
የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እንደገለጸው በዚህኛው ወር ከፍተኛ የዋጋ ንረት ከታየባቸው ምርቶች መካከል፣ ፍራፍሬዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ሙዝና አቮካዶ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች ከፍተኛ የዋጋ ንረት ታይቶባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስኳር እና ቡና በዚህ ወር አስደንጋጭ የዋጋ ንረት አስመዝግበዋል፡፡ በተለይ ስኳር እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የተደረገበት ሲሆን፣ አንድ ኪሎ ስኳርም እስከ መቶ ብር ድረስ መሸጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንዲሁም ቡናም በተመሳሳይ ሁኔታ በጥቅምት ወር አሳሳቢ የዋጋ ንረት አስመዝግቧል፡፡
ከአትክልት ደግሞ ቲማቲም፣ ካሮት እና ድንች የሚፋጅ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአትክልት ተራ፣ በመርካቶ እና በሌሎች የአዲስ አበባ ትላልቅ የገበያ ስፍራዎች በአትክልት ዋጋ ላይ አስደንጋጭ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ከጥራጥሬ እህሎች ደግሞ በጤፍ፣ ስንዴ እና በቆሎ ላይ መጠነኛ ጭማሪ መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ለደሃው ብቻ ሳይሆን፣ አለው ለሚባለው የህብረተሰብ ክፍልም እጅግ ፈታኝ ደረጃ ላይ መድረሱ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ በፍጆታ ምርቶች ላይ በየወሩ እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀሳብ ላይ ጥሎታል- እንደ መረጃዎች ገለጻ!
No comments:
Post a Comment