Thursday, July 28, 2016

በጎንደር ብአዴን እና ሕዝቡ ያደረገው ስብሰባ ተጠናቀቀ

ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም ከሰሜን ጎንደር ሕዝብ የተወጣጡ ሽማግሌዎች ከብአዴን ባለስልጣናት ጋር ዉይይት ማድርጋቸው ይታወሳል። በዚህ ወይይት ሐምሌ 17 ቀን በጎንደር ሰልፍ እንደሚደረግ ሽማግሌዎች ባሳወቁት መሰረት የብአዴን ባለስልጣናት ሰልፉ ለ10 ቀናት እንዲራዘም መጠየቃቸውም ተዘግቧል።
ሰልፉ ለሐምሌ 24 ቀን እንዲሚደረግ ዘገባዎች በስፋት እየጠቆሙ ሲሆን አቶ በረከት ስምኦንን እና የክልሉ አስተዳዳሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ያካተተ የብአዴን አመራር ከሕዝቡ ጋር በጎንደር ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት መወያየታቸዉንም ለማወቅ ተችሏል።
ከስፍራው የደረሱ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በስብሰባው የሕዝቡን አቋም ያንጸባርቁ የነበሩ ሲሆን፣ አቶ በረከትም ከሕዝቡ የተነሱ ብሶቶችና ጥያቄዎችን በማስታወሻ ደብተራቸው ላይ ማስፈራቸዉን ጠቁመዋል። አቶ በረከት የሕዝቡን ጥያቄ ይዘው እንደሚቀርቡና ተመልሰው መጥተው ለሕዝቡ ሪፖርት እንደሚያደረጉም ቃል ገብተዋል። “አንድ ደብተር ሙሉ ጥያቂያችሁን ፅፌ ይዤያለሁ ፣ ለሚመለከተው አካል ወስጄ አንድም ሳልቀንስ አቀርብና እንወያይበታለን። ከዛ መልሱን ይዤ ወደ እናንተ ተመልሼ እመጣለሁ” ነበር ያሉት።
ሕዝቡ ጌታቸው ረዳ የተባለው ግለሰብ እና ኢቢሲ በአማራው ክልል ህዝብ ላይ ሲያሾፉና ስድብ ሲዘነዝሩ እንዴት ዝም ብላችሁ ታያላችሁ ሲሉም የብአዴን አመራር አባላትን አፋጠዉም ነበር። “ እንዴት ጌታቸው ረዳ የተባለ ጅል የአማራው ክልልን ህዝብ ሲሰድብ ዝም አላችሁ? እንዴት ብትንቁን ነው ይህን ትንሽ ሰው ሚኒስትር አድርጋችሁ የሾማችሁብን? ..” የሚሉት በጌታቸው ረዳ ላይ ከቀረቡት አቤቱታዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ነበሩ። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጌታቸው ረዳና በኢቢሲ ሲቀርቡ የነበሩ ዘገባዎች አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸው ሕዝቡን በአሰቸኳይ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን ፣ አቶ በረከትም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ላይ እየቀረበ ያለው ነገር ብዙ እንደማይጥማቸው ለሕዝቡ ገልጿል።
ሌላው የብአዴን አመራር አቶ ብናልፍ አንዷለም የተባሉኢ ግለሰብ ሲናገሩ ላዳመጠ የትግራዩ አባይ ወልዱ የሚናገር ነበር የሚመስለው። የክልሉን ህዝብ እንደሚወክሉ ፖለቲከኛ ሳይሆን በጥቅም የተገዙ፣ የለየለት የህወሃት ካድሬ መሆናቸዉንም ነበር ያረጋገጡት። እንደ ወንበዴ በሌሊት መጥቶ ዜጎችን ለማፈን የተንቀሳቀሰውን አሸባሪ ቡድን በማሞገስ ” የፌድራል ፖሊስ ህጋዊ ነው…” የሚል የመሳሰሉትን ፍሬከርስኪ አስተያየት ለመስጠት ሲሞክሩም በተሰብሳቢው ጩኸት ንግግራቸው በተደጋጋሚ ተቋርጧል። ሰዉዬ በተናገሩ ቁጥር ሕዝብ እያስቆማቸው ምናምንቴ ነበር የሚመስሉት።
ከሕዝቡ ይሰጡ ከነበሩ አስተያየቶች መካከል፡
“ ይሄን ሁሉ ግፍ በሰፊ ትዕግስታችን ችለን ተቀምጧል ።አሁን ግን ትግስታችን ተንጠፍጥፎ አልቋል”
“ ህወሓት አንዳች እርምጃ እወስዳለሁ ብትል የሚመጣው አፀፋ የከፋ እንደሆን የጎንደር ሕዝብ መልክቱን በብአዴን በኩል ልኮላታል”
“ የህወሓት የበላይነት እስከ መቼ? ከአሁን በኋላ ኢህአዴግ አብቅቶለታል ፣ ኢህአዴግ የጎንደር እናቶችን ደም እምባ ያስነባውን የመላኩ ተፈራን ስራ በሕወሓት አማካኝነት በጎንደር ሕዝብ ላይ ደጋግሞ እያደረገው ነው “
“ወንድሞቻችንን ከወልቃይት ገፍታችሁና አባራችሁ፣ ጎንደር መጠው ቢጠጉ፣ ህዝብን ንቃችሁ አፍናችሁ ወስዳችሁ ፣ ህወሓት የጎንደር ሕዝብን በደንብ ታውቀዋለች እንግዲህ ይለይልናል ፣ “
ይገኙበታል።
ለ10 ቀናት ተላልፎ የነበረዉና እሁድ ሐምሌ 24 ቀን በጎንደር ክተማ ይደረጋል ተብሎ የታቀደው የሰላማዊ ሰልፍ ነገር፣ እነ በረከት በተገኙነት ስብሰብ ላይ ሳይነሳ ስብሰባው ተበትኗል። በእርግጥ ሰላማዊ ሰልፉ በታቀደለት ቀን እንደሚካሄድ ሕዝቡ የስማ እንደሆነ ከጎንደር የሚደርሱ መረጃዎች ሲጠቁሙ፣ በሶሻል ሜዲያም ቅስቀሳዎች በስፋት እየተደረጉ ነው።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሕዝቡ ወገን መሆናቸዉን አስመስክረዋል። አቶ በረከትም በርጋታና በአክብሮት ነበር ሕዝቡን ሲያዳምጡ የነበሩት። ምን ያህል ሕዝቡ እንዳከረረ በመረዳታቸው አቶ በረከት አዲስ አበባ ያሉ ጓደኞቻቸውን አሳምነው መሰረታዊ የፖለቲክ ለዉጥ እንዲመጣ በመጨረሻው ሰዓት የድርሻቸዉን አዎንታዊ ሚና ይጫወቱ ይሆናል የሚል ግምት ያላቸው ጥቂቶች ቢኖሩ፣ አቶ በረከት የተላኩት ጊዜ ለማራዘም እና ህዝቡን ለማዘናጋት ነው የሚለው አስተያእይት ግን አይሎ የሚሰማ አስተያየት ነው።
በኦሮሚያ የተነሳው ቀዉስ፣ ሰሞኑን የቀድሞ የሕወሃት ጀነራሎች ያቀረቧቸው ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎች ተደምረው፣ በኢሕአዴግ ዉስጥ ለዉጥ እንዲመጣ የማይፈለገውን አክራሪ ቡድን ወደ ጎን ተገፍቶ፣ ፔሪስትሮይካ በኢትዮጵያ እንዲመጣ የሚረዳ ሃይል ከኢሕአዴግ ዉስጥ ይወጣ ይሆን ? በቅርብ የምናየው ይሆናል። አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው፤ ጨዉ ለራስህ ስትል ጣፍጥ እንደተባለው አራት ኪሎ ያሉ ባለስልጣናት ለራሳቸው ያስቡበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

No comments:

Post a Comment