Friday, August 18, 2017

በወልድያ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰማn source mereja

በወልድያ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰማ
በወልድያ ተቃውሞ መቀስቀሱን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ በዛሬው ዕለት የወልድያ ህዝብ ‹‹አላግባብ የተጫነብኝን ግብር አልከፍልም፡፡›› ብሎ አሻፈረኝ ማለቱን ከስፍራው የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ከተማው ውጥረት ማርገዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ለአምስት ቀናት የስራ ማቆም አድማ ላይ የሰነበተው የወልድያ ህዝብ፣ በዛሬው ዕለትም ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ የህወሓት መንግስት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ የግብር ጫና መጣሉ አይዘነጋም፡
በሀገሪቱ ነጋዴዎች ላይ የተጫነውን የግብር ጫና ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ ተቃውሞ መቀስቀሱ የሚታወስ ሲሆን፣ ወልድያም ተቃውሞ ከተቀሰቀሰባቸው ከተሞች አንዷ ሆና ሰንብታለች፡፡ በዛሬው ዕለት ተቃውሞው በድጋሚ ማገርሸቱን የተናገሩት የከተማዋ የቢቢኤን ምንጮች፣ ህዝቡ ግብሩ ካልተቀነሰለት በቀር ለመክፈል ዝግጁ አይደለም ብለዋል፡፡ ምንጮቹ አክለውም ‹‹በግብር ስም ዘረፋ መፈጸም ተገቢ አይደለም፡፡›› ሲሉም የህወሓትን መንግስት የዘረፋ አዝማሚያ ተችተዋል፡፡
የከተማዋ ህዝብ ግብር አልከፍልም ማለቱን ተከትሎ፣ የፖሊስ ኃይሎች በከተማዋ መሰማራታቸውን የገለጹት ምንጮች፣ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስም ከተማዋ ውጥረት ላይ እንደነበረች ይገልጻሉ፡፡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ከተማዋ ጭር ብላ መታየቷን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መሸት ካለ በኋላ የፖሊሶች ቁጥር ጨምሮ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጥያቄአቸው እስካልተመለሰ ድረስ፣ የዛሬው ተቃውሞ በነገው ዕለትም ሊቀጥል እንደሚችል ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከግብር ጫና ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ከተነሳ በኋላ፣ መንግስት የግብር ቅነሳ ይደረጋል የሚል ማስተባበያ ቢሰጥም፣ በመጨረሻም ግን ውሸት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
BBN

No comments:

Post a Comment