Tuesday, October 24, 2017

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ዶክመንተሪ ፊልም ሊሰራ ነው

የገዥው ፓርቲ ልሳን የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዶክመንተሪ ፊልም ሊሰራ መሆኑን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ዶክመንተሪው የሚያተኩረው ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተካሔዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ሲሆን፣ ፊልሙ ህዝቡ ያነሳውን የነጻነት ጥያቄ ሌላ መልክ ሰጥቶ ጥላሸት የመቀባት ዓላማ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የገባው የህወሓት መንግስት፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የሚገኘው የብሔረሰቦች አብሮ የመታገል ሁኔታ በእጅጉ እያስፈራው እንደመጣ ይነገራል፡፡ ቡድኑ ይህን ሁኔታ ለመሰባበር ወይም የአንድነቱን ጉዞ ለማሰናከልም ደፋ ቀና እያለ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ህዘቡ የመብት ጥያቄውን እያቀረበ የሚገኘው በግልጽ እና በማያሻማ መንገድ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በኩል ሊሰራ የታቀደው ዶክመንተሪ ፊልም ግን፣ አንዱ ብሔር በሌላው ላይ በጠላትነት እንደተነሳ ተደርጎ ለማቅረብ ታቅዷል፡፡ ለዚህ ዓላማ ሲባልም አስቀድሞ በሰልፎች ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ተደርገው፣ ሰልፉ ሌላ ዓላማ ያነገበ እንዲመስል ጥረት እያደረጉ ያሉ ካድሬዎች መኖራቸው ታውቋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ በተደጋጋሚ በሰጠው መግለጫ፣ ሰልፎቹን ወደ ሁከት ለመቀየር ሲሞክሩ የነበሩ ሰዎች ተያዙ የሚል ቃል ሲደጋግም ቆይቷል፡፡ ይህም የፊልሙ አንድ ግብዓት መሆኑንም የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡
የተቃውሞ ሰልፍ በተካሔደባቸው የኦሮሚያ ከተሞች፣ ቪዲዮ ካሜራ የያዙ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሰራተኞችን መመልከታቸውንም የዓይን እማኞች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በየከተሞቹ የተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችን ቀርጾ ያስቀመጠው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን፣ በቀጣይም ሁከት ተነስቶባቸዋል በተባሉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በመመስረት አዲስ ፊልም ሊሰራ ማቀዱን ከመረጃዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ቴሌቭዥን ጣብያው ከዚህ ቀደም የተለያዩ አካላትን እና ሰዎችን ስም ለማጥፋት ዶክመንተሪ ፊልም ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ጣብያው ምንም እንኳን ፊልም የመስራት አባዜ ቢኖርበትም፣ የሰራቸው ፊልሞች ግን አንድም ቀን በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው እንደማውቁ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment