Thursday, July 6, 2017

” እኛን ሰዎች ኤርትራን ሸጣችኋታል እያሉ ያሙናል፡፡ ” ኃይለማርያም ደሳለኝ source bbn

ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም እስራኤልን ብቻ መጎብኘታቸው ቅር እንዳሰኛቸው የፍልስጤሙ መሪ ተናገሩ . BBN.

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ፍልስጤምን አለመጎብኘታቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የፍልስጤሙ መሪ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድም ሁለት ጊዜ እስራኤልን መጎብኘታቸውን ያስታወሱት የፍልስጤሙ መሪ መሐሙድ አባስ፣ ፍልስጤምን አለመጎብኘታቸውም ቅር እንዳሰኛቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነገሯቸው ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የእስራኤል ጉብኝት ተከትሎ፣ ፍልስጤም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተለየ ሁኔታ እየተከታተለችው እንደምትገኝም የፍልስጤሙን መሪ ጠቅሶ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
ሁለቱ መሪዎች የተነጋገሩት በአዲስ አበባ ሲደረግ በነበረው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ኢ-መደበኛ በሆነ ውይይት ላይ ሲሆን፣ በውይይቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ተደጋጋሚ ወቀሳ ቀርቦባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ፍልስጤም ባቀረበችው ግብዣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሀገራቸውን እንዲጎበኙ የቀረበላቸውን ተደጋጋሚ ግብዣ አለመቀበላቸው ቅር እንዳሰኛቸው የፍልስጤሙ መሪ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን እንደ አገሬ ነው የማያት፡፡›› ያሉት ፕሬዚዳንት መሐሙድ አባስ፣ ‹‹ከእስራኤል ፕሬዚዳንት ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ያለው ችግር የአገሬን ሉዓላዊነትና ደኅንነት እየተፈታተ ነው፡፡›› ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያ ደሳለኝ ከዚህ ቀደም እስራኤልን የጎበኙት በግላቸው መሆኑን ለፍልስጤሙ መሪ የገለጹላቸው ሲሆን፣ ‹‹ፍልስጤምን መጎብኘት አለመቻሌን ከእስራኤል ጋር አታያይዙት፡፡›› ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በቅርቡ እንኳን ወደ እስራኤል አቅንተው የነበሩት መንግስታቸውን ወክለው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሆኖም ‹‹ወደ እስራኤል የሔድኩት በግሌ ነው፡፡›› ማለት ለምን እንደፈለጉ አልታወቀም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ‹‹ኢትዮጵያ ከፍልስጤም ጋር ያላትን ግንኙነት ወደፊት ታጠናክራለች፡፡›› ብለዋል፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም ንግግራቸውን ቀጥለው በውይይቱ ላይ ‹‹እኛን ሰዎች ኤርትራን ሸጣችኋታል እያሉ ያሙናል፡፡ እውነታው ግን የሕዝብ ውሳኔ ነው፡፡›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹እናንተም ሕዝቦቻችሁን መሠረት አድርጋችሁ በመካከላችሁ ያለውን ግጭት መፍታት ይገባችኋል፡፡›› ሲሉ ለፍልስጤሙ መሪ መሐሙድ አባስ ምክር ቢጤ ለግሰዋል፡፡ መሐሙድ አባስ በበኩላቸው፣ ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር ያላትን ቅራኔ ለመፍታት ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አቶ ኃይለማርያም በበኩላቸው ‹‹በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ውሳኔ ዘላቂነት ላይ ጥርጣሬ ቢኖረኝም ጅምሩ ጥሩ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
BBN

No comments:

Post a Comment