Wednesday, June 7, 2017

የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ለሕዝባቸው ነጻነት፤ ለአገራቸው አንድነት ለሚያስቡ ወገኖች ባለ5 ነጥብ መልክት አስተላለፈ source zehabesha


የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት የአመራር ጉባኤ አካሄደ
የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት የተመሰረተበትን ዓላማ ከወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ለማራመድ፤ ባለፈው ዓመት ካከሄደው የአባላት ኮንግረስ በኋላ ስላከናወናቸው ተግባራት ለመገምገም፤ መጪውን አንድ ዓመት ሊያከናውን ስለሚገባው ተግባራት እቅድ ለማውጣት ለሶሥት ቀናቶች በሰሜን አሜሪካ ችካጎ ከተማ ጉባኤ አካሂዷል።
በዚህ ጉባኤ የአመራር አባላት በኑሮ ምክንያት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ወደ ጎን በመተው በአካል ተገናኝተው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ያካበቱትን ልምድ ለትግል አጋሮቻቸው ለማካፈል በግል ህይወታቸው ያላቸውን የኑሮ ጫና ወደ ጎን በመተው አውሮፓ ካናዳ እና ሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የድርጅቱ አመራር አባላት ሙሉ በሙሉ በአካል ተግኝተው፤ ስለ ድርጅታቸው መክረዋል።
ከተወያዩባቸው አጫጭር አጀንዳዎች ውስጥ፦
1. ድርጅታቸው ስላከናወናቸው እና ለወደፊት ሊያከናውን ስለሚገባቸው ተግባራት በተለያዩ ኑእስ አጀንዳዎች በመከፋፈል፤
2. ወያኔ በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በጎንደር ክ/ሀገር እና በደቡብ የኦሮሞ ማህበረሰብ ወገኖቻችን ላይ እያከናወነ ያለውን የግፍ ጭፍጨፋ እና መሬታችን ለሱዳን አሳልፎ ለመሥጠት የሚያደርገውን ድብቅ ሴራ፤
3. ሕዝባችን ከጭፍጨፋ፤ አገራችንን ከመከፋፈል አደጋ ለማዳን ከግፈኛው የወያኔ ሥራዓት ለማላቀቅ ሊደረግ ስለሚገባው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት፤ ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት አጀንዳዎች ዙሪያ የመከረ ሲሆን፤ በቀዳሚ አጀንዳው እንደተመለከተው፤ ማንኛውንም ዓይነት ተግባራት እንደ ድርጅት ውጤታማ ለማድረግ፤ በቅድሚያ የድርጅታዊ አሰራር እና ጥንካሬን ተገቢውን ትኩርት በመስጠት በጥንካሬ ላይ መተኮር ስላለበት በመምከር፤ የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት፤ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዙሪያ በቀጣይ ሊያከናውን ያቀዳቸውን የፖለቲካ እና የማህበራዊ እንቅሥቃሴዎች፤በዞን እና በቀጠና ከፋፍሎ የበለጠ ጠንክሮ መሥራት ስላለበት ተግባሮች በጥልቀት መርምሮ የውስጥ መመሪያዎቹን አጽድቋል።
በተከታታይ ደግሞ፤ ወያኔ አገራችን ኢትዮጵያን ለዘለዓለም ቀጥቅጦ ለመግዛት ባለው የተፈጥሮ ባህሪው ምክንያት፤ ወገኖቻችን የጠየቁትን ዲሞክራሲያዊ እና ሰበአዊ መብት በኃይል ለመጨፍለቅ፤ በህይዎት እና በንብረት ላይ እያደረሰ ያለውን ጭካኔ የተሞላበት ወታደራዊ እርምጃ ገምግሟል። በተለይ በአሁኑ ወቅት በደቡብ (በኦሮምያ)፤ በጎጃም እና በጎንደር ክ/ሀገሮች እያደረሰ ያለው ገደብ የሌለው ጭፍጨፋ ፈጽሞ ህዝባዊ ትግሉን በእልህ የበለጠ ሊያቀጣጥል የሚችል መሆኑን በሁሉም አካባቢዎች በተግባር እየተፈጸሙ ያሉትን ሕዝባዊ እንቅሥቃሴዎች ገምግሟል።
ወያኔ ሰንጎ የያዘውን ሕዝባዊ ማእበል ለማዳፈን ጊዚያዊ የወታደራዊ አስተዳደር ቢያውጅም፤ እየታየ ያለው ሕዝባዊ ምላሽ ግን፤ ወታደራዊ አስቸኳይ አዋጅ ከምንም የማያስጥለው ህዝባዊ ብሶት የወለደው የለውጥ ማእበል መሆኑን ነው። በአኳያው፤ ይህን የተቀጣጠል ሕዝባዊ ትግል በተቀነባበረ እና በጠነከረ መልኩ በማቀናጀት ለአንዴ እና ለመጨረሻ የወያኔን ግፈኛ ሥራዓት አስወግዶ፤ በምትኩ የዜጎቿ ነፃነት በእኩልነት የተመሰረተባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመገምባት፤ ሁሉም ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ መሥራት የሚጠበቅባቸው መሆኑን እና በዚህ ዙሪያ የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ሊያበርክት የሚገባዊ ድርሻ መክሯል።
በመጨረሻም በሚከተሉት ጉዳዮች ዙሪያ የአቋም መልክቱን ለሕዝባቸው ነጻነት፤ ለአገራቸው አንድነት ለሚያስቡ ወገኖች አስተላልፏል።
1. ድርብ ሱሪ — አያስጥልም እንዲሉ፤ ወያኔ ብሶት የወለደውን ሕዝባዊ የለውጥ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ በኃይል መጨፍለቅ እንደማይቻለው አምኖ፤ አገራችንን ወደከፋ ጥፋት ከሚውስድ የአደጋ ጉዞ እንዲታቀብ እና የወታደራዊ አዋጁን አንሥቶ አገሪቱን በተረጋጋ መንገድ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥራዓት ለሚያሸጋግር ጊዚያዊ መንግሥት እንዲያስረክብ፤
2. ሕዝባዊ መነሳሳቱን አቅጣጫ ለማስቀየር በስፖርት እና በንግድ እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚገናኘውን ንፁህ ዜጋ ምክንያት እየፈጠረ የሚጭረውን የጎሳ እሳት እሱን ጭምር የሚያቀጥለው መሆኑን አምኖ ከቀጣይ ትንኮሳ እንዲታቀብ። በተለይ በመቀሌ ስታዲዮም በወያኔ ካድሬዎች የተለኮሰውን እና ቂም የቋጠረውን አጸያፊ ድርጊት በአድሎአዊ ፍርድ ሌላ ጦስ ለመፍጠር ከመጣር ይልቅ፤ ሚዛን ባለው መልኩ ለተደበደቡት የጣና ማዕበል የእግር ኳስ ቡድን አባላት እና ደጋፊዎች ህጋዊ ምላሽ እንዲሰጣቸው፤
3. በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት አጥቶ የነበረውን በስፋት እና በውህደት የሚኖረውን የጎንደር ክ/ሀገር ሕዝባችን “ቅማንት እና አማራ” በሚል በአንድ ወቅት ተለኩሶ፤ በኋላም ደብዝዞ የነበረውን አደገኛ ከፋፋይ ሂደት እንደገና ነብስ በመዝራት ወያኔ እያካሄደ ያለውን የቅማንት ካድሬዎች ሥልጠና እንዲያቆም፤ የጎንደር ሕዝብም፤ በድብቅ ወያኔ እየቀበረ ያለውን አደገኛ የዘር ቦምብ በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ ሳይፈነዳ በራሱ ካድሬዎች እግር ተረግጦ እንዲፈነዳ በአስቸኳይ የተለመደ የአንድነት ክንዱን እንዲያጠነክርና የእምቢታ ድምጹን እንዲያሰማ፤
4. የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ የጎንደር ሕዝብ ወያኔ ውስጥ ውስጡን ሲጎነጉን የነበረው የአገራችንን መሬት ለሱዳን ቆርሶ የመሥጠቱ ፍጻሜ ላይ ለማዋል ቀን ከሌት እየሰራ እንደሆነ አውቆ በድንበር ዙሪያ እየተዋደቁ ያሉ ወገኖቻችንን የሞራል እና የቁሳቁስ እርዳታ እንዲያደርግ፤
5. በመጨረሻም፤ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት እና ሌሎችም በሕዝባችን እና በአገራችን ዙሪያ የተጋረጡ አደጋዎችን ለማክሸፍ ሁሉም የተቀዋሚ ድርጅቶች ልዩነታቸውን አቻችለው፤ የአገራቸውን ጥቅም አስቀድመው በጋራ አብረው ይህን አስከፊ ሥራዓት ለአንዴ እና ለመጨረሻ እንዲያስወግዱ ጥሪውን አሥተላልፏል።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት።

No comments:

Post a Comment