Tuesday, October 31, 2017

በህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት ብሶበታል ተባለ source zehabesha



በህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት እየባሰበት እንደመጣ ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ፓርቲው አጣብቂኝ ላይ በወደቀበት በዚህ ሰዓት፣ ባለስልጣናቱ የተለያየ አስተሳሰብ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ህዝባዊ ንቅናቄ በፓርቲው አመራሮች ዘንድ የሚወሰነውን ውሳኔ ጉራማይሌ እንዲሆን እንዳደረገው የጠቆሙት ምንጮች፣ ፓርቲው ትልቅ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል፡፡ ፓርቲው ከፍተኛ መናጋት እና ክፍፍል እየገጠመው እንደመጣ ከዚህ ቀደም ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮችን ለሁለት ከከፈሉ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የፖለቲካ እስረኞችን የተመለከተው እንደሆነ ታውቋል፡፡
በተለይ በፖለቲካ ጉዳይ የታሰሩ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን መፍታት በኦሮሚያ ክልል ለተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ እንደ ማብረጃ ይጠቅማል ብለው ያሰቡ የፓርቲው አመራሮች፣ እስረኞቹ እንዲፈቱ ሀሳብ ማቅረባቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በሌላ ወገን ያለው አመራር ግን አንደኛው አመራር ያቀረበውን ሀሳብ እንደማይቀበለው መግለጹን ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ በአንደኛው ወገን ‹‹ከመሬት ተነስቶ የፖለቲካ እስረኞቹን መፍታት ከባድ ሽንፈት ነው የሚያስከትልብን›› የሚል አመለካከት የያዘ ሲሆን፣ በሌላኛው የፓርቲው ወገን ደግሞ፣ ‹‹እስረኞቹን መፍታት ከመጣብን መዓት አይበልጥም፡፡›› የሚል አመለካከት መኖሩንም ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በተለይ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች በፖለቲካ ጉዳይ የታሰሩ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን መፍታት፣ በኦሮሚያ የተፈጠረውን ቀውስ በመጠኑም ቢሆን ሊያበርደው ይችላል የሚል አቋም የያዙ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች፣ ሃሳባቸው የበላይነት እየያዘ እንደመጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም እስረኞቹን በነጻ ከመልቀቅ ይልቅ፣ ጉዳዩ የፍርድ ሂደቱን የተከተለ እንዲመስል በዋስ መልቀቁ እንደሚሻል በአንደኛው የፓርቲው ወገን ስምምነት ላይ መደረሱን የቢቢኤን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዛሬው ችሎቱ፣ አቶ በቀለ ገርባን በዋስ የፈታበት ምስጢርም አንደኛው የህወሓት/ኢህአዴግ አመራር ቡድን በደረሰበት ስምምነት መሆኑን የሚገልጹት መረጃዎች፣ በቀጣይም ከኦሮሞ ፖለቲከኞች ውስጥ ከእስር ሊፈታ የሚችል ሰው እንደሚኖር ከወዲሁ ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም በቀጣይ ማን ከእስር እንደሚፈታ ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

No comments:

Post a Comment