” የማይሰርቅ ባለስልጣን የተደበቀ አጀንዳ አለው። ” የሕወሓት ክቡር ሚኒስትሮች እና የገና በዓል ስጦታዎቻቸው
#Ethiopia " የማይሰርቅ ባለስልጣን የተደበቀ አጀንዳ አለው። " የሕወሓት ክቡር ሚኒስትሮች እና የገና በዓል ስጦታዎቻቸው በበዓል ስጦታዎች ተንበሸበሽኩ፡፡ ......... ይኼንን የምታየውን ሙክት ,,,,,,,,,, ይኼንን ካርቶን ሙሉ ኮኛክና ውስኪ ........ ይኼንን 59 ኢንች ዘመናዊ ቲቪ ....... የአዲሱን ኒሳን ፓትሮል መኪና ቁልፍ  ....... ሰው ግን ለምንድነው ሌባ የሚሆነው፡፡. ..... አንዳንዱ ኑሮ አልሞላለት ሲለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የመበልፀግ ትልቅ ራዕይ ስላለው ...........
#Ethiopia ” የማይሰርቅ ባለስልጣን የተደበቀ አጀንዳ አለው። ” የሕወሓት ክቡር ሚኒስትሮች እና የገና በዓል ስጦታዎቻቸው
በበዓል ስጦታዎች ተንበሸበሽኩ፡፡ ……… ይኼንን የምታየውን ሙክት ,,,,,,,,,, ይኼንን ካርቶን ሙሉ ኮኛክና ውስኪ …….. ይኼንን 59 ኢንች ዘመናዊ ቲቪ ……. የአዲሱን ኒሳን ፓትሮል መኪና ቁልፍ ……. ሰው ግን ለምንድነው ሌባ የሚሆነው፡፡. ….. አንዳንዱ ኑሮ አልሞላለት ሲለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የመበልፀግ ትልቅ ራዕይ ስላለው ………..
[ክቡር ሚኒስትር ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]
  • ምንድነው እየሰማሁት ያለው?
  • ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
  • በዓለም ዙሪያ ማለቴ ነው፡፡
  • ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሥልጣን ይጨብጣሉ፡፡
  • እሺ?
  • ባራክ አባማ ይሸኛሉ፡፡
  • እሺ?
  • ሌላ ደግሞ …
  • ሌላ ምን?
  • የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በሙስና ተጠርጥረው በፖሊስ ተመረመሩ፡፡
  • ሙስና ስትል ምን ትዝ አለኝ መሰለህ?
  • ምን ትዝ አለዎት ክቡር ሚኒስትር?
  • ሰው ግን ለምንድነው ሌባ የሚሆነው፡፡
  • ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡
  • ለምሳሌ?
  • አንዳንዱ ኑሮ አልሞላለት ሲለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የመበልፀግ ትልቅ ራዕይ ስላለው ነው፡፡
  • ህም…
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • እኔ ግን ከአንተ ከንቱ ሐሳብ እለያለሁ፡፡
  • እስኪ ይንገሩኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • ሙስና ውስጥ የሚገባው በሞራል መዝቀጥ ምክንያት ነው፡፡
  • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
  • የደሃ ኩሩ ሌብነትን ይፀየፋል፡፡
  • የሀብታም ኩሩስ ክቡር ሚኒስትር?
  • እሱ በሁለት ይከፈላል፡፡
  • በምንና በምን ክቡር ሚኒስትር?
  • ሞራል ካለው ምልጃ አይፈልግም፣ አይልከሰከስም፡፡ ሞራል ከሌለው ግን ከደሃ ላይም ይቀማል፡፡
  • እኔ ግን ክቡር ሚኒስትር …
  • አንተ ምን?
  • ማለቴ አለ አይደል?
  • ምንድነው እሱ?
  • ይኼ ዘመን እኮ ያሳሳል፡፡
  • በምኑ?
  • ደልቃቃ ቪላ፣ ቅንጡ መኪና፣ ፀዳ ፀዳ ያሉ …
  • ማቴሪያሊስት ከሆንክ የሚያጓጓ ብዙ ነገር አለ፡፡
  • እርስዎ ምንድነዎት?
  • እኔ ነፍስና ሥጋዬን አመጣጥኜ ነው የምኖረው፡፡
  • እንዳይሰሙዎት?
  • እነ ማን?
  • በሀብት ላይ ሀብት የሚደረድሩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኔ ህሊናዬን ነው የምፈራው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ብዙዎች ወደኋላ የቀሩት ህሊና ህሊና ነው ሲሉ ይባላል እኮ፡፡
  • ይኼ የአንተና የቢጤዎችህ ወሬ ነው፡፡
  • ሀብት ያካበቱት ግን እንዲህ አይሉም፡፡
  • ሰማህ?
  • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼ ሁሉ ዳርዳርታህ ይገባኛል፡፡
  • ምንድነው እሱ ክቡር ሚኒስትር?
  • ህሊናዬን ትቼ ሌላ ነገር ውስጥ እንድገባ፡፡
  • እንዴት አወቁ ክቡር ሚኒስትር?
  • ዓይንህ ያሳብቃል፡፡
  • ምን እያለ?
  • ለምን አንሰርቅም እያለ ነዋ፡፡
  • እርስዎ መስረቅ ወይም ሌብነት ይላሉ እንጂ የተከበረ ስም አለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ይባላል?
  • ቢዝነስ!
  • የትኛው ዲክሽነሪ ውስጥ ነው ያገኘኸው?
  • አራዶቹ ዲክሽነሪ ውስጥ፡፡
  • ሌብነት አራድነት ከሆነ ጨዋነት ምን ሊባል ነው?
  • በዚህ ዘመን ጨዋነት ራሱ አይታመንም፡፡
  • ለምን?
  • ምናልባት የተደበቀ አጀንዳ ይኖረዋል ተብሎ ይፈራል፡፡
  • ማነው የሚፈራው?
  • ጠንቃቆቹ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እነዚህን ጠንቃቆች ከማለት ሌላ ማለት ይቀላል፡፡
  • ጠንቃቆች ምን ይባሉ ክቡር ሚኒስትር?
  • ሴረኞች!
[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸውን ጠርተዋት እየተነጋገሩ ነው]
  • ይኼ አማካሪዬ ከእነ ማን ጋር ነው የሚውለው?
  • በብዛት ጓደኞቹ ሀብታሞች ናቸው ይባላል፡፡
  • ከድሮ ጀምሮ ነው?
  • ኧረ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያፈራቸው ናቸው አሉ፡፡
  • አንቺ በምን አወቅሽ?
  • ወሬ ይደበቃል እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
  • ማን ነገረሽ?
  • ክቡር ሚኒስትር ምንጩን አይጠይቁኝ፡፡
  • የሀብታሞች ጓደኛ ለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለሽ?
  • ምሳው ክትፎ እራቱ ጎልድ ሌብል እንደሆነ በስፋት ይወራለታል፡፡
  • ሀብታሞቹ ለምን ጓደኛ አደረጉት?
  • የወርቅ ማዕድን የሚባል ቅፅል ስም ስላለው፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ እንደሆነ ስለሚነገርለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የእኔ አማካሪ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ስለሆነ?
  • የክቡር ሚኒስትሩ የተከበረ አማካሪ ስለሆነ ነዋ፡፡
  • ቢሆንስ?
  • ቁልፉ በእጁ ነው ይባልለታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኔ የት ሄጄ?
  • እርስዎ አዲስ ስለሆኑ እሱ ነው የሚታወቀው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በምንድነው የሚታወቀው?
  • ነገሮችን በማሳለጥ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ማሳለጥ?
  • አዎን ማሳለጥ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • ውሳኔዎችን ያስቀለብሳል፣ ለቢጤዎቹ በሚጠቅም መንገድ ያስወስናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼንን እያደረገ ነው?
  • ከማድረግም በላይ ዕውቅና አግኝቶበታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን የሚባል ዕውቅና?
  • የተከበሩ አማካሪ፡፡
  • አንቺም ታውቂያለሽ?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምን አልነገርሽኝም?
  • እርስዎ መቼ ጠየቁኝ?
  • ካልተጠየቅሽ አትናገሪም?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ልሳንሽ ይዘጋ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ እየተበሰጫጩ ሾፌራቸው ወደ ቤት እየወሰዳቸው ነው]
  • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን ሆንኩ?
  • የተናደዱ ይመስላሉ፡፡
  • አንዳንዴ የሚያናድድ አይጠፋም እባክህ፡፡
  • እነዚህን ሁለት ሰዎች አጠገብዎ አስቀምጠው እንዴት አይናደዱ ክቡር ሚኒስትር?
  • ማንን?
  • አማካሪና ጸሐፊ ተብዬዎቹን ነዋ፡፡
  • ለምን እንዲህ አልክ?
  • ሁለቱ አንድ ላይ ሲገጥሙ አይቻሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ያደርጋሉ?
  • የጥቅም ተጋሪ ናቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አሁን ግን የተጣሉ ይመስላሉ እኮ?
  • የጥቅም ግጭት ሲፈጠር እርስ በርስ ይያያዛሉ፡፡
  • ከዚያስ?
  • አንዳቸው ሌላቸውን ማማት ነው ሥራቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አሁን ተጣልተዋል ማለት ነው?
  • ዞረው መግጠማቸው አይቀርም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኔ ከጸሐፊዋ እንደሰማሁት አይመስለኝም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ጥቅም ያፋቅራል፣ ጥቅም ያጋጫል ሲባል አልሰሙም?
  • ይኼንን ሁሉ ጉድ ሰምቼ ሊታረቁ?
  • እነሱ ቆዳቸው ወፍራም ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሁለቱንማ እለያየለሁ፡፡
  • አንዳቸው ለአንዳቸው ይቅርታ ይጠይቁዎታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼን ያህል ምን ስለሆኑ?
  • ስለሸጡት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምንድነው የሸጡት?
  • ህሊናቸውን፡፡
[ክቡር ሚኒስትር ቤት ሲገቡ ባለቤታቸው ከደጅ በፈገግታ ተቀበሉዋቸው]
  • ምን ተገኘ እባክሽ እንዲህ በፈገግታ የተሞላሽው?
  • ደስ ሲለኝስ?
  • ይኼን ያህል?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ንገሪኝ እባክሽ?
  • በዓል ደርሷል አይደል?
  • አዎን፡፡
  • ከወጪ ተገላገልኩ በዚያ ላይ …
  • ምን አግኝተሽ?
  • ስጦታ፡፡
  • የምን ስጦታ?
  • በበዓል ስጦታዎች ተንበሸበሽኩ፡፡
  • ማን ሰጠሽ?
  • ማን ምን እንደላከልኝ ላሳይህ፡፡
  • እንዴ ይኼ ሁሉ ምንድነው?
  • ይኼንን የምታየውን ሙክት የላከልኝ አማካሪህ ራሱ ነው፡፡
  • ምን?
  • ይኼንን ካርቶን ሙሉ ኮኛክና ውስኪ የላከልኝ የአማካሪህ ጓደኛ ነው፡፡
  • እንዴ?
  • ይኼንን 59 ኢንች ዘመናዊ ቲቪ የላከልኝ ሌላው የአማካሪህ ጓደኛ ነው፡፡
  • ኧረረረ …
  • ይኼንን ደግሞ …
  • ይኼንን ምን?
  • ተመልከተዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የቁልፍ መያዣ ይመስላል፡፡
  • ተሳስተሃል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • የአዲሱን ኒሳን ፓትሮል መኪና ቁልፍ የላከው ደግሞ የተከበረው አማካሪ ምርጥ ጓደኛ ነው፡፡
  • ምን አልሽ አንቺ?
  • መልካም የገና በዓል