Thursday, October 26, 2017

የሰው ሕይወት የተቀጠፈበት የአምቦ የተቃውሞ ውሎ በቢቢሲ ዘገባ source zehabesa

በግጭቱ ቢያንስ 10 ሰዎች እንደተገደሉ የአይን እማኞች ይናገራሉ
(Photo credit – BBC)
ስለአምቦው ውሎ የቢቢሲ ዘገባ እንደወረደ:-
በስልክ ያነጋገርናቸው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች እንደነገሩን ስኳር ጭነው በከተማው የሚያልፉ መኪኖች እንዳሉ መረጃ ለአካባቢው በመድረሱ ፤ መኪኖቹን ለማስቆም በመጠባበቅ ከትናንት ጀምሮ መንገድ መዝጋት ጀምረው ነበር።
ምክንያታቸው ደግሞ በሀገሪቱ የሚታየው የስኳር እጥረት በአምቦም የሚስተዋል መሆኑ ነው።
በከተማዋ አንድ ኪሎ እሰከ 70 ብር ድረስ ይሸጣል ይላሉ።
እናም በዚህ ሁኔታ ስኳር ተጭኖ ወደሌላ ቦታ መሄዱን በመቃወም ነው መንገድ መዝጋት የጀመሩት።
” ከተማዋን አቆርጠው የሚሄዱ ዋናና መጋቢ መንገዶች በመዘጋታቸው የክልሉ ፖሊስና እኛ ሆነን በህገወጥ መንገድ ሊያልፍ የነበረውን ስኳር ስንጠብቅ አድረናል”ይላሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለገ አንድ የአካባቢው ነዋሪ።
ዛሬ ግን ከማለዳው አንድ ሰዓት አካባቢ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት መለያ የለበሱ በተቃዋሚዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸውን ተናግሯል።
“እኔ በአይኔ ያየሁት አምስት ሰዎች ሲገደሉ ነው።ግን የሞቱት በጣም በርካታ ሰዎች ናቸው” ያለን ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ነው።
” ሁለት የፌደራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ በድንጋይ ተደብድበው እንደሞቱ አይቻለሁ” ብሎናል።
ቢቢሲ ግን የሟቾቹን ትክክለኛ ቁጥር ለማረጋገጥ አልቻለም።
ከግጭቱ ጋር ተያይዞ በንብረት ላይም ጉዳት የደረሰ ሲሆን የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ንብረት የሆኑ ሁለት የጭነት መኪናዎች ተቃጥለዋል።
በከተማዋ ስኳር እንዳይዘዋወር መንገዶች እንዲህ ተዘግተዋል
የአሮሚያ ክልል የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስ ቡክ ገጻቸው የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በሌሎች ሰዎች ላይም የአካል ጉዳት መደረሱን የሚገልጽ መረጃ አስፍረዋል።
” ከሰላማዊ ሰልፍና ከስኳር ፍተሻ ጋር በተያያዘ ወጣቶችን በማነሳሳትና ስርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ በማድረግ ለግጭቱ መንስዔ የሆኑትን አካላት እናወግዛለን” ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት ከተማዋ በአንጻራዊነት የተረጋጋች ትመስላለች፤ ነገር ግን መንገዶች እንደተዘጉ ሲሆን ሰልፈኞቹም ወደየቤታቸው አልተመለሱም።
ከዚህም የተነሳ ብዙዎች አሁንም ተጨማሪ ጉዳት ሊደርስ የሚችል ስጋት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment