Thursday, January 5, 2017

በአየር ኃይል አብራሪዎችና ቴክኒሺያኖች ላይ እርምጃ መወሰድ ተጀመረ By posted by ብርሃኑ አየለ




በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎች እና በቴክኒክሺያኖች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው።ገዢው ፓርቲ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ምድቦች ውስጥ በአካሄደው ግምገማ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ግንኙነት አላቸው ተብሎ በሚጠረጠሩ አባላት ላይ ከእስር እስከ ሥራ ማገድ እርምጃ እየወሰደ ነው።
በምስራቅ አየር ምድብ በተዋጊ ሄሊኮፕተር በረዳት አብራሪነት ተመድቦ የሚገኘው የመቶ አለቃ ገመቹ ሀሰን ከግምገማ በኋላ ከአየር አብራሪነት የታገደ ሲሆን የግምገማው መሪ የነበረው የአየር ኃይል ም/አዛዥ እና የዘመቻ ሀላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ማአሾ ሀጎስ ስሙን በመጥቀስ በረራ እንድታቆም የተደረገበትን ምክንያት ታውቃለህ ብሎ ሲጠይቀው መቶ አለቃም ገመቹም በንዴት አዎ አውቀዋለሁ የታገድኩበት ገመቹ ስለሆንኩ ነው ብሎ ምላሽ ሰጥቷል። ይህን ተከትሎ አብራሪው በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ከስራው ታግዶ ይገኛል።
በሌላ በኩል በምእራብ አየር ምድብ በተደረገው ግምገማ የሚግ 23 ጄትአብራሪ የሆነው የመቶ አለቃ መስራች እንዳለ በአማራ ክልል እየተካሄደ ከአለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር ግንኙነት አለህ በማለት እርምጃ ሊወሰድበት እንደሆነ ከአየር ኃይል ምንጮቻችን ገልፀዋል። መቶ አለቃ መስራች እንዳለ ላይ ስለሚወሰድበት እርምጃ ከፍተኛ የኃይል አዛዦች እየመከሩበት የሚገኙ ሲሆን እስከ አሁን ባገኘነው መረጃ መሰረት ውሳኔ እንዳልተሰጠበት ታውቋል።
ከዚህ በፊት ከማእከላዊ አየር ምድብ ተይዘዉ የታሰሩት 3 አብራሪዎች ከ2 አመት በላይ ተፈርዶባቸዉ ናዘሬት እስርቤት ይገኛሉ። በማዕከላዊ አየር ምድብ በተደረገ ግምገማ ላይ የአየር ሃይል አባላት ስለታሰሩት አብራሪዎች በማንሳት “እነሱ ያለጥፋታቸዉ ነዉ የታሰሩት፤ አየር ሃይሉ ያለምንም ምክንያት ሰዎችን እያሰረና እያባረረ ተቋሙን እየጎዳ ነዉ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ አመራሮቹ ማስተካከል አለባቸዉ” በማለት አባላቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአየር ሀይል አብራሪዎችና በስርአቱ ከፍተኛ የጦር አዛዦች መካከል ከፍተኛ የሆነ አለመግባባት እንዳለ ከአየር ሃይል ያሉ ምንጮቻችን ገልጸዋል። የአየር ሃይል አብራሪዎች ባለው የስራ ብልሹነት ምክንያት ስራዎች እየተስተጓጎሉ ነው በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ። ለስርአቱ ታማኝ ደጋፊዎች የሚባሉት አብራሪዎች ጥፋት ቢሰሩም እንኳን ተጠያቂዎች አይደረጉም።
በምስራቅ አየር ምድብ ማዘዣ በሆነው ድሬዳዋ አየር ሃይል ሶሰት ሄሊኮፕተሮችን በመግጨት ከባድ ኪሳራ በተቋሙ ላይ ያደረሰዉ ሌ/ኮ ፀጋ ዝአብ ካሳ የተባለ የሄሊኮፍተር አብራሪ በአሁኑ ሰአት ምንም እርምጃ ሳይወሰድበት በስራው ላይ ይገኛል። ተቋሙ እንደዚህ እይነት ከባድ ኪሳራ ባደረሱት አካላት ላይ እርምጃ ሳይወስድ በሌሎች አብራሪዎች ላይ አላግባብ የሚወሰዱ እርምጃዎች በአየር ሃይል አባላት ላይ ከፍተኛ የሆነ ቅሬታን እያስነሳ ነው።
ለአገዛዙ ታማኝ አይደሉም ተብለው በሚጠረጠሩ የአየር ሃይል አብራሪዎች ላይም ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment