Sunday, January 15, 2017

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አላና ፖታሽን በታክስ ማጭበርበር source ethiopian reporter




ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አላና ፖታሽን በታክስ ማጭበርበር ወነጀሉ

-  አላና ፖታሽ ግን በሰላማዊ መንገድ ችግሩን እንፍታ ብሏል
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አላና ፖታሽ የተሰኘውን በአፋር ክልል በፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ተሰማርቶ የነበረውን የካናዳ ኩባንያ በታክስ ማጭበርበር ወነጀሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አላና ፖታሽ የኢትዮጵያ መንግሥትንና አይሲኤል የተባለውን የእስራኤል ኩባንያ ማጭበርበሩን ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ የማዕድን ዘርፍ ስላለበት ሁኔታና እንደ አላናና አይሲኤል ያሉ የማዕድን ኩባንያዎች ሥራቸውን አቋርጠው መውጣት በዘርፉ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአላና ጉዳይ ከታክስ ስወራ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
‹‹የአላና ፖታሽ ጉዳይ ግብር ከማጭበርበር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኩባንያው ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር መክፈል ያለበት የግብር ዕዳ አለበት፡፡ ያንን ግብር መክፈል አለበት፡፡ መንግሥት ይኼን በሆነው መንገድ በሕግም ፈልጎ ያስከፍላል፤›› ብለዋል፡፡
በቶሮንቶ ስቶክ ገበያ ተመዝግቦ ሲንቀሳቀስ የቆየው አላና ፖታሽ፣ ‹‹አላና ፖታሽ አፋር›› የሚባል እህት ኩባንያ በማቋቋምም በአፋር ክልል ዳሎል አካባቢ የፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ሥራ ለስድስት ዓመታት ያህል ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ አላና ፖታሽ አፋር ለማዕድን ፍለጋ ሥራው 90 ሚሊዮን ዶላር ማውጣቱን፣ 3.2 ቢሊዮን ቶን የፖታሽ ክምችት ማግኘቱን በወቅቱ አስታውቋል፡፡
የፖታሽ ክምችቱን ለማልማት 750 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው፣ የፖታሽ ማምረቻ ፋብሪካውን ገንብቶ በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ430 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት የሚያስችል ዕቅድ ለመንግሥት አቅርቦ ይሁንታን አግኝቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 የማዕድን ሚኒስቴር ለአላና ፖታሽ አፋር የከፍተኛ ማዕድን ማምረቻ ፈቃድ ሰጥቶታል፡፡
ይሁን እንጂ በዓለም ገበያ የማዕድናት ዋጋ በመውደቁና አላና ፖታሽ የሚፈለገውን ካፒታል ማሟላት ባለመቻሉ፣ እስራኤል ኬሚካልስ ሊሚትድ (አይሲኤል) ለተባለው ታዋቂ የማዳበሪያ አምራች የአክሲዮን ድርሻውን ሸጧል፡፡ አይሲኤል ቀደም ሲል የአላና ፖታሽ በቶሮንቶ ስቶክ ገበያ 16 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ገዝቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 የተቀረውን 84 በመቶ በ140 ሚሊዮን ዶላር ገዝቶታል፡፡
በወቅቱ የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ስለሽያጩ ቀደም ብሎ አልተገለጸልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰሙ ቢሆንም፣ የአላና ፖታሽ ኃላፊዎች በበኩላቸው ለሚኒስቴሩ አሳውቀናል ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
አላና ፖታሽን ከገዛ በኋላ አይሲኤል የአላና የማዕድን ማምረቻ ፈቃድ እንዲዛወርለት ለማዕድን ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡ ሚኒስቴሩ ማመልከቻውን በመገምገም ላይ ሳለ የፖታሽ ፕሮጀክቱ ሥራ እንዳይቋረጥ አይሲኤል ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች አስገብቶ ሥራውን እንዲቀጥል መፍቀዱን የቀድሞው ሚኒስትር አቶ ቶለሳ ሻጊ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች አይሲኤል አስፈላጊዎቹን ሰነዶች አሟልቶ እንዲያቀርብ ጠይቀው ጉዳዩን በማየት ላይ ሳሉ፣ አይሲኤል (አላና ፖታሽ አፋር) ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር በታክስ ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ገብቷል፡፡ ባለሥልጣኑ በአላና ፖታሽ ሊከፈል የሚገባ የዊዝሆልዲንግና የቫት ክፍያ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ በአላናና በአይሲኤል መካከል በተፈጸመው ሽያጭ ውል መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን የካፒታል ዕድገት ግብር በአጠቃላይ 55 ሚሊዮን ዶላር ግብር እንዲከፈል ጠይቋል፡፡
የአይሲኤል ኃላፊዎች በበኩላቸው በአላና ሊከፈል የሚገባ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የዊዝሆልዲንግና የቫት ግብር ለመክፈል ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ ይህን ሊቀበል አልቻለም፡፡
በግብር ጥያቄው የተደናገጡት የአይሲኤል ኃላፊዎች ሥራቸውን አቁመው ከአገር ወጥተዋል፡፡ በጥቅምት 2009 ዓ.ም. የአይሲኤል ዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያሠራን ስላልቻለ በኢትዮጵያ የጀመርነውን ኢንቨስትመንት ለማቋረጥ ተገደናል፤›› ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊውን መሠረተ ልማትና የሕግ ማዕቀፍ ሊያቀርብልን ባለመቻሉ፣ የታክስ ባለሥልጣኑ አላና ፖታሽ አፋር ላይ ሕገወጥ የታክስ ጥያቄ በማቅረቡ የኩባንያው ሥራ እንዲቋረጥ ወስነናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ድርጊት ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ከለላ ውሎችን የጣሰ ነው፤›› ብሏል ቦርዱ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሰጡት ምላሽ ከአይሲኤል መግለጫ ጋር የማይጣጣም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት አላና ፖታሽን እንጂ አይሲኤልን እንደማያውቀው ነው የተናገሩት፡፡
‹‹አይሲኤልን በተመለከተ አይሲኤል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተደራደረው ነገር የለም፡፡ አላና ፖታሽ ከሚባል አንድ የፖታሽ ኩባንያ ጋር የኢትዮጵያ መንግሥትን ሳያሳውቁ ከበስተጀርባ ተደራድረው ነው የመጡት፡፡ እኛ አሁንም የምናውቀው አላና ፖታሽን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተመዝግቦ ሲንቀሳቀስ የነበረው እሱ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አይሲኤል ከበስተጀርባ ተደራድሮ ከበስተጀርባ እንደሄደ ተናግረዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም እኛ የምናውቀው አላና ፖታሽን ነው፡፡ እኛ አገር ውስጥ ተመዝግቦ የሚሠራው አላና ፖታሽ ነው፡፡ ከቀጠለ ይቀጥላል፣ ካልቀጠለ ለሌላ ኩባንያ እንሰጣለን፡፡ ብዙ ፈላጊዎች ስላሉ ብዙ የሚያሳስበን ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ አላና ፖታሽ አይሲኤልን እንዳጭበረበረ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ ‹‹አይሲኤል በራሱ በአላና ፖታሽ የተጭበረበረ መሆኑን አውቆ ነው የሸሸው፡፡ ምክንያቱም እኛ ግብር ይከፈል ስንል እነሱ ከጀርባ የተፈራረሙት ይህን ሁሉ ስለማያካትት፣ ከዚህ ተቋም ጋር መቀጠል አንችልም ብለው ነው የሄዱት፡፡ አሁንም ቢሆን መጥተው ግብሩ ከተከፈለ በኋላ ስማቸውን ለማዛወር ከፈለጉ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝግጁ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼን ቢሉም የቀድሞ አላና ፖታሽ ማኔጅመንትና ቦርድ አባላትና የአይሲኤል ኃላፊዎች በድብቅ የተደረገ ስምምነት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የቀድሞ የአላና ፖታሽና የአይሲኤል ኃላፊዎችን አስደንግጧል፡፡
ከአላና ፖታሽ አፋር መሥራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ነጂብ አባቢያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሰዎች ሳያሳስቷቸው እንዳልቀሩ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን እናከብራቸዋለን፡፡ ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅና፣ ከአፍሪካ በፍጥነት በማደግ ላይ የምትገኝ አገር መሪ ናቸው፡፡ አላና ፖታሽን በተመለከተ ግን የቀረበላቸው መረጃ የተሳሳተ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚናገሩት በበታቾቻቸው በቀረበላቸው መረጃ ነው፡፡ እኔ የቀረበላቸው መረጃ የተሳሳተ ነው ባይ ነኝ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ በጣም ቀላል ነው፡፡ አላና ፖታሽንና አይሲኤልን በተመለከተ የተፈጸመው ውል የተመዘገበና በእኛና በመንግሥት እጅ የሚገኝ ለመሆኑ ሰነዶቹን በእርጋታ በመመርመር ማረጋገጥ ይቻላል፤›› ብለዋል አቶ ነጂብ፡፡
አላና ፖታሽ ለአይሲኤል መሸጡ በገሃድ የተካሄደ እንደሆነ፣ በወቅቱ የአላናና የአይሲኤል ከፍተኛ ኃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ከቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ከቀድሞ የማዕድን ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ ጋር በመገናኘት አይሲኤል በኢትዮጵያ ለመሥራት ስላሰበው ሰፊ ኢንቨስትመንት ማብራሪያ መስጠታቸውን፣ በወቅቱም መሪዎቹ ዕቅዱን በበጎ ሁኔታ መቀበላቸውንና ማበረታታታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹በድብቅ የተደረገ ድርድር የተባለው እኔ አልገባኝም፡፡ ሁለቱም ኩባንያዎች በስቶክ ኤክስቼንጅ ለሕዝብ ለሽያጭ የቀረቡ በመሆናቸው ማንኛውንም መረጃ መደበቅ አይችሉም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖች ስላላቸው ለእነሱ እያንዳንዱን ነገር ማሳወቅ በሕግ ይገደዳሉ፡፡ ግዢውም ቢሆን በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ሪፖርተርን ጨምሮ ዘግበውታል፡፡ ምኑ ነው ድብቅ?›› ብለዋል፡፡
አይሲኤል አላና ፖታሽን ከመግዛቱ ቀደም ብሎ ጀምሮ ከግብርና ሚኒስቴርና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በቅርበት ይሠራ እንደነበር የአይሲኤል ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የአይሲኤል ዋና ባለድርሻና የእስራኤል ቁጥር አንድ ቱጃር የሆኑት ኢዳን ኦፋርና በወቅቱ የአይሲኤል ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ሚስተር ስቴፋን ቦርጋስ፣ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ በማዳበሪያ አጠቃቀም ዙሪያ ለሚካሄዱ ፕሮግራሞች የገንዘብና የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ቃለ መጠይቁ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ 600,000 ዶላር መለገሳቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የታክስ ማጭበርበር ተፈጽሟል ስለተባለው አቶ ነጂብ አይሲኤል አላና ፖታሽን ከመግዛቱ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል አላና ፖታሽ ስላለው ንብረትና ዕዳ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የኢትዮጵያና የውጭ ባለሙያዎች ቀጥሮ ሰፊ የምርመራ ሥራ መሥራቱን፣ ባካሄደውም ጥናት አላና ያለበትን ዕዳ አብጠርጥሮ ማወቁንና ዕዳውንም ለመክፈል መስማማቱን ተናግረዋል፡፡
‹‹እንኳን በዓለም ገበያ ላይ የተመዘገበ ኩባንያ ስትገዛ አይደለም አዲስ አበባ ውስጥ አንድ አነስተኛ ቤት ስትገዛ የባንክ ዕዳ አለበት ወይ? የአገር ውስጥ ገቢ አለበት ወይ? ክርክር አለበት ወይ? መንገድ ይወጣበታል ወይ? ብለህ ትጠይቃለህ፡፡ እንዴት ነው አይሲኤልን የሚያህል ግዙፍ ኩባንያ የሚገዛውን ኩባንያ ዕዳ ሳያጣራ ገንዘብ የሚከፍለው?›› ሲሉ በሁኔታው ግራ መጋባታቸውን ገልጸዋል፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደብዳቤ እንደሚጽፉ፣ ከተፈቀደላቸውም በአካል ቀርበው ለማስረዳት ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያለውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንደምንፈታው አምናለሁ፡፡ ሁሉም ነገር በመዝገብ የተያዘ ነው፤›› ያሉት አቶ ነጂብ፣ አላና ፖታሽ ለማዕድን ፍለጋ ሥራው 90 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን፣ በወቅቱ ለ450 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ አብዛኛው ባለአክሲዮን ድርሻውን ከስሮ መሸጡን ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የቀድሞ የአላና ፖታሽ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፈርሃድ አባጎቭ፣ ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ተመካክረው ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አይሲኤል ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአላና ዕዳ የሆነ ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር (200 ሚሊዮን ብር) የታክስ ግብር ለመክፈል ሐሳብ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ 55 ሚሊዮን ዶላር የካፒታል ዕድገት ታክስ ጨምሮ እንዲከፍል በመጠየቁ ሳይስማሙ ቀርተዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 4 ቀን 2016 አይሲኤል (አላና ፖታሽ አፋር) ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ለማዕድን ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ የዳሎል ፖታሽ ፕሮጀክቱን ዘግቶ ለመንግሥት ማስረከብ እንደሚፈልግ፣ አላና ፖታሽ አፋር የሚጠበቅበትን (ያለበትን) በሰነድ የተደገፈ ግብር እንዲሁም ሌላ ማንኛውም ዕዳ ካለ ለመዝጋት ፍላጎት እንዳለው አሳውቋል፡፡ ፕሮጀክቱን ለመዝጋት የሚልካቸውን ባለሙያዎች ምንም ዓይነት ችግር እንደማይፈጠርባቸው ዋስትና እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ሪፖርተር ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ አይሲኤል ለጻፈው ደብዳቤ እስካሁን ከመንግሥት በጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሪፖርተር ለአይሲኤል ኃላፊዎች በኢሜይል አድራሻቸው ለላካቸው ጥያቄዎች ማተሚያ ቤት እስከገባበት ሰዓት ድረስ ምላሽ አላገኘም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የማዕድኑ ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል የገለጹ ቢሆንም፣ ኢኮኖሚው በማዕድን ዘርፉ ላይ ጥገኛ እንዲሆን መንግሥታቸው እንደማይፈልግ አስረድተዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment