Friday, December 2, 2016

አዎን ፈሪዎች ነን፤ ግርማ በቀለ ወ/ዮኃንስ



አዎን ፈሪዎች ነን፤ ግርማ በቀለ ወ/ዮኃንስ
ፈሪዎች ስለሆንን ከአገርና ከወገን መለየትን አንደፍርም፤
ፈሪዎች ስለሆንን ከአገርና ከወገን መለየትን አንደፍርም፤
ፈሪዎች ስለሆንን ከስደት ይልቅ ማሰቃያና ማጎሪያ  ቤቶችን፣ሲያልፍም የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል  እንደፍራለን፤
ፈሪዎች ስለሆንን ውርደትና ጭቆናን ለመሸከም ድፍረት የለንም፤
ፈሪዎች ስለሆንን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን ለመሸከም አቅም አጥተናል፤ …….
በመሆኑም ፡-
ለህዝባችን ጭቆና አይመጥነውም ብለን ስለምናምን  ኑሮኣችንም ሞታችንም በአገራችን ከህዝባችን ጋር ይሆን ዘንድ መርጠናል፡፡ ዋጋው ጠፍቶን አይደለም፡፡ ሰላማዊ ዜጎች መብታቸውንና ክብራቸውን በመጠየቃቸው፣ አገሬን በማለታቸው የደረሰባቸውን ሳናውቅና ስላልደረሰብን አይደለም፤ የተገደሉትን፣ አካላቸው የጎደለውን፣ የተሰደዱትን የአገርና ወገን ብርቅዬ ልጆችና ለሌላውም የሚተርፉ ምሁራን ፣ በእስር ቤት የሚሰቃዩትን፣ … ከርቀት ሳይሆን ከድርጅታችን ጭምር  በቅርብ እናውቃለን፡፡ ይህን እየጻፍኩ ባለሁበት የድርጅታችን የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት/ኦህዲኅ/ ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ሰብሳቢና ጽ/ቤት ተጠሪ መምህር ዓለማዬሁ መኮንን ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የዞን ሥራ አስፈጻሚ አባላችን ወጣት ዳዊት ታመነ ፣የዞን ምክትል ሰብሳቢ መምህር ኢንድሪስ መናን ፣ የዞኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላችን ወጣት መሃመድ ጀማል  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥም በእስር ቤት ናቸው፡፡ ከዞኑ ሥራ አስፈጻሚዎች የቀሩት ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ ወጣት ዳዊት ታመነ አምና አቶ ዓለማዬሁና ሌላው የዞን ሥራ አስፈጻሚ አባላችን አቶ አብረሃም ብዙነህ፣እንዲሁም ወዳጃችን አቶ ስለሺ ጌታቸው በፀረ- ሽብር ህጉ ከጂንካ ከ500 ኪ/ሜትር በላይ ርቀት ተወስደው አዋሳ በታሰሩ ጊዜ እስከሚፈቱ ተመላልሶ ይጠይቅና ጉዳያቸውን ይከታተል የነበረ ቆራጥ ታጋይ ነው፡፡ድርጅታችንና  ዳዊት በየትም የሚደረግ  ሰላማዊ ትግል አጋር ናቸው፡፡ ዳዊት አሁን የታሰረው  የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነውን የጎጃሙን  ሰማዕት የ ‹‹ሣሙኤል አወቀ›› የዝክር ቲ-ሸርት ከቤቱ መገኘቱ ከ‹ወንጀል› ተቆጥሮበት  ነው፡፡  አዎን ዛሬም ነገም በየትም የአገራችን ክፍል የሚደረገው የነጻነት፣ የመብት ህዝባዊ ትግል አጋር ነን፡፡ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ሰላማዊ ትግል፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ ክልል፣ በኮንሶ ህዝብ … የተደረጉት ህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች አጋርነታችን በአደባባይ ገልጸናል፡፡አማራ በራሱ ተወካይና አስተዳዳሪ ሲሰደብ እስከ ባህርዳር ተጉዘን አውግዘናል፡፡
እስራትን እኛም ታስረን- ለዚያውም ከመኖሪያችንና ከሥራችን ቦታ በ750 ኪ/ሜትር ርቀት፣ ለዓመት ያህል ታስረን አይተነዋል፡፡ እስራትን አንድ ጊዜ ሳይሆን ደጋግመን አጣጥመነዋል፡፡ ለብቻችን ሳይሆን ባለቤታችንና ወዳጆቻችን ጋርም እስራትን ቀምሰናል፤ ሩቅ ሳይሆን ካቻምና፡፡  በዚህ ሁሉ ውስጥ  እየወደቅን እየተነሳን ላለፉት 25 ዓመታት በሰላማዊ ትግል  የገፋነው፣ዛሬም  ‹‹ሣይቃጠል በቅጠል ›› እያልን የምንጮሄው  መከፈል ያለበትን ለመክፈል ስለወሰንን ፤ ስለሁላችን መብት፣ክብርና ጥቅም፣ ‹የአገራችን ታላቅነት› መመለስ  ነው፡፡
ሰላማዊ ትግል የሚጠይቀንን መክፈል የወሰነው ደግሞ የትግሉም የለውጡም ቀዳሚና ዋነኛ (ብቸኛ አይደለም)  ባለቤት አገር ቤት ያለው  ህዝብ በመሆኑና ፣ለዘላቂ መፍትሄው ለውጡ በሠላማዊና ሠላማዊ  መንገድ ብቻ መሆን አለበት በሚለው ላይ የጸና አቋም ስላለን ነው፡፡ ከተለመደው  በኃይል የሚደረግ  የአሸናፊዎች የሥልጣን  ሽግግር በዘላቂ ሰላማዊ ሁላችን አሸናፊ የሚያደርግ የሥርዓት ለውጥ  መሆን አለበት በሚለው ላይ ግልጽና የማይናወጥ ጠንካራ እምነት ስላለን ነው፡፡ ለዚህም ነው ለዘላቂ መፍትሄ  በአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችን ሁሉ አካታች የሽግግር መንግስት በማለት ደጋግመን የምንጮሄው ፣ ለተግባራዊነቱ ያለማሰለስ የምንታገለው – ስለሁላችንና አገራችን ስንል ፡፡
ግን ፣
የምንፈራው ዘረኝነት ነግሶ – መከባበር፣ መተማመንና የወንድማማችነት መንፈስ ረክሶ፣ የወንድም ደም በወንድሙ ፈሶ….የትናንት አብሮነታችን ተዘንግቶ፣ የጋራ ተጋድሎኣችንና የሁላችን ድሎች ተረስተው ብቻ ሣይሆን ለ‹‹ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ›› ማዳበሪያ፣ ‹ምርጥ ዘር› እና  የመስኖ ውሃ ሆኖ እንዲያገለግል የተሸረበብን ሴራ ስር እንዳይሰድ እንጂ በአገራችን ፣በህዝባችን መሃል ሆነን ይህ ሴራ እውን እንዳይሆን ለመቀልበስ በሚደረገው ሰላማዊ ትግል የሚጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል አይደለም ፡፡የፈራነው የክብራችንን መደፈር እንጂ ማስከበርን አይደለም፣ ለዚህማ ዋጋ እየከፈልን አስርተ ዓመታትን አስቆጥረናል፡፡
ነጻነታችንን ማስነጠቅን ክብራችንን ማስደፈርን ፈራን እንጂ በአገራችን በጭቆና ውስጥም ቢሆን ስለክብራችንና ነጻነታችን መጠየቅን አይደለም የፈራነው፡፡ የፈራነው እነርሱ ገዢዎችና ጨቋኞች እንድንፈራ የፈለጉትን- ነጻነታችንን መጠየቅ፣ ክብርና መብታችንን ማስከበር ሳይሆን  በተቃራኒው እንዳንደፍር የፈለጉትን ያለፍርሃት ተጋፈጥን ፤ በፍላጎታቸው ቦይ አልፈሰስንም፤ አንፈስም፡፡ አዎን በኦሮሚያ ‹‹ የአማራው ደም ደሜ ነው›› ፣በአማራ ‹‹የኦሮሞው ደም ደሜ ነው›› የሚል መፈክር መስማት፣ ኢትዮጵያዊያን በሚገኙበት የዓለም መዳረሻ በሙሉ የአማራው፣ የኦሮሞው ፣ የኮንሶው ፣ የጋምቤላው፣ የሱማሌው፣ .. ጉዳይ ጉዳዬ ነው የሚል የጋራ ድምጽ በአንድነት ሲሰማ ፍርሃታችን ይገፈፋል፣በተቃራኒው እነርሱ የዘረኝነት ድልድያቸው በመሰበሩ  ፣ የመከፋፈል መርዛቸው በመርከሱ  ፍርሃት ያርዳቸዋል፡፡ በቅድሚያ የተከተልነው አቅጣጫ ትክክለኛ፣ የተያዝነው ትግል ሰላማዊና የዘላቂ መፍትሄ አዋላጅ፣ ዓላማችን የሁላችን በሁላችን የምትገነባ የዜጎች እኩልነትና መብት፣ ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት የተከበረባት ፣የሁላችን  ፍትሃዊ ጥቅምና ፍላጎታችን የምናረካባት በልማትና ታሪክ የቀደመች፣ ስመጥር ሉዓላዊት አዲስቱን ኢትዮጵያ መመስረት ነውና የምንፈራው እነዚህን እንዳንጠይቅ ለእነዚህ እንዳንታገል ቀፍድዶ የሚያስረውን መከፋፈልና አንድነት ማጣት  እንጂ ስለነዚህ የሚከፈለው ዋጋ አይደለም፡፡ የምንፈራው ከሰው በታች የሚያውለንን ጭቆና አሽቀንጥሮ ለመጣል ከሚደረገው ትግል የሚያግተን  ለአብሮነታችንና ለተባበረ ትግላችን እንቅፋት የሚሆኑ ሁኔታዎችን ነው፡፡
የስደት መንገድ ባይጠፋንና ፤ ገና በወጣትነታችን- በላጤነታችን ከዓመት እስራት ከወጣን  በኋላ  አውሮፓና አሜሪካ ብንሄድም፤
ከዚያ በኋላም በተለያዩ  የሥራ አጋጣሚዎች ደጋግመን ከአገር ወጥተን ብናውቅም ፤……ስደትን በእጅጉ እንፈራለን፡፡
ብርቅየዋ የአገር ልጅ ዓለም ጸሃይ ወዳጆ በግጥሟ እንደገለጸቺው ስደት መነቀልና ባዶነት ነው፤ የፈለግነው ቁሳዊ ፍላጎት ሁሉ ቢሟላ ያለመርካት፣ ምግብ በሞላበት መራብ፣ የሚጠጣው በሞላበት መጠማት… ፣ሁሌ  ‹‹ ማን እንደሃገር ፣ማን እንደ ወገን›› እያሉ በትዝታ መቆዘም፣ ከአገርና ወገን ናፍቆትና ሰቀቀን የጸዳ የተሟላ ሥነልቡናዊ መደላደል ማጣት፡፡ ስደት ክብርን ይነጥቃል፣ ለውርደት ይዳርጋል፡፡ ‹‹ ከአገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ- ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ ›› እንዲል የአገሬ ሰው፡፡ ይህ አገሩን ይዞ ይዞራል ለሚባለው ኢትዮጵያዊ ምቾትን ሙሉ አያደርግም ሳይሆን ምቾት ይነሳል፡፡ ይህም በአገር ከህዝባችን ጋር አብረን ኖረን፣ አብረን ለመሞት ያለንን  የጸና አቋማችን  የሚያጠናክር ነው፡፡ ይህን ደግሞ ዕድሜ ለመረጃ ቴክኖሎጂ ዘመን- ዓለም መንደር ሆናለችና ሄደን ‹በባዶነት› ተሰቃይተን ማረጋገጥ የለብንም፡፡ በተለያየ ምክንያት በተለይም ያለንበት የመረረ ጭቆናን በአገራቸውና ህዝባቸው መሃል ሆነው ማየትና መቋቋም ፣… ያልቻሉ (የጭቆናው  ቀንበር ለኅሊናቸው ሸክም አቅም በላይ የሆነባቸው)፣ በአገራቸው እንዳይኖሩ በወጡበት እንዲቀሩ የተገፉ፣  በአገራቸው ጥረው ግረው የመኖር ዕድል ያጡ፣ የዕድሉ በር የተዘጋባቸውና ተስፋቸው የተሟጠጠ፣ የኑሮውን ጫና መሸከም ያልቻሉ ግን ከእኛ በማያንስ ሁኔታ ስለአገራቸውና ወገናቸው የሚንገበገቡ ስደተኛ ወገኖቻችን የሚያከፍሉን የስደት ኑሮ ተሞክሮና መረጃ ከበቂ በላይ ነው፤ ትግሉንና መስዋዕትነትን ሳይሆን ስደትን የሚያስፈራ ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል አርበኛው እስክንድር ነጋ አስተምህሮም ይሄው ነው፡፡ ስለሆነም ስደተኛ ወገኖቻችን በአገራችን ከህዝባችን ጋር አብረን ኖረን፣ አብረን ለመሞት አደፋፈሩን እንጂ አላስፈራሩንም፡፡ የስደትን ክብደት አስተማሩን እንጂ ለቁሳዊ ፍላጎት እንድንገዛ አልቀሰቀሱንም ፡፡ ከእነርሱም የተማርነው  ‹‹ ነቢይ በአገሩ አይከበርም››  የሚለውን ነውና በእነርሱ ውስት ያለው ለሌላው የሚተርፍ እምቅ አቅም የወሰድነውን አቋም አጠነከረልን እንጂ፣ ቀበቶኣችንን እንድናላላ አላደረገንም፡፡ ስለዚህም ስደትን ፈራን፤ አዎን ለዚህ ፈሪዎች ነን፡፡ ሰው እንኳን  በቀዬውና በአገሩ  ቀርቶ በተሰደደበትም ያለውን የሰው ልጅ ክብርና ነጻነት ነገሩንና በአገራችን ያለው ጭቆና እስከአጥንታችን ዘልቆ ገብቶ እንዲሰማን ፣ የተያዝነውን የነጻነት ትግል እንዲናጠናክር የሞራል  ስንቅ አቀበሉን እንጂ ስለመብትና ክብራችን መሞትን እንድንፈራ አላስተማሩንምና ፣ ስለነጻነታችንና ክብራችን ደፈርን፡፡
የዓለም ህዝብ ወደፊት እየገሰገሰ ባለበት ወደኋላ የመመለሳችን ጉዳይ ያስፈራናል ፣ለዚህ በጣም ፈሪዎች ነን፡፡ ይሁን እንጂ ወደነበርንበት የሥልጣኔ፣ የመከባበርና አብሮነት፣ የጀግንነትና ተጋድሎ የጋራ ታሪክ ከፍታ ለመመለስ የምናደርገው ትግል የሚጠይቀው ዋጋ  ከቶውንም አያስፈራንም ፡፡
ትናንት – የ‹ፈርስት ሂጂራ› መሪ እንዳሉት በዓለማችን የመጀመሪያዋ ስደተኛ ተቀባይ አገር ነበርን፤ በታሪካችን ከተራቡ  አፍሪካዊያን ወንድሞች አልፈን እስከ አውሮፓ ድረስ ለተራቡ መጋቢ ነበርን ፣በጥንታዊ ሥልጣኔ ተምሳሌት አገሮች ተርታ እንጠቀሳለን፣ ( የጥንታዊ ሥልጣኔ ትውፊቶችና አሻራዎች ዛሬም ድረስ አሉን፣ በቱሪስቶች እየተጎበኙ ነው)፣  የቅኝ አገዛዝ አስነዋሪዎችና የጥቁር ህዝብ የነጻነት አርኣያዎች ….. ነበርን፤ ‹ነበርን› ፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ አንጻር  ዛሬ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ስንታይ የዓለም ጭራ ሆነናል፡፡ ስደተኛ ተቀባዮች -ስደተኛ፣ የተራበ መጋቢዎች – የረሃብ ምሳሌዎችና ምግብ ተመጽዋቾች፣ የሥልጣኔ ቁንጮዎች – የኋላቀርነት ተምሳሌቶችና ያልተጣራና ያልተመዘነ የውጪ ሸቀጥና ቴክኖሎጂ ማራገፊያዎች፣ ከቅኝ አገዛዝ ተጠያፊነት ማማ ወርደን ‹ወዶ ገቦች› እና የነጻነት አፋኞች ተላላኪ ተዋጊዎች …. ሆነናል፡፡ በዓለም ፊት ረክሰናል፤ ተዋርደናል ማለት ይቻላል፡፡ ያስቆጫል፣ ያንገበግባል፡፡ በጨቋኝ አገዛዝ መንግስታት ተደጋጋሚ በትርና ሥር የሰደደ ጭቆና የትናንቱን አብነትና ትውፊት ከበጎ ጎኑ በተቃራኒ በማተኮራችን የኋሊዮሽ መጓዝ ተገደናል፡፡ ከአንድነታችንና አብሮነታችን ፣ ከጋራ ተጋድሎኣችንና ድሎቻችን በልዩነታችንና በገዢ አመራሮች በደል ላይ እንድናተኩር በመሆኑ ለገዢዎቻችን ተመችተናል፡፡  በተለይ በዚህ በዛሬው የጥቂት ዘረኛ  ቡድኖች   በተሰመረልን አቅጣጫ በተያያዝነው መንገድ  የ‹ሴራው› ሰለባ ሆነን ከቀጠልን  ከዚህ ወደከፋ አዘቅት፣ መቀመቅ መውረዳችን ፣ ለበለጠና የከፋ ውርደት መዳረጋችን አሌ አይባልም፡፡ የሚያስፈራን ይህ ‹ሴራ› የሚያመጣብን ጣጣ እንጂ ይህን ‹ሴራ › ለመቀልበስ የሚደረገው ትግልና የሚጠይቀው መስዋእትነት አይደለም፡፡ በኋሊዮሽ ጉዞኣችን ፣በመለያየታችንና መከፋፈላችን  የደረሰብን እንዳይደገም በተሻለና ወቅቱን በሚመጥን ፣ከዘመኑ በማይጣላ ፣….ከዓለም ጎን  የሚያቆመን፣ በሂደትም ከነበርንበት ከፍታ የሚመልሰን ሥርዓት እውን እንዲሆን አዲስቱን ኢትዮጵያ የመገንባት ተግባር የሁላችን መሆኑን ለመስበክ፣ ለዚህ ተግባራዊነት መስዋዕትነት መክፈል ለነጻነት፣ ለራስ ክብርና ማንነት፣ለሰብዐዊነት  የምንሰጠውን ቦታና ዋጋ የሚያሳይና ክብርን የሚያጎናጽፍ አኩሪ ተጋድሎ መሆኑን በመረዳታችን የምንፈራው ከዚህ ተጋድሎ ወደኋላ የሚጎትተንን ሁኔታ እንጂ  ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት አይደለም፡፡
አብረሃ ደስታ ‹‹የሰላማዊ ትግል በሮች ሲዘጉ የአመጽ በሮች ይከፈታሉ›› እንዳለው እየሆነ ያለው በጊዜ የአመጽ በሩ እንዲዘጋ ገዢው ህወኃት/ኢህአዴግ  ከተያያዘው የተለመደ የትዕቢት፣ እብሪትና ሴራ ፖለቲካ ወጥቶ ሁላችንን አሸናፊ ለሚያደርግ  ሁሉም የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያዊያን ተቀራርበው ብሄራዊ መግባባት የሚፈጥሩበት  ዕርቅ የሚወርድበት የውይይትና ድርድር መድረክ ተዘጋጅቶ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ካልተዘጋጀ በአገርና ወገን የሚያስከትለው ጥፋት በእጅጉ  ያስፈራናል እንጂ፤ ይህን አስፈሪና አሳሳቢ ሁኔታ ለመቀልበስ የሚጠይቀው መስዋዕትነትና ዋጋ አያስፈራንም፡፡
ህወኃት/ኢህአዴግ  እንደለመደው በተያያዘው መንገድ መቀጠልና ‹በጥልቅ ተሃድሶ› ታድሼ፣ ተጠናክሬ ወጥቼ የጭቆና ቀንበሩን አክብጄ እቀጥላለሁ በሚል ‹በአስቸኳይ አዋጅ›  ህዝብንና የሰላማዊ ትግል ሃይሎችን አትስሙ፣ አትናገሩ፣ አትነጋገሩ፣ አትመልከቱ ፣ አትገናኙ/አትሰብሰቡ  … በሚል መተንፈሻ አሳጥቶ፣ በእስራትና ወከባ አጅቦ የሰላማዊ ትግል ምህዳሩን መዝጋቱ፣ የህዝቡን  እምቢተኝነት ማፈኑ … ጊዚያዊ እፎይታ ይሰጠው እንደሆን እንጂ ህዝባዊ ትግሉን አይቀለብሰውም፣ አያስቀረውም፤ይልቁንም የአመጹን በር አስፍቶ ይከፍተዋል፣ በሰላማዊ ትግል ላይ ያለውን የተሟጠጠ የህዝብ ተስፋ ጨርሶ ያጠፋዋል፡፡ በኦሮሚያ ፣አማራ፣ ኮንሶ፣ የ‹በቃኝ› ህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ወደ ከፍተኛ ደረጅ ይገፋቸዋል፣ ሌሎችን ዜጎች የእምቢተኝነት ትግሉን እንዲቀላቀሉ ያነሳሳቸዋል ፤ የሰላማዊ ትግል ሰባኪዎችንና ታጋዮችን ወደ በረሃ ይገፋቸዋል ( የትናንት ሰላማዊ ታጋዮች እነ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፣ የሰማያዊ ወጣቶች፣ የመኢአድ አባላት… ዛሬ የት እንዳሉ ያጤኑኣል ) ፣የሌላውን አማራጭ  ተከታዮችን አብዝቶና አጠናክሮ (ከአገር ቤት ከአርባምንጭ ድረስ ፣ ከውጪ ከአውሮፓ አገራት ጭምር የትጥቅ ትግሉን የተቀላቀሉትን ያስታውሷል) ….. ወደተለመደው በመሳሪያ ኃይል የመተማመንና የኃይል/ትጥቅ ትግልና የአሸናፊ ጠቅላይ ወይም /እና አግላይ (ህወኃትን) የመንግስት ሽግግር አዙሪት ይከተናል፡፡ ይህን እንፈራለን ብቻ ሳይሆን በእጅጉ እንፈራለን፡፡  በወንድማማቾች መካከል በሚደረግ የትጥቅ ትግል/ጦርነት በዜጎች ህይወትና አካል፣ በአገር ሃብትና መሰረተ ልማት የሚያደርሰውን ጥፋትና ውድመት እንዲሁም  የቱንም ያህል የታጠቀና በወታደራዊ ኃይል የተደራጀና የተጠናከረ ጨቋኝ አገዛዝ  ህዝብን አሸንፎ  እንደማያውቅ … ለህወኃት/ኢህአዴግ መካሪ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡ ህወኃት ደርግን ብቻዬን አሸነፍኩ በሚል ግብዝነት ታስሮ በሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና በህዝብ ላይ ከሚያሳየው እብሪት ራሱን ነጻ ማውጣት እንዳለበት፣ ለራሱም ለአገሪቱም የሚበጀውን መንገድ ሊመለከት ግድ እንደሚለው፣ ለውጡ አይቀሬ የመሆኑ ሃቅ በህዝባዊ የእምቢተኝነት ትግልና በዲፕሎማሲ መድረኮች በግልጽ ሊነገረው ይገባል ፡፡ ትናንት ህወኃት በአሸናፊነት ሥነ ልቡና ያገለላቸውና  ‹‹ እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው ›› በሚል ለይስሙላ አሳትፎ ከሽግግሩ ወቅት ‹ያባረራቸው› ዛሬ ድረስ ህወኃት/ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንና ህዝቡን እያስከፈለ ያለው ዋጋ መረሳት ያስፈራናል፡፡ ይህ እንዳይደገም የምናደርገው ሰላማዊ ትግል ግን አያስፈራንም፤ ቅንጣት ያህል ፡፡
ህወኃት/ኢህአዴግ የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ለመነጠል የሚያሰራጨው ፕሮፖጋንዳና የሚፈጽመው ተግባር በህዝብ ላይ የፈጠረው ስሜት በእጅጉ ያስፈራናል  እንጂ ፣ይህን አደገኛ አዝማሚያና አፍራሽ አስተሳሰብ ለመቀልበስ የሚጠይቀው መስዋዕትነትና  ዋጋ አያስፈራንም፡፡ የትግራይ ህዝብ ላይ የተጫነውን ጭቆና ድርብ ድርብርብ መሆኑን መረዳት ፣ህዝቡ  ቀርቶ ህወኃትም የመፍትሄው አካል የመሆኑ አስፈላጊነት ላይ ጠንክረን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ አካታች መድረክ የምንለውም ይህንኑ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ ህወኃት ‹‹የትግራይ ህዝብና ህወኃት፣ የኢትዮጵያ ህዝብና ኢህአዴግ አንድ ናቸው፤ ዕጣ ፈንታቸውም የተያያዘ/የተሳሰረ  ነው፡፡ እኛ ህወኃት/ኢህአዴግ ከሥልጣን ከወረድን አገር ትፈራርሳለች …›› የሚለው ማስፈራሪያ ይንኮታኮታል ፡፡
ሌላው የአገራችን ህዝብ የህወኃት ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሆኖ ከትግራይ ህዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ከጥያቄ የመግባቱ አዝማሚያ ፣ የመተማመንና ወንድማማችነተ መንፈስ መሸርሸሩ ጉዳይ ያስፈራናል እንጂ፣ ይህን ለመቀልበስ …. የምንከፍለው ዋጋ  አያስፈራንም፤ ለዘላቂ ለውጥ ለጤናማ የህዝብ ግንኙነት…. አብሮነትና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መከፈል ያለበት ዋጋ ነውና- አያስፈራንም፡፡
የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች  የጥቂት ዘረኛና ጠባብ ጥቅመኛ ቡድን አባላት ጥቅም ለማስጠበቅ ፣ ሥልጣን ለማስቀጠል ጋሻ መከታ ሆኖ የማገልገል የተላላኪነት ሚና ያሳስበናል እንጂ፣ ይህን ለመመከት ጥቅመኞችንና ተላላኪዎችን ከህዝብ ለመለየት የሚጠይቀው መስዋዕትነት አያስፈራንም፡፡ …. የምንፈራው ስለአገር ስለወገን ከምንከፍለው መስዋዕትነት የሚጎትተንን፣ የመስዋዕትነታችን ውጤታማነት የሚያኮላሽ፣ ….የህዝባችን ሥቃይና መከራ ዘመን የሚያራዝም ሁኔታ እንጂ ፣ወደ ትግሉ ስንገባ ያለመስዋዕትነት ድል ያለመኖሩን ተቀብለን ነውና  ይህ አያሳስበንም፣ አያስፈራንም ፡፡
ግን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማይከፋፈል፣ አገሪቱም በማንም መቼውንም እንማትጠፋ፣ የዚህ ጠባብ ዘረኛ አገዛዝ ዘመንም የህዝባችን  አንድነት ሊያጠናክር ፣ የአገራችንን ቀጣይነትና ዘላቂ ሰላምና ክብር በጠንካራ መሰረት ላይ እንድታነጽ በጥልቅ እንድንፈተንበት የመጣ ነው ብለን ስለምናምን በጥቂት ዘረኞችና ጥቅመኛ ቡድኖች የተሸረበው ሴራ እንደሚከሽፍ፣ ለውጡ አይቀሬ ስለመሆኑ  አንጠራጠርም፡፡  ስለዚህም አንፈራም፡፡
በሰላማዊ ትግል  ከተሰለፉ የአገር ቤት ሰላማዊ ታጋዮች አልፎ በውጪ አገር ባሉ ድርጅቶች መካከል  መከባበርና መወያየት፣ …. መጥፋቱ  የተናጠል ሩጫው፣ መከፋፈልና አንጃው፣ አለመተማመን፣  ተባብሮ በአገራዊ ጉዳይ ላይ አብሮ በመስራት ደጋግሞ መክሸፍ፣ ….. ህዝብ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ያለው እምነት ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ  በእጅጉ ያሳስበናል፣ ያስፈራናል፡፡  ይሁን እንጂ ይህ የተቃውሞ ጎራው  ያለመተማመንና አብሮ የመስራት ችግር እንዳይቀጥል ‹ማዶ ለማዶ› ከሚተያዩበት፣ ሲያልፍም ከሚጠላለፉበት ሁኔታ ወጥተው አብረው እንዲሰሩ ለሚደረገው ጥረት የምናደርገው አስተዋጽኦ  አያስፈራንም፣ ይቀጥላል፡፡
ለትግሉ የምንከፍለው መስዋዕትነት አያስፈራንም ስንል የእኛ ትግል የሚፈራው ጭቆናና ጨቋኞችን እንጂ አንዱን ወይም ሌላውን  ህዝብ ባለመሆኑ፣ የትግላችን ግብም አንድን ጨቋኝ በሌላ ለመቀየር፣ ወይም በጥላቻ ላይ ቆሞ  ህወኃት/ኢህአዴግን በማስወገድ ብቻ ያልተወሰነ፤ በአገርና ህዝብ ዘላቂ ጥቅምና ሰላም፣ በእኩልነትና ፍትሃዊነት በምንገነባው አንድነት ላይ ያነጣጠረ፤ መሰረታችን፣ የጥንካሬና ጽናት ምንጫችን እውነትና እውነት ብቻ  በመሆኑ ነው፡፡  ስለዚህም ፍርሃታችን ትግላችን በዝና፣ በሥልጣን ጥማት፣ ሃብትና ጥቅም  ዓላማውን  እንዳይስትና የሥቃይ ዘመናችን እንዳያራዝም፤ በጥላቻ፣ እብሪት፣ ማንአለብኝነትና  የኃይል አምልኮ እንዳይጠለፍ፤ ከዘላቂ፣ሰላማዊ…. ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ በተቃራኒ አቅጣጫውን ወደ አግላይና ጠቅላይ የሥልጣን ሽግግር እንዳያዞር  ነው፡፡
በውጪ አገር አሁን የተጀመረው የ‹ ቪዥን -ኢትዮጵያ/ ኢሳት› ስለመጪዋ ኢትዮጵያ ፣ የሎንዶንና አትላንታ የኦሮሚያ ተወላጆች ‹ በትብብር ስለመስራት› በተደረጉት የውይይት መድረኮች የተንጸባረቁት ሃሳቦች፣  ….ትምህርታዊነቱ ለመማር ለሚፈልግ ጅምሩ ጥልቅ መልዕክት አለው፡፡ ይህ እንደተለመደው  አንዳይከሽፍ ሥጋት ቢኖረንም በጅምሩ ያለን ተስፋ የቀጣዩን ጊዜ ብሩህነት ያመላክታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን  ጥረት ለማበረታታትና ለማገዝ የምንቆጥበው የለም፡፡ በተመሳሳይ በአገር ቤት እንዲህ ዓይነቱ ትርጉም ያለው ውጤት ሊያመጣ የሚያስችል  የተቃውሞ ጎራው ግንኙነት እንዲጀመር የነቃ ተሳትፎ ለማድረግና የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ያለንን ቁርጠኝነት ስናረጋግጥ የፈራናቸው ጉዳዮች  እውን እንዳይሆኑና በአገርና ህዝብ ላይ ጥፋት እንዳያመጡ እያንዳንዱ ዜጋ ያለማሰለስ በንቃት መሳተፍ ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አይደለም እላለሁ፣ እናንተስ ???
በመጨረሻም በእኛ በኩል ከላይ ባቀረብነው ሁኔታ በአገራችን ከህዝባችን ጋር እየኖርን፣ እየታገልን – የቱንም መስዋዕትነት ለመክፈል ያለንን ውሳኔና ቁርጠኝነት ደግመን  እንገልጻለን፡፡
  1. በፌስ ቡክ ለመገናኘት ባለብን ችግር  ምክንያት በዚህ መልክ በድረ- ገጾች  ለመወያየት  አስበናል፡፡ ከዚህ በፊት በፌስ ቡክ ‹ጨዋታ› በሚል አቀርብ የነበረው ዓይነት በዚህ ደግሞ ‹እኔ የምለው› በሚል በተከታታይ ለማቅረብ ሙከራው ተጀምሯልና ወዳጆቼበ- Ethiomedia .com   እና Mereja.com  ላይ እንድነገናኝ ጥሪዮ ይድረሳችሁ፡፡
  2. አስተያየታችሁን በኢሜይል አድራሻዬ — girmabkbk62@yahoo.com  ላኩልኝ፡፡
ህዳር ሥላሴ/ 07/03/09.   በቸር  ያገናኘን፡፡

No comments:

Post a Comment