማንነት ጥያቄውን ሽፋን በማድረግ፣ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ጋር በተለያዩ ተንቀሳቃሽ ስልኮች በቀጥታ ተገናኝተዋል፡፡ በትግራይ ክልላዊ መንግሥትና በወልቃይት አስተዳደሮች ላይ የግድያና የአፈና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ለወጣቶች የጦር መሣሪያ አስታጥቀዋል፡፡ የታጠቁት ወጣቶች በዳንሻ ከተማ ግለሰቦችን እንዲገድሉ፣ አፍነው እንዲወስዱና በቃፍታ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ፣ የዳንሻና ሶሮቃ መንገድ እንዲዘጋ ማድረጋቸውን ክሱ ይዘረዝራል፡፡
በክልሉ በሰሜን ጎንደር ዙሪያ በፀገዴ ወረዳዎች በደባርቅ፣ እንጂባራ፣ ወረታ፣ ደምቢያ፣ መገራ፣ በምዕራብ አርማጭሆ በመተማ ዮሐንስና ዙሪያው ተከሳሾቹ ከመጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ባስነሱት አመፅ በመንግሥትና ሕዝብ ተቋማት፣ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ ድርጅቶችና ተሽከርካሪዎች ላይ ከ95.9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ማድረሳቸውን በክሱ ተጠቅሷል፡፡ በጎንደር ከተማ በሚገኙ ቀበሌዎችም በመንግሥትና በሕዝብ ተቋማትና በተሽከርካሪዎች ላይ ከ10.6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡
ከነሐሴ 18 ቀን እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ በምዕራብ ጎጃም በሚገኙ በባህር ዳር ዙሪያ መርዓዊ ከተማ፣ በሜጫ ወረዳ፣ በቡሬ፣ በደጋ ዳሞት አዴት ከተማ፣ በፍኖተ ሰላምና ባህር ዳር ከተማ ከ95.3 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንና በድምሩ ከ202 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡
ተከሳሾቹና ኮሎኔል ደመቀ ሰብሳቢ በመሆን ሰኔ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ውስጥ በሚገኝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ግለሰቦችን በመሰብሰብ፣ ‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም፡፡ የወልቃይት ፀገዴ የማንነት ጥያቄውን ምክር ቤቱ ወርዶ ሊያየው የሚችለው ደም ሲፈስና ግጭት ሲከሰት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ተወክላችሁ የተገኛችሁ በሙሉ ወደ መጣችሁበት ቦታ በመሄድ፣ አመፅ በመፍጠርና መንገዶችን በመዝጋት የሽብር ተግባር መፈጸም አለባችሁ፡፡ ይህንን ስታደርጉ ከእናንተም ሆነ ከመንግሥት አካላት ሰው ሊሞት ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለወልቃይት ሕዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄያችንን ይፈታልናል፤›› በማለት ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
በወረቀትና በብዕር የሚመጣ ፍትሕ እንደሌለና በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ አመፅ እንዲነሳ የሚያደርጉና የሚያስተባብሩ ሰዎችን በመምረጥና በመመልመል፣ የሽብር ተግባሩን እንዲያፋፍሙ ተልዕኮ መስጠታቸውንም ክሱ ይገልጻል፡፡
ተከሳሾቹ በተለያዩ አካባቢዎች ለመለመሏቸው ወጣቶች ገንዘብ በመላክ ከአዲ ረመጽ አካባቢ ጥይት ገዝተው እንዲዘጋጁ ማድረጋቸውን፣ ወጣቶችን እያፈኑ መውሰዳቸውን፣ በተለያዩ ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውንና የግድያ ሙከራ ማድረጋቸውንም ክሱ ያብራራል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የማንነት ጥያቄውን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ በውጭ አገር ከሚገኙት ስረበ ጥሩነህ፣ መዓዛው ጌጡና አስማረ ከተባሉት የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች ጋር በስልክ ግንኙነት በማድረግ የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኙ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል፡፡
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጣቂዎች በኤርትራ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በማድረግ፣ የጦር መሣሪያ እንዲገዙና በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ፀገዴ ወረዳዎች በተለያዩ አካባቢዎች መንገድ በመዝጋት እንዲፈጸም ትዕዛዝ መስጠታቸውን ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቹ ክሱን በንባብ አሰምቷቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ የተገለጸውን የሽብር ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀእናለን)፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001ን ተላልፈው በመሆኑ፣ የሽብርተኝነት ክስ እንደተመሠረተባቸው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ የተጠቀሱባቸው የሕግ አንቀጾች ዋስትና ስለሚከለክሉ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የቅድመ ክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡና ከጠበቃ ጋር ተመካክረው ታኅሳስ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment