Thursday, June 29, 2017

የሕወሓት የስንብት ዐዋጅ (ምሕረት ዘገዬ) source ecadef

ምሕረት ዘገዬ
ሰሞነኛው ሕወሓታዊ  የዕውር ድምብር እንቅስቃሴ ብዙ ነገሮችን እንዳስታውስ አድርጎኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህንን አዲስ አበባን ለኦሮሞ የመስጠት ጉዳይ በዩቲዩብ ስመለከት ከመደንገጥም አልፌ ከሦስት ቀናትም በኋላ አሁን ድረስ ላልተወኝ ራስ ምታት መጋለጤን ልደብቅ አልፈልግም፡፡ የዕብድ ሥራም አንዳንዴ ያስደነግጥና እስኪለቅ ድረስ መቸገር ይኖራል፡፡ የድንጋጤየ ዋና መነሻ የወያኔው ዕብደት የወለደው ይህ ሕዝብን የማተረማመስ ሥልት ከቁም ነገር የሚጣፍ ሆኖ ሣይሆን ከወኔያው ታሪክ በመነሣት ብዙ “አይሆኑም” የሚባሉ ነገሮች በመሆናቸው እነዚህ ውሉዳነ አጋንንት የቆይታ ዕድል ካገኙ ይህም ቅዠት እውን ሊሆን እንደሚችል በመጠራጠር ነው፤ “ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር” ይባላልም እኮ፡፡ እንጂ እንዲህ ያለ ዘመኑን ያልዋጀ የዕብደት ዐዋጅ ኢትዮጵያን ያሰጋታል ብዬ ከልቤ አምኜበት አይደለም፡፡(በነገራችን ላይ ኤርምያስ ለገሠ በዚህ ነገር ዙሪያ የጻፈው ግሩም ወቅታዊ  ሀተታ አለና ያላነበበ ሰው ቢያነበው ጥሩ ነው እላለሁ፡፡)
ይህ ክስተት ከሚያስታውሱኝ በጣም በርካታ ነገሮች ውስጥ አንድ ሁለቱን ያህል ላስታውሳችሁ፡፡
ከምድራዊው ልጀምር፡፡ በትዳር ሕይወቷ ብዙ ልጆችን ያፈራች አንዲት የቤት እመቤት በጠና ትታመምና ንስሃ ለመግባት በዚያውም የኑዛዜ ቃሏን በእማኞች ፊት ለመስጠትና ይህችን “ቆሻሻ” ምድር ለመሰናበት ሁለት ሽማግሌዎችንና የነፍስ አባቷን ታስጠራለች (አሉ)፡፡ የተባሉት ሰዎች መጥተው ያችን እንደወያኔ በፅኑ ጣዕር ወህማም ላይ የነበረችን ሴትዮ በመክበብ ማዳመጥ ይጀምራሉ ፡፡ የአሥራ አንድ ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ በቅድሚያ ንስሃዋን ማውረድ የፈለገች ይመስላል፡፡ እናም ቀጠለች – “መምሩ ደህና አድርገሁ ይፍቱኝ፤ በደምብ ይጸልዩልኝ፡፡ በቁርጥ ስለተያዝሁ እውነቱን ብቻ ነው የምናገረው፡፡ ለትዳሬ ታማኝ አልበርሁም፡፡ … የመጀመሪያው ልጄን የወለድሁት ከጎረቤታችን ከአቶ አውግቼው ነው፤ ሁለተኛውን ልጄን የወለድሁት ከአጥቢያ ዳኛው ከአጋፋሪ እንደሻው ነው፤ ሦስተኛውን ልጄን የወለድሁት ከባለቤቴ ነው፤ አራተኛውን ልጄንም የወለድሁት ከራሱ ከባለቤቴ ነው፤ … አምስተኛውን ልጄን የወለድሁት ከርስዎ ከራስዎ ከመምሩ ነው፡፡…” ሴትዮዋ አልጨረሰችም፤ የሕወት ድርሣኗን ከፍታ እውነትና እውነቱን ብቻ እየተናዘዘች ነበር፡፡ ሴትዮዋ በመጨረሻ የተናገረችውን ያልሰሙ በመምሰልና ለማመንም በመቸገር ጭምር ሽማግሎቹ ተደናግጠው “ምን አለች፣ ምን አለች?” ብለው እርስ በርስ ይጠያየቃሉ፡፡ ይህችን ጠባብ ዕድል ያገኙት የንስሃ አባት “ኧረ ገና ብዙ ትዘባርቃለች!” በማለት ሰዎቹ በቄሱ ላይ ያሳደሩትን ጥርጣሬን የተሻገረ የውስልትና ሥራ ለማስቀየስ ይሞክራሉ፡፡ ይህን ለማለት ያበቃቸው አለሥራቸው ታምተው ሣይሆን “ሴትዮዋ በጣር ስላለች የምትለውን አታውቅም” ለማለት ፈልገው ነው፡፡ አለቃ ገ/ሃናም ያመለጣትን እውነተኛ ፈስ እንዳልፈሳች ለማስመሰል ስትል በአፏ “ጡጥ!” ያደረገችዋን መንገደኛ “ይቺ ሌላ፣ ያቺ ሌላ” ሲሉ እንደነቁባት መግለጻቸውን እዚህ ማስታወስ ሳይገባኝ አይቀርም፡፡ የምትደበቅ እውነት እንደጭስ ናት – እንደምንም ብላ መውጣቷ አይቀርም፡፡
ለማንኛውም ወያኔ ገና ብዙ ይዘባርቃልና በጥንቃቄ መከታተል ተገቢ ነው፡፡ እነሱ ፈንጂ ባጠመዱ ቁጥር፣ እነሱ ወጥመድ በዘረጉ ቁጥር፣ እነሱ ጉድጓድ በቆፈሩልን ቁጥር እየዘለልን የምንገባ ከሆነ ስህተቱ የኛ እንጂ የነሱ አይደለምና በሚያልፍ መጥፎ ዘመን የማያልፍ ጠባሳ በታሪክ ስንክሳር ላይ ላለመተው ብዙ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን እኛ ብዙኃኑ ነን፡፡ እመለስበታለሁ፡፡
ሰማያዊውን ልቀጥልና ወደ ቁጭቴ(ማጠቃለያየ) ላምራ፡፡ በክርስትናው እምነት እንዲህ ያለ ታሪክ አለ፡፡ መላእክት ፈጣሪን ቅዱስ እግዚአብሔርን በመንበሩ ያጡታል፡፡ ይደናገጣሉ፡፡ ያኔ የመላእክት አለቃ የነበረው ሊቀ ሣጥናኤል የመላእክቱን መደናገጥና የተፈጠረውን ክፍተት በመረዳት በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ሄዶ ይቀመጣል፡፡ ዱሮም ይቀና ነበር ማለት ነው፡፡
መላእክቱ “ማን ነው የፈጠረን?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሊቀ ሣጥናኤልም “እኔ ፈጠርኳችሁ!” ይላቸዋል፡፡ ያመኑት አመኑ – በርሱም “ቆርበው ዳኑ”፡፡ ያላመኑት ግን “ፈጣሪያችንን እስክናገኝ በያለንበት (በጽናት) እንቁም!” ብለው ይወስናሉ፡፡ በወቅቱና አሁንም ቢሆን በኃያልነቱና በእልኸኝነቱ የማይታማው ሊቀ ሣጥናኤል እንደተነቃበት ሲረዳ እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ/ጦርነት ውስጥ ይገባና በየዋህነትም ይሁን በክፉ መንፈስ ተነድተው ፈጣሪያቸውን የካዱ መሰል መላእክት ጋር በመሆን በዓላማቸው ጸንተው ለፈጣሪያቸው ከቆሙት እነቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ጋር ክንፋቸውን እየተነጫጩ በጨበጣ ይተጋተጉ ያዙ፡፡ በዚያ ታላቅ መንፈሣዊ ጦርነት እግዚአብሔር ባይደርስላቸው ኖሮ አሁን ዓለማችንን በታላቅ ግዳይነት አጋድሞ እየተጫወተባት የሚገኘው ሊቀ ሣጥናኤል ሊያሸንፋቸው ተቃርቦ እንደነበር የሃይማኖት አባቶችና መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ ግን ያቺ የፈተና ጊዜ አልፋ ዳፋዋ ግን ለአዳምና ሔዋን ደርሳ በነሱም ሳቢያ ወደኛ ተላልፋ ይሄውና በሕወሓት አማካይነት ሌላ ኢትዮጵያዊ የመጨረሻ ፍልሚያ ውስጥ ገብተናል፡፡
አንደናገጥ፡፡ ብዙ ሰው የተደናገጠ ይመስላል፡፡ ብዙ ሰው ደግሞ እንደቀልድ እያዬ ይዝናናበት ጀምሯል፡፡ እንዳንደናገጥ የምመክረው ወያኔ ካርዶቹን ሁሉ አሟጦ ተጠቅሞ( አብዛኛውን በድርቅናና ሳናምንለት ነው) እዚህች የማትረባ ካርድ ላይ በመድረሱና ይህችም ካርድ እርባናቢስ በመሆኗ ነው፡፡ ወያኔና እግዚአብሔር፣ ወያኔና የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ወያኔና እውነት፣ ወያኔና ሰብኣዊነት… በቅጡ ሳይተዋወቁ እነዚህ እርጉሞች ሊሰናበቱ መቃረባቸው ግን በእውነቱ ያሳዝነኛል – “ሰው”ነትን አውቀውና ሆነውም ቢያዩት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከጉርምስና እስከ ጉልምስና፣ ከወመሽነት እስከ ጅጅትና ፈጣሪንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ማወቅ አለመቻል የአለመታደል ሁሉ ጫፍ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የዐዋጅ ጋጋታም አንዱና ምናልባትም ትልቁ የድንቁርናቸው ምልክት ነው፡፡ አንድ ሰው እየሞተ እንኳን ልብ ካልገዛና ወደሰውነቱ – ወደኅሊናው ካልተመለሰ – በስም እንጂ በግብር ሰው መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ለምሣሌ ወያኔዎች አዲስ አበባ እንደገቡ ሰሞንና ከዚያም በኋላ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፉትን የጥቁር አንበሣ ጄኔሬተር፣ የጎንደር ከተማ (ሆስፒታል?) ጄኔረተር፣ የአዲስ አበባ ዳቦ ቤቶች(ከኤርምያስ ሁለተኛው መጽሐፍ እንዳነበብኩት፣ በቢሊዮኖች ብር የሚገመት የመንግሥትና የግል ድርጅቶችን ሀብትና ንብረት … ቢቻል መመለስ ባይቻል መጸጸትና ለመካስ መሞከር ካልቻሉ በርግጥም እንደተወለዱ ሞቱ ሊባሉ የሚገባቸው የሰው ጭንጋፍ ናቸው፡፡ ይህን የቤት ሥራ ለትግራይ ክፍለ ሀገር ብንሰጥ የምንችል ይመስለኛል፡፡
አዲስ አበባ መተተኛ ከተማ ናት፡፡ አዲስ አበባ ልትለውጣቸው ያልቻለቻቸው ሕወሓትን የመሰሉ የጨለማው መንግሥት ወኪሎችን እንጂ ተራ ዜጋን በደቂቃዎች ውስጥ ለውጣ ክፉዎችን ገር፣ ተንኮለኞችን የዋህ የምታደርግ ግሩም ከተማ ናት፡፡ አንድ ሰው ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ይምጣ፣ የትኛውንም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ይናገር አዲስ አበባ ሲደርስ አዲስ አበቤ እንጂ ጎጃሜ ወይም ሸዌ፣ ወሎዬ ወይም ጎንደሬ፣ ወለጌ ወይም ሐረሬ … አይሆንም፡፡ ለልጆቿ ልዩ ፍቅር ያላት፣ ገዢዎች ጣልቃ እስካልገቡባት ድረስ በተቻላት መጠን ሁሉንም ልጆቿን በእኩል ዐይን የምታይ፣ ልዩ መስተጋብር ያላት፣ ልዩ የመቻቻልና የመደጋገፍ፣ የመተሳሰብና የመተዛዘን መንፈስ ያረበበባት በውነትም ልዩ ከተማ ናት – የኔ አዲስ አበባ፡፡ ሁሉንም ሆና፣ ስለሁሉም ተጨንቃና ተጠባ የሁሉንም ስሜት ገዝታ ከክፉዎቹ ገዢዎቿ መዳፍ ምሥኪን ልጆቿን ጠብቃ የምትኖር ከተማ ከአዲስ አበባ ውጪ ብዙም አላውቅም፡፡
አንድ ወቅት እንዲህ ሆነላችሁ፡፡ አንድ ሽማግሌ ከሰሜን ሸዋ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡበት የፍርድ ቤት ሙግት ነበራቸው፡፡ ቀጠሯቸው እየተራዘመ ሲሄድ አንድ ችግር ገጠማቸውና ለችሎቱ አቤት አሉ፡፡ “ክቡር ፍርድ ቤት፣ ውኃየ አልቆብኛልና በእግዜር ይሁንባችሁ ዛሬ ፍረዱልኝ ወይም ፍረዱብኝ!” ብለው ያመለክታሉ፡፡ የመሃል ዳኛውም “የምን ውኃ ነው ያለቀብዎት?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ እርሳቸውም “‹የአዲስ አበባ ውኃ አይለቅም‹ ሲባል ሰማሁ፤ ቤት ንብረቴን የትሚናቸውን ጥዬ እዚሁ መቅረት ስላልፈለግሁ የምጠጣውን ውኃ ታገሬ ተመንዝ ነው ይዤ የመጣሁት፡፡ የዚህን አገር ውኃ እዚሁ እንዳያስቀረኝ በመፍራት አልጠጣም፡፡…” አዎ፣ ዳኞቹ ተሳስቀው ወዲያዉኑ ወሰኑላቸው ይባላል፡፡ አዲስ አበባ ፍቅሯ እስከዚህ ነው፡፡
የአዲስ አበባን ባለቤትነት እንኳንስ ሕወሓት ዋና አዛዡ ዲያብሎስም አያገባውም፡፡ እንኳንስ ተላላኪው ሕወሓት የርሱ አለቆች ነጫጭባዎቹም አያገባቸውም፡፡ ይህች ታሪካዊት ከተማ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት እንጂ፣ የአፍሪካውያን የጋራ ንብረት እንጂ፣ የዓለማችን ሕዝብ የወል ገንዘብ እንጂ ከ90 ጎሣና ነገድ ለአንዱ ወይ ለሌላው በገጸ በረከትነት የምትሰጥ ቁስ አካል አይደለችም፡፡ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ …. የለም … የለም… ተረቱ ልክ አይደለም – ባይሆን “በሰው ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” ቢባል ይሻላል፡፡ ለማንኛውም ወያኔዎች ስለተጨነቁ አይደለም እንዲህ ያደረጉት፡፡ ወያኔዎች ይህን ያደረጉት በተለይ ኦሮሞንና አማራን፣ በአጠቃላይ ደግሞ ኦሮሞንና ሌላውን ኢትዮጵያዊ ለማባላት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተበላ ዕቁብ ው፡፡ አንዳንድ ጅላጅሎችና ወያኔ-ተከል መሠሪዎች ግን እዚህና እዚያ እንደማይጠፉ መጠቆም ብቻ ሣይሆን በርግጠኝነት እንዳሉ ተረድተን ምንም ኃይልና ጉልበት ሳናባክን በጥርሳችን ብቻ እየሳቅንባቸው ቀኒቷን እንጠብቅ፡፡ እኛ ግን አደራችሁን በከፍተኛ ደረጃ እንጠንቀቅ፡፡ “እንዲህ ልጠግብ በሬየን አረድሁ” እንዳለችው ነፈዝ ሴት ላለመሆን የምንሠራውንና የምንሆነውን እያሰብን እንሥራ፣ እንሁንም፡፡ ሲያልፍ ለሚቆጭ ነገር እንዳንዳረግ እንትጋ፡፡
የኢትዮጵያ ነፃነት አንድ ቦታ እየተሠራች ነው፡፡ ያገሬ ገበሬ “ሳለ ፈጣሪ አሟጠሸ ጋግሪ!” የሚለው በፈጣሪው ዕፁብ ድንቅ ተዓምራዊ ሥራ ስለሚተማመን ነው፡፡ ስለዚህም በሰብኣዊ የውሱንነት ባሕርይ ምክንያት የመምጫዋን ጊዜና የምትመጣበትን አቅጣጫ ለይቼ ማወቅ ባልችልም ነፃነታችን እጅግ ቀርባለች፡፡ ንፋሷ አልባብ አልባብ በሚለው መለኮታዊ መዓዛው እያወደኝ ነው፡፡…
እመለስበታለሁ ወዳልኩት ነገር ልመለስ፡፡ ወገኖቼ! “ዐይጥ ወልዳ ወልዳ ጅራቷ ሲደርስ ሲጥ አለች” ይባላል፡፡ “ጦም ጧሚና ሰው ጠባቂ” ሲባልም ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ ያልተነካካችሁ፣ የሰው ላብ፣ የሰው ደም፣ የሰው ሃቅ… የሀገርና የወገን ዕንባ… በእጃችሁ የሌለባችሁ ወገኖች ይበልጥ ተጠንቀቁ፡፡ በነፃነት ቀን የምናፍርበት መጥፎ ሥራ ይዘን እንዳንዋረድ አሁኑንና ከአሁኑ እውነተኛ ንስሃ እንግባ፡፡ ሀገራችን ስትፀዳ የሚወጣ ዕድፍና ቆሻሻ ይታየኛል፡፡ ከቤተ መንግሥት ተጠራርጎ የሚጣል እጅግ የሚገማና የሚሰነፍጥ ቆሻሻ ይታየኛል፡፡ ዲያቆናት፣ ደባትር፣ ካህናትና ጳጳሣት ከየቤተ ክርስቲያናት እንደቁንጫና ትኋን በፍሊት ተጠራርገው ሲወገዱና ዲያብሎስ በነሱ ውስጥ ሲወገር ይታየኛል፡፡ ቤተ እግዚአብሔርን መጫወቻና መሣቂያ መሣለቂያ እንዳደረጉት ሁሉ ማጣፊያው ለሚያጥራቸው መከራና ስቃይ ይዳረጋሉ፤ ያም ቀን ቀርቧል፡፡ በቤተ ክርስቲያናት አካባቢ የሚደረጉ ወንጀሎችንና ነውሮችን በሚመለከት ዝርዝሩን ብንናገር ቤተ ክርስቲያን የሚሄድን ሰው ተስፋ ማስቆረጥ ይሆናል፡፡ በጎቹን ቀበሮና ተኩላ የሚያስበላ እረኛ ዋጋውን ከጌታው ያገኛል፡፡
አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፡፡ ያን ማን ካደ? ከመነሻውስ አዲስ አበባን ስጡን ብሎ በሰላማዊ ሰልፍም ይሁን በወረቀት አቤቱታ ያቀረበ አለ ወይ? “ና አልመታህም!” አለው አሉ አንዱን፡፡ “ና አልመታህም”ን ምን አመጣው? አለና ሸሸው አሉ፡፡ እናስ! “አዲስ አበባን ለኦሮሞ ሰጠን፤ በኦሮምኛ የሚያስተምሩ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ…” ቲሪሪም ቲሪሪምን ምን አመጣው? ወያኔዎች ጊዜ ካገኙ ገና ብዙ ይዘባርቃሉ፤ እንኳን ከፎከረ ከወረወረም የሚያድነው አምላከ ኢትዮጵያ ይሠውረን እንጂ ብዙና ብዙ የሚያጨራርሱን ዕቅዶች በመጋዘናቸው ውስጥ አሉ፡፡ በኦሮምኛ ይቅርና በጋፋትኛስ ቢሆን አንደኛ ትምህርት ቤት ቀርቶ ዩኒቨርስቲስ ቢሆን እንዳይከፍት የተከለከለ ወገን አለ ወይ? የምን ቅቤ አንጓችነት ነው? ማነው ሰጪ? ማንስ ነው ተቀባይ? ማን ነው መፅዋች? ማንስ ነው ተመፅዋች?
ኦሮሞዎችና አማሮች ስሙኝ፡፡ በልጅነቴ ልጆችን የምናጣለበትንና እኔም ሕጻን ሳለሁ እያጣሉኝ ትልልቆቹ የሚዝናኑብኝን አንድ ጨዋታ ላስታውሳችሁ፡፡ ጎርመስ ጎርመስ ያሉት ነፍስ ያላወቁ ትናንሽ ልጆችን ያመጡና በእጃቸው መዳፍ ላይ ምራቃቸውን እንትፍ ይላሉ፡፡ ከዚያም ወደ ሁለት ልጆች መሀል ይዘረጉና “የማን አባት ገደል ገባ፤ የማን አባት ገደል ገባ!” ይላሉ፡፡ አባቱ ገደል እንዳይገባበት በመሥጋት ቀድሞ “የጀገነው” ልጅ ያን ምራቅ በማበስ ለመቅደም ፈራ ተባ ይል የነበረውን ሌላውን ልጅ ይቀባዋል፡፡ ያ ተደፈርኩ ያለው ልጅ ምራቅ የቀባውን ልጅ በዱላ ማቅመስ ወይም  የባላንጣውን ወገብ በትግልመሰቅሰቅ ይጀምራል፡፡ ጠቡ እየከረረ ይሄዳል፡፡ ልጆቹ በእልህ ሲፋለሙ የጠቡ አነሳሾች አንድ ጥግ ጥላ ላይ ቁጭ ብለው እየተደሰቱ ይዝናናሉ – እንደወያኔ በሰው ስቃይ መደሰት፤ ዘመነ ግላዲያተር በሉት፡፡  በሰባና በሰማንያ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት እፍኝ የማይሞሉ ወያኔ ትግሬዎች በነዚህ ኆልቁ መሣፍርት በሌላቸው አማሮችና ኦሮሞዎች መሀል በሚፈጥሩት አርቲፊሺል ጠብ ሊዝናኑና ሂትለራዊ አገዛዛቸውን ሊቀጥሉ መሆኑን የማይረዳ ዜጋ ካለ በርግጥም በትንሹ የዋህ ነው፡፡ የተደገሰለትን የዕልቂት አታሞ በራሱ ጊዜ እየደለቀ ወደ መቀመቅ ለመውረድ የተዘጋጀ የለዬለት በግ ነው፡፡ መቶና ዘጠና ሚሊዮን በግ ደግሞ ሊኖር አይገባም፡፡ የእስካሁኑ ይብቃን፡፡ ለራሳችን ስንል ነው የሚበቃን ደግሞ፡፡
ስለዚህ የትኛውም ከተማ ለማንም ተሰጠ ይባል፤ ግዴለም፡፡ ኢትዮጵያም ከነነፍሷ ለጭዳነት ቀርባ ባወጣች እየተቸበቸበች አይደለም እንዴ ? በነዚህ ማፊያዎች ያልተሸጠ ነገር፣ በወያኔ ያልተጓጓዘ ነገር፣ ሕወሓት ያላደረሰው ጥፋት ከፀሐይ በታች ምን አለ? ስለዚህ ለማይቀረው ነፃነታችን ወደፊት ከሚገለጥልን አቅጣጫ የሚመጣውን መልካም ንፋስ ከመጠበቅና የበኩላችንን አስተዋፅዖ በምንችለው ከማበርከት ባለፈ በነዚህ ያበቃላቸው የሰይጣን ሽንቶች እንዳንታለል የዜግነቴን አደራ እላለሁ፡፡
ለመሆኑ የኦሮሞው ችግር የስም ለውጥና በራስ ቋንቋ መናገር አለመቻል ነው እንዴ? አለቃ ገ/ሃና ምን አሉ? “ይቺ ሌላ፣ ያቺ ሌላ!”  አዳማና ናዝሬት፣ ቢሾፍቱና ደብረ ዘይት፣ ፊንፊኔና አዲስ አበባ፣ ጂጂጋና ጂግጂጋ፣ አለማያና ሀሮማያ፣ አዋሳና ሀዋሳ፣….  በራሳቸው ዳቦ የሚያስገኙ ቢሆን፣ ዴሞክራሲና ነፃነት የሚያመጡ ቢሆን፣ ስደትን የሚያስቀሩ ቢሆን፣ በመቶዎች በረንዳ የሚያድሩ ዜጎቻችንን ቤት ውስጥ የሚያሳድሩ ቢሆን፣ የወያኔን የመሬት ዘረፋና የሕወሓታውያንን ጋጠወጥነት የሚከላከል ቢሆን፣ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት ከሕወሓት ዘረፋና ንጥቂያ የሚታደግ … ቢሆን ኖሮ የኔም ስም ከምሕረት ወደ ሥምረት ቢለወጥ ግድ ባልነበረኝ፡፡ ግን ግን ከዚያች ሴተኛ አዳሪ የምንማረውና ልብ የምንገዛው መቼ ይሆን? እንደወያኔ ያለ ሞላጫ አጭበርባሪ በ“ነገ እሰጥሻሁ” የማያልቅ ነገ  እያታለለ ቢያሰለቻት ጊዜ “አጭበርባሪ ‹አይበልጠኝም›!” አለቻ! ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ ሆኖ ሳለ ወያኔ ቤተ መንግሥት ውስጥ ቁጭ ብሎ ያሻውን እያደረገ በዚህ በጣም ትንሽ ነገር ያጨራርሰናል፤ ለነገሩ እነሱ ምን አጠፉ? ገልቱዎቹ እኛ! በ“ማን አባት ገደል ገባ!” የሕጻናት ጨዋታ ተሸንፈን ሀገራችንን ከኛ ላነሱ ደናቁርት የሰጠን እኛው ነንና there is no one to blame. ዓለማችን ውስጥ ከ7106 የማያንሱ ቋንቋዎች ይነገራሉ፡፡ አንዱ አንዱን ይውጣል፤ አንዱ ከአንዱ ማሕጸን ይወጣል፡፡ በዚህ ሰው ይተላለቃል? ወይ ሞኝነት! በጀመርኩት እንግሊዝኛ ባወራ፣ በኦሮምኛ ባወራ፣ በአማርኛ ባወራ፣ በትግርኛ ባወራ፣ በጉራግኛ ባወራ፣ በሱማሌኛ ባወራ፣… ሃሳቤን ገለጥኩበት፣ ከሰው ጋር ተገናኘሁበት እንጂ ቋንቋ እኔን ፈጠረኝ እንዴ? ኢንሻኣላህ – እመለስበታለሁ፡፡ ግን ልድገመው – የቀጣፊ ሲሳይ አንሁን!! ችግራችን የሀገር ማጣት እንጂ የቋንቋና የቦታ ስም አይደለም፡፡ ወያኔዎች ዳቢትና ወርቹን፣ ፍሪምባና ጭቅናውን ይዘው እኛን በባዶ ጭራና ለዋገምትና ለዋንጫ እንኳን በማይውል ጠማማ ቀንድ ሲያጣሉን ማየት እጅግ ያማል፤ እናንተንስ አያማችሁም? mz23602@gmail.com

1 comment:

  1. ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡

    ReplyDelete