Monday, June 26, 2017

ብሄርተኝነት ወደ ዘቀጠ ዘረኝነት ይወስዳል ፤ ዘረኝነት ደግሞ ወደ ውድቀት ይመልሳል

በቶማስ ሰብሰቤ
በብሄር ፖለቲካ ብሄርተኝነት አዎንታዊ ከመሆን ይልቅ ለዘረኝነት ቅርብ ነው።በተለያያ የማህበረሰብ የእውቀት፣የአስተሳሰብና የባህል ልዮነት ውስጥ ለብሄርተኝነት ትልቅ ቦታ መስጠት ዘረኝነት በማሳደግ ወደ ለየለት ዝቅጠት ማምራት ነው።ብሄርተኝነት ውስንነት ላይ መሰረት አለው ፣ ውስንነቱ ደግሞ በዛች በምታስባት ነገር ላይ ይበልጥ ትኩረት እንድሰጥ ያስገድድሃል።የበላይነትና ሌላውን እንደ ራስ ያለማየት ሰወኛ ያልሆነ ባህሪ ያመጣብሃል።
ስለ ራስ ብቻ ብዙ እንድትጨነቅ አድርጎ ትልቁ ነገር እንዳታይ ያደርግሃል።ሰው በተፈጥሮው ስለ ራሱ ብቻ እንዳያስብ ፣እንዳይጨነቅና እንዳይኖር የተፈጠረ ስለሆነ ማስብ የተቸረው እንስሳ ነው።ብሄርተኛ ስትሆን ደሞ ለሰው የተቸረው የማስብ ፀጋ ሳታውቀውም ከሰውነት እንደ ፀጉር ያልቃል ያኔ የዘረኝነት መንገድ ትጀምረዋለህ ፤ ያኔ ስለ አንድ ጠባብ ነገር እየተጨነክ ትልቁን ነገር ትስተዋለህ።
ዘረኝነት የብሄር ፖለቲካ የበኩር ልጅ ነው።ዘረኝነት ከአንድነት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰው ተፈጥሮ ጋር የተጣላ ነው።ባለፉት 26 አመታት ያለው የብሄር ፖለቲካ በትንሹ እንኳን ካስተዋልነት ከእንድነት ጋር ብቻ ሳይሆን የተጣላነው ብዙዎች ከሰውነት ሰበዓዊ ፍጥረት ደረጃ ወርደው በተጨማለቀ በዘረኝነት ዝቅተጥ ውስጥ ገብተዋል።ከደርግ ውድቀት በፊትና በኋላ የመጣው ብሄርተኝነት የመልክ ፣የአካሄድና የስልት ልዮነት ይኑረው እንጂ በባህሪውና አላማው ተመሳሳይ ነው።
ከደርግ ውድቀት በፊት ያለው የሻቢያ፣የህውሃትና የኦነግ ብሄርተኝነት ጥላቻና ራስን በራስ ማስተዳደር ላይ መሰረት ያደረገ ነበር።ሻቢያም ሆነ ህውሃት ለህዝቦቻቸው ፀረ አንድነት ፣ ሌላውን የመጥላት ፖለቲካ ፣ በሀሰት የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የትግራይና የኤርትራ ህዝብ በሌላው ኢትዮጰያዊ በተለይ በአማራው መደብ ጭቆና እንደደረሰበት ፣ ከማንም በላይ ራሱን እንዲወድ አድርጎ የተነገረው ወቅት ነው።ሻቢያም ሆነ ህውሃት ጠንካራዉን የደርግ መንግስትን ለመጣል በጥላቻ ብሄርተኝነትና በዘረኝነት ህዝባቸው አነሳስተው ሻብያ ሀገር መስርቷል ፤ ህውሃት መንግስት ሆኖል።
ይህና ሌሎች ውስብስብ ጥላቻ ፣ ሸፍጥና የጠነባ ህዝብን ከህዝብ ያቃቃረ ዘረኝነት ከተሰራ በሃላ የመጣው ስርዓትም ደሞ የብሄርተኞች የፖለቲካ ዳማ ይዞ ከደርግ ውድቀት በኋላ አለ።ህውሃት ቅደመ ስልጣን በጥላቻ ሲያብጠለጥለው የነበረው አማራ “ትምክተኛ” ፤ ሌላውን ተቀናቃኝ ኦሮሞ “ጠባብ ” ብሎ ሁለቱ ትልልቅ ብሄሮች የመብት ጥያቄ ካነሱ ለማደፈ በዚህ ስልት እየኖረ ነው።በተለይ አማራና ኦሮሞ ህውሃት ከመንበረ ስልጣኑ በፊትና በኋላ ያሰመረባቸው ብሄሮች ቢሆኑም ሌላው ኢትዮጵያዊም ከአንድነት ይልቅ ልዮነት ፣ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅና በጠባብ ነገር ብዙ ጊዜ እንዲፈጅ የመጣ ሰርዓት ነው ብሄርተኝነት።
መንግስቱ ኋይለ ማሪያም በብሄርተኝነትና ገንጣይነት ህውሃትና ሻቢያ ሲያስቸግሩት ብዙ ይናገር ነበር።ጓድ መንግስቱ በንቀት ” ሰሜን ኢትዮጵያ የሻቢያና የወያኔ መደበቂያ ሳይሆን መቀበሪያ ይሆናል” ይሉን ነበር።የተናቀ ያስረግዛል ይሉት ፕሬዘዳንቱን አፍንጫቸው ድረስ መተው አባረው ይኸው ዛሬ እነሱንም ባለ ጊዜ ሲሆኑ “ብሄርተኝነት ወደ ዘቀጠ ዘረኝነት ይወስዳል ፣ዘረኝነት ወደ ውድቀት ይመልሰናል” ስንላቸው እንደ ፕሬዘደንት መንግስቱ ይንቁናል።
ለመንግስቱ ውድቀት በርካታ ነገሮች ቢኖሩም ለህውሃትና ሻቢያ የሰጡት ንቀት ከፍተኛ ቦታ አለው።ህውሃትና ሻቢያ ከውጪ ሀገራት ጋር ያላቸው ግንኙነት በሰፊው አያሳስባቸውም ፤ የሰሩት ህዝብ ለህዝብ የማቃቃር ስራ እንብዛም ቦታ አልተሰጠውም፣ ሁለቱም በተሳሳተ ታሪክ ፣ውንጀላና ጥላቻ ህዝባቸውን ለጦርነት ሲያስነሱ ለፕሬዘደንት መንግስቱና ጓዶች ሰሚ የለውም ነበር ።መጨረሻ የጉዱ ቀን መጣና 4 ኪሎ ቁጭ አሉ።
ዛሬም ህውሃት ኢህአዴግ በእጁ ጠፋጥፎ የሰራው ብሄርተኝነት ወደ ዘረኝነት ተቀይሮ ሊበላው ነው።ያኔ ለስልጣን ማራዘምና ከፋፍሎ ለማስተዳደር ምቹ የሆነው የብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ዛሬ ምርጥ የደለበ ዘረኛኒዝም አሳድጎልናል።ኢህአዴግን በትጥቅ ትግል አይወድቅም ፣ ኢህአዴግ በምርጫ አይወድቅም ፤ ኢህአዴግ የሚወድቀው እራሱ ባመጣው የብሄርተኝነትና የዘረኝነት ፖለቲካ ጠርዝ ነው።ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ያደገው ወጣት ስለ ልዮነቱ የዘመረ ነው።
ስለ ራሱ ብቻ እንዲያስብ የተገደደ ፤ ስለ ሌላው ኢትዮጵያዊ የማይጨነቅ ፣ ትልቁ ሀገር ሳይሆን ትንሽየዋ ክልል በዓይነ ህሊናው ያለ ፣ ብሄርተኝነት ዘረኝነት ወልዶበት በዝቃጭ ኢ _ሰበዓዊነት አስተሳሰብ እንዲጫወት ያደረገው ስርዓት ነው።ይህ ስርዓት ደሞ ወደድንም ጠላንም ሁሉም ሀገሬን ከማለት ይልቅ አጉል ውድድር ውስጥ አስገብቷል።ምንም ነገር ሲሰራ እንደ ሀገር ከመቆም ይልቅ በጣም ርካሽ በሆነ በዘር ቆጠራ ፣በዘር ልማት ፣በዘር ባለሞያ ፣በዘር ስልጣን ፣በዘር ሃይማኖት ፣በዘር ማህበርና በዘር ባህል አጉል በዘረኝነት የተጨመላለቀ አካሄድ ላይ ነን።
ይሄ ትውልድ የኢትዮጵያ መሬት በሱዳን ከመወሰድ ይልቅ ሲዳማ ከወላይታ የወሰደው መሬት ይሰማዋል።ልክ ሎሬት ፀጋዮ ገብረ መድህን “የዘንድሮ ትውልድ ወኔው የሚመጣው አረቄ ሲጣጣ” ነው እንዳሉት የህውሃት ኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ ወጣት ከሀገሩ በላይ ክልል ሲነካበት እንዲያመው አድርጎ ነው የተሰራው【የተወሰኑ ሀገር ወዳድ ወጣት እንዳለ ሳይረሳ】 ይህ ፅንፈኝነት ደሞ መጀመሪያ አምጪውን ህውሃት ኢህአዴግን ይበላዋል።ዛሬ ህውሃት ኢህአዴግ ፈታዋለው የሚለው ለ26 አመታት የዘራው ዘረኝነት አይደለም ሊፈታው ይቅርና ራሱን ያጭደዋል።
የህውሃት ኢህአዴግ በምርጫ ሳይሆን ባመጣው የዘር ፖለቲካ ይወድቃል ፣ህውሃት ኢህአዴግ በትግል ሳይሆን ውሃ አጠጥቶ ባሳደገው ብሄርተኝነትና ዘረኝነት ይወርዳል።ይህን ስል ካሳቀ ደሞ ጓድ መንግስቱ ያኔ የናቀ ትዝ ይበልህ።የአንድ ብሄር ተጠቃሚነትና ህውሃት ኢህአዴግን የደገፈ በማህበራዊ ፣ፖለቲካዊና ፣ኢኮኖሚያዊ ዘርፋ ላይ በሃገሪቱ የበላይ ተጠቃሚ ሲሆን ጪሰኛው መቆጣቱ አይቀርም።
የሀገሩቱ የሲቪክ ማህበራት በማዳከም ፣ የውጪ ግንኙነት የበላይነት ፣የንግድ የበላይነት ፣የወሳኝ ስልጣን የበላይነት ፣ የተደማጭነትና የተፈሪነት የበላይነት የወሰደው የህውሃት አመራር ዛሬ የደህነንነት መስሪያ ቤቱን ፣መከላከያውንና ሀገሩን ስለተቆጣጠረ እድሜ ያለው ይመስላዋል።ነገር ግን ህዝብ ከማንም በላይ ነው።ህዝብ በሀገሪቱ ያለው የብሄር ፖለቲካ መጠቃቀም ከማንም በላይ አይቶ “በቃኝ” ብሏል።ከዚህም አልፎ ዘረኛ ፣ብሄርተኛ ትውልድ ተፈጥሯል።ዘረኝነት የዘቀጣ፤ ብሄርተኝነት ርካሽ ፖለቲካ ቢሆንም ፤ ዘረኝነትና ብሄርተኝነት አምጪውን ኢህዴግን ሲበላው ማየት ያስደስታል።

No comments:

Post a Comment