Tuesday, January 24, 2017

ግንቦት ሰባት ፥ ኢሳት እና ትግሉ – (ኄኖክ የሺጥላ)



ግንቦት ሰባት ፥ ኢሳት እና ትግሉ (ኄኖክ የሺጥላ)
ከግንቦት ሰባት ጋር የሚያስታርቅ ነገር እስከ አሁን አልገጠመኝም! ከግንቦት ሰባት ጋር ያጋጨኝ ነገር ፥ ከወያኔ ጋር ያጋጨኝ አይነት አይደለም! ግንቦት ሰባት የከሸፈ ፥ አቅም የሌለው ፥ አቅመ ቢስነቱን እያወቀ በደረቁ የኢትዮጵያ ህዝብን ለማጭበርበር ደፋ ቀና የሚል ድርጅት ስለመሆኑ ከማንም በላይ ደጋፊዎቹ እና መሪዎቹ በደንብ ያውቃሉ። ግንቦት ሰባት በአባላቱ ላይ ሳይቀር ፕሮፖጋንዳ የሚሰራ ድርጅት ነው። አሁንም በመላው አለም ላይ ሊያደርጉት ያሰቡት ጉዞ ፥ ከጭንቀት የመነጨ ፥ አባላትን ለማረጋጋት ታስቦ የተዶለተ ተራ የፖለቲካ ቁማር ስለመሆኑ ፥ ከስብሰባው ቀድሜ ፥ በስብሰባው ላይ ፥ ይህ ነው የሚባል የረባ ነገር እንደማያስተላልፉ መናገር እችላለሁ!
ችግሩ የግንቦት ሰባት መክሸፍ አይደለም ። ችግሩ ግንቦት ሰባት በኤች አይቪ እንደተያዘ ክፉ አባወራ ማሰቡ ነው እንጂ ! በዚህም ድምዳሜው ፥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢሳትን ተአማኒነት ፥ እና የኢሳትን የህዝብነት ለድርጅቱ ተክለ ሰውነት ሲባል እንዲረግፍ እያደረገ ያለ ድርጅት ነው ! እኔን ከያዘኝ ኢሳትም ይማቅ አይነት ነገር! ይህ ግንቦት ሰባትን ከወያኔ ጋር የሚያመሳስለው አብይ ጉዳይ ይመስለኛል። ግንቦት ሰባት ደጋፊዎቹን ያለ ምክንያት የመደገፍ ጥቅምን አጥምቆዋቸዋል ። ሃሳብን መሞገት ሲያቅታቸው ፥ ባለቻቸው ሚጢጢ ትልቅነት ግዝብዝ ሲሆኑ ታስተውላለህ ።
ለምሳሌ
የዛሬ ሁለት ሳምንት እዚህ ሳን ሆዜ የሚኖር የግንቦት ሰባት በከተማው ሁለተኛ ሰው የሚያስተዳድረው ሆቴል አለው። ይህ ሰው ጥሩ ወዳጄ የነበረ ነው። የግንቦት ሰባት አባል በነበርኩበት ወቅት ከዚሁ ሰው ጋር ነው ሎስ አንጀለስ ድረስ ተጉዘን የኤፍሬም ማዴቦን « አማራ ምን አባቱ !» አይነት ንግግር የሰማነው። ያም ሆኖ ከግንቦት ሰባት ራሴን ካገለልሁ በኋላ ከዚህ ሰው ጋር ያለኝን ሰዋዊ ወዳጅነት ያለ ምክንያት ወይም የግንቦት ሰባት አባል ስለሆነ ማቋረጥ አለብኝ ብዬ አላስብም ነበር ። ስለዚህም የዛሬ ሁለት ሳምንት ከወዳጆቼ ጋር በሆቴሉ ሄደን ምሳ ለመብላት ( በቁጥር ስምንት ስለሆነን ) በቅድሚያ ወንበር ለመያዝ ደወልሁለት ። ምንም ችግር የለም አለኝ። ከሰዓታት በኋላ ደውሎ « ድርጅቴን ግንቦት ሰባትን ስለጎዳህብኝ አንተ ምግብ ቤቴ መጥተህ እንድትመገብ አልፈልግም !» የሚል መልስ ሰጠኝ ። በመጀመሪያ ሰውን በፖለቲካ አቋሙ አላስተናግድም ማለት የሚያስከስሰው ነገር እንደሆነ እንኳ በቅጡ የሚያውቅም ሰው አለመሆኑ ገረመኝ ፥ በሁለተኛ ደረጃ እዚህ ድረስ እስኪበሰብሱ ድርጅት ማፍቀራቸው አዘንኩላቸው ። ይህም ከወያኔ ማንነት ጋር ፍፁም አንድ ነው !
ዛሬ ድርጅቴን ስለተናገርክብኝ እቤቴ አትበላም ያለኝ ሰው ነገ ስልጣን ቢይዝ ፥ ሃገር መግባት አትችልም ስላለማለቱ ዋስትናው ምንድን ነው ! እንግዲህ ይህ ሰው ራሱ በሳን ሆዜ የኢሳት የገቢ አሰባሳቢ አካል ነው ። አሁን በዚህ ሰው መነፅር ኢሳትን እንድናይ የሚያደርጉን ግንቦት ሰባቶች ናቸው ! የኢሳትን ህልውና የሚፈታተን ርካሽ ነገር የሚፈፅሙትም ፥ ኢሳት ያገኘው ህዝባዊ ተቀባይነት በመጠቀም ፥ ከነሱ ጋር በ አልቦነታቸው ምክንያት የሚጋጨውን ( ወይም የሚጠይቀውን ) ሰው ሁሉ ግጭቱን ወደ ኢሳት እያዞሩ ፥ በቀጥታ ፀቡን ከኢሳት ጋር እንድናደርግ የሚያደርጉን !
ይህ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ወደፊት ልክ ዛሬ የግንቦት ሰባት ህልውና አደጋ ላይ እንደወደቀው ( ከስሩ እንደተሽመደመደ ) ሁሉ ፥ የኢሳትም ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም ! ትንቢት አይደለም ግን I can see it!
በቀጣይ ግንቦት ሰባት እንደ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ የጀመረው ነገር ፥ ሆድ አደር እና ምልምል የአማራ ልጆችን በማሳመን ፥ የአማራ ማህበር እየፈጠሩ ፥ አማራን እንዲሰበስቡ የማድረግ ስራ ነው ። ይህ ለግንቦት ሰባት ለጊዜው የሚፈልገውን የሰው እና የቁስ ሃይል ያመጣለት ይሆናል ፥ ኋላ ላይ ግን ማቆም እና መቋቋም የማይችለው ጉልበት ተፈጥሮ እነዚህ በስውር የተቋቋሙ የአማራ ሃይሎች ተገንጥለው እንደሚወጡ ለመገመት ብዙ ማወቅ አይጠይቅም ! ወያኔ ትግሬ በተለያየ ጥቅማ ጥቅም ብአዴን የሚባል ቡድን መስርቶ አማራውን ለመቆጣጠር የሄደበት መንገድ ፥ ዛሬ ለወያኔ ከፍተኛ ስጋት እና የውስጥ አርበኛ በመሆን የቁም ስቅሉን የሚያሳዩት እነማን እንደሆኑ ፥ እነማን መረጃ እንደሚሰዱልን የታወቀ ነገር ነው !
ባጭሩ ከግንቦት ሰባት ጋር የሚያስታርቁኝ ( እኔን እና የአማራ ወጣቶችን ማለቴ ነው ) የሚከተሉት ይሆናሉ ብዬ እገምታለሁ
1ኛ ግንቦት ሰባት አቅም የሌለው አየር ወለድ ድርጅት መሆኑን አምኖ የትግል ስልት ለውጥ ማድረግ
2ኛ አማራን ለስልጣን መወጣጫነት ለመጠቀም ከማሰብ እና አማራን አዚህ ደረጃ ከመናቅ መውጣት
3ኛ ስለ አንድነት እየሰበከ እራሱ በብሄር የተደረጃ ድርጅት ነውና ፥ ይህንን መዋቅሩን ቀይሮ ሁሉ አቀፍ ህብረ ብሄራዊ ማዕከላዊ መዋቅር ያለው ድርጅት ለመሆን መንገድ መክፈት
4ኛ ላምባልዋለበት ኩበት መልቀሙን ማቆም! የአማራ ትግልን የኔ ነው ብሎ መታበዩን መግታት
5ኛ ከምንም በላይ በህዝብ ገንዘብ የቆመውን ኢሳትን የህዝብ እንዲሆን መፍቀድ! ለድርጅት ተክለ ሰውነት ሲባል የኢሳትን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ተራ ጉንጭ አልፋ ፕሮፖጋናዳ በኢሳት እንዲሰራ ከማድረግ መቆጠብ
እና ሌሎች !
ኄኖክ የሺጥላ

No comments:

Post a Comment