Wednesday, August 2, 2017

ዶክተር መራራ ጉዲና ሁለት እጃቸውን ወደ ኋላ በካቴና ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ source abbay media

ታዋቂው ፖለቲከኛና የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር መራራ ጉዲና ሁለት እጃቸውን ወደ ኋላ በካቴና ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ።
በዘረፋ የታሰሩ እንዲሁም ነፍስ ያጠፉ ግለሰቦች ላይ የማይፈጸም ድርጊት ዶክተር መራራ ላይ መከሰቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ዶክተር መራራ ጉዲና ሁለት እጃቸውን ወደ ኋላ በካቴና ታስረው ፍርድ ቤት የማቅረቡ ርምጃ እሳቸውን በማዋረድ የደጋፊዎቻቸውን ቅስም ለመስበር ነው የሚለው የበርካቶች እምነት ነው። ርምጃው ደግሞ ቁጣን የሚቀሰቅስ መሆኑን የፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ይዘው የቆዩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፕሬዝዳንት ዶክተር መራራ ጉዲና በአውሮፓ ሕብረት ግብዣ ቤልጂየም ብራስልስ መገኘታቸውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰሃል በሚል መታሰራቸው ሲታወስ ቆይቶ ክሱ ወደ አሸባሪነት መለወጡ ይታወቃል።
ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያስተማሩትና ከዛሬ 40 አመት በፊት ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ተሳታፊና የለውጥና የመብት አቀንቃኝ የሆኑት ዶክተር መራራ ጉዲና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያለጊዜያቸው በጡረታ እንዲወጡ ያደረጋቸው ሲሆን አስፈላጊውን መመዘኛ አሟልተው የፕሮፌሰርነት ማእረግ እንደተነፈጉም ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።
ለረዥም ጊዜ ከኖሩበት ቤት መባረራቸውንም ተከትሎ አዲስ አበባ ጫፍ ላይ ተጀምሮ ወዳላለቀ ቤት መግባታቸውን ማስታውስ ተችሏል።
ዶክተር መራራ ጉዲና ሁለት እጃቸውን በካቴና ወደኋላ ታስረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 25/2009 እንደሆነም ታውቋል።
በነፍስ ማጥፋት፣በዘረፋ፣እንዲሁም በተራ ስርቆትም ሆነ በሌላ ወንጀል እንዲሁም በፖለቲካ ጭምር የታሰሩ በአብዛኛው በካቴና በማይታሰሩበት ሁኔታ እኚህን ታዋቂ ምሁርና ፖለቲከኛ በካቴና አስረው ፍርድ ቤት ያቀረቡበት ምክንያት አልታወቀም።

No comments:

Post a Comment