Wednesday, December 28, 2016

በአገሪቱ ለሚታየው ፖለቲካዊ ቀውስና ህዝባዊ እምቢተኝነት ዛሬም የፕሮፖጋንዳ መፍትሄ ?ቆንጅት ስጦታው



በአገሪቱ ለሚታየው ፖለቲካዊ ቀውስና ህዝባዊ እምቢተኝነት ዛሬም የፕሮፖጋንዳ መፍትሄ ?
የህወኃት/ኢህአዴግ የ25 ዓመታት ጭቆና የወለደው ብሶት በአገራችን አራቱም አቅጣጫዎች ከህዝብ የወጣ በህዝብ የተከወነና የተመራ የህዝባዊ እምቢተኝነት ተቃውሞ እንቅስቃሴ ለኣመታት መደረጉ አይካድም ፡፡ ከህገመንግስት ዝግጅት አንስቶ ከጅምሩ ህዝብ ያሰማውን ተቃውሞና የመገለል ስሜት አቆይተን ከምርጫ 2002 ወዲህ የተከሰሰቱትን የቅርቦቹን በጥቅል ብንመለከት እንኳ–
1. የሙስሊም የእምነት መብት መከበር ጥያቄና ለዓመታት የዘለቀ ጠጠር ያልተወረወረበት ሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴ፤
2. በኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የመሬት ወረራና የነባር ባለይዞታ ገበሬዎችን የማፈናቀል ተቃውሞ፤
3. የደቡብ ኦሞ የሃመር ወጣቶች ዓመታት ያስቆጠረው የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥያቄ፤
4. የኦሮሚያ ከላይ የህዝብ ተቃውሞ እንደገና ማገርሸትና የህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ያለመገታት ፣
5. የቁጫ፣ የኮንሶና የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የማንነትና አከላለል ጥያቄ ፣….. እናገኛለን ፡፡
ለእነዚህ ሰላማዊና ህገመንግስታዊ የመብት ጥያቄዎችና የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች መንግስት ምን እና እንዴት ምላሽ ሰጠ ? በውጤቱስ ምን ተከተለ ? ችግሩ ተፈታ ወይስ ችግሩን ‹ለሚያዳፍን › ለአስቸኳይ አዋጅ ዳረገን ? …እያልን በርካታ ጥያቄዎች ማዥጎድጎድ ይቻላል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎችና ህዝባዊ ተቃውሞዎች ዘላቂና አካታች መፍትሄ በሚፈልጉበት ወቅት ላይ የመገናኘታችን እውነት የጋራ ሥምምነት የተደረሰበት ቢመስልም በመፍትሄው ላይ ግን ለዋናው የችግሮች ምንጭና መንስኤ /ህወኃት/ኢህአዴግ/ ሽፋን/ከለላ ለመስጠት ‹ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ › እንዲሉ በተቃዋሚዎች የውስጥ ችግሮችና ድክመቶች ላይ ‹ትኩረት › ማድረግ ተይዟል፡፡ ለዚህም እንዲህ እንጠይቃለን፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመት፣ የውስጠ- ዲሞክራሲ ፣የአቅም ፣አደረጃጀት፣ … ውስንነትና ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው-
1. በተቃዋሚ ፓርቲዎች ‹‹ ሰርጎ በመግባት፣ በህግ/አዋጅ በማፈን ፣ በእስራት፣ ማስፈራራትና ግድያ ፣….. ዕድገታቸውን ያቀጨጨው ፣ እንቅስቃሴኣቸውን የቀየደው ማነው?
2. የዲሞክራሲ ተቋማት ለዲሞክራሲ ሥርዓት ያላቸውን አበርክቶ በአዋጅ የገደለው፣… የዲሞክራሲ ዕድገት ሂደት ነው እያለ ‹ የዲሞክራሲ አቀንጭራ › የሆነው ማነው ? የህዝብ መገናኛ ብዙሃንን በቁጥጥሩ ሥር አውሎ፣ መያዶችንና ነጻውን ፕሬስ በአዋጅ ቀይዶ የኃሳብ ልዩነቶችን ፣ፍጭቶችን ያፈነው ማነው?
3. ከውይይትና የኃሳብ ፍጭት ይልቅ ‹‹ ከፈለጋችሁ ‹መንገዱን ጨርቅ › ያርግላችሁ›› እያለ ጦርነት ሲጣራ የኖረው ማነው? የውይይትና ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ ጥሪ ሲቀርብለት ‹ማን ከማን ተጣላ› በማለት ሲያሾፍ የከረመው ማን ነው ?
4. በህገ መንግስት የተደነገጉ የዲሞክራሲ ተቋማትን /ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን ፣ እንባ ጠባቂ ፣ ጸረ-ሙስና …/ የራሱ ንብረት አድርጎ የህዝብ አሜነታ ያሳጣው ማነው?
5. ‹የመንግስት ሥልጣን ከኢኮኖሚ የበላይነት አይነጣጠልም› በሚል ፖሊሲ እየተመራ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የማይቻል ያደረገውና በኢኮኖሚ ልማት አውታሮች ላይ ጥፋት የጋበዘው ማነው ?
6. ፖለቲካ ማጭበርበር ፣ማታለል፣ በቃል አለመገኘት ፣ክህደትና ውሸት … እንደሆነ በተደጋጋሚ የገባውን ቃል እያጠፈ፣ በአደባባይ ህዝብን እየዋሸ ፣ የማይተገበር ዕቅድ እየነደፈ ( ባድሜ……፣ከሰማይ በታች ….. ተሃድሶ… ጥልቅ ተሃድሶ…) ለህዝብ ያስተማረው ማነው ?… ህዝብን በምርጫ ፖለቲካ ተስፋ ያስቆረጠው ማነው?
7. የወጣቱን ችግር እፈታለሁ እያለ…ነገር ግን እየሰደበ ያለው ማነው ? ለመሆኑ በድንገት ተነስቶ 10 ቢሊዮን ብር መደብኩ ያለው መንግስት በኦሮሚያ ብቻ ሥራ ይፈጠርለታል ለተባለው (ኢቢሲ/ኢቲቪ ታህሳስ 13/09 ዓም) 4.3 ሚሊየን ወጣት ብቻ ቢውል ለአንድ ወጣት የሚደርሰው 2 325 ብር መሆኑን ስናስብ ማታለል/ የህዝብ ንቀት ባለቤት ማነው ?
8. ህገመንግስቱን እየረገጠ፣ እየሸራረፈና እየደፈጠጠ ያለውና ህገመንግስታዊነትን ‹የተስፋ ዳቦ› አድርጎ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያበቃን፣ ጥላቻንና አድሎኣዊነትን በመዝራት ለዘረኝነትና ጠባብነት በሩን የከፈተው ማነው ? ሲጠቃለል፡- የሁሉም መልስ ህወኃት/ኢህአዴግ ህገመንግስቱን በመጨፍለቅ የፈጸመው ነው፡፡ ይህ በሆነበት፡-
በአገራችን ለሚታየው ፖለቲካዊ ቀውስ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ድክመቶችና ችግሮች በሽፋንነት ሣያነሱ፣ህገመንግስቱን አክብሩ ሳይሉ ገዢው ፓርቲ/መንግስት በብቻውና በራሱ የፈጸማቸውን ስህተቶችና በዲሞክራሲ ሂደት ላይ ያበጃቸውን ጋሬጣዎች በማንሳትና እነዚህን በማስተካከል ብቻ ሊገኝ የሚችለውን ለውጥ ማሳየት አይቻልምን? እንዲያው የተቃዋሚዎች ድክመት ህዝብ ለሚጠብቀው ዘላቂ መፍትሄ ያላቸውን ብቃት፣ ዝግጅትና ቁርጠኝነት እንዲሁም የጠራ ሃሳብና የአቋምና የፖለቲካ መፍትሄ ወጥነት አጠያያቂ ያደርግ ከሆነ እንጂ እስካሁን በአገራችን ለታዩት ችግሮች እንደምን በምክንያትነት መቅረብ እንደሚችልና ለዘላቂ መፍትሄው ያለውን ፋይዳ በግልጽ ብንወያይበት መልካም ነው፡፡
በ1986 በግዮን ኮንፍረንስ ያነሳውንና እስከዛሬ የቀጠለውን የሠላምና ዕርቅ ተቀራርቦ የመነጋገር አጀንዳ እንደአዲስ ግኝት አንስቶ ባለቤቱን የተቃውሞ ጎራ ህገመንግስት እንዲያከብር መወትወት ወደ መፍትሄው ያደርሰናል? እንነጋገርበት፡፡

No comments:

Post a Comment