Thursday, July 13, 2017

ፍርድ ቤቱ በእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብ ላይ ብይን ሰጠ • 5 ተከሳሾችን በነፃ አሰናብቷል • አቶ በቀለ ገርባ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ተከላከል ተብሏል source mereja.com

ፍርድ ቤቱ በእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብ ላይ ብይን ሰጠ
• 5 ተከሳሾችን በነፃ አሰናብቷል
• አቶ በቀለ ገርባ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ተከላከል ተብሏል
(በጌታቸው ሺፈራው)

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሀምሌ 6/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያና መዝገብ በተከሰሱት 22 ተከሳሾች ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ ሁለት ክስ ቀርቦባቸው የነበር ሲሆን ከ1ኛ እስከ 13ኛ ያሉት ተከሳሾች ኦሮሚያ ውስጥ ተከስቶ በነበረው ህዝባዊ አመፅ ‹‹በቀጥታ በመሳተፍ፣ ከውጤቱም ተካፋይ ለመሆን›› የሽብርተኝነት ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 3 ስር የተደነገገውን ተላልፈዋል ተብለው ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ በሁለተኛ ክስ ከ14ኛ እስከ 22ኛ ያሉት ተከሳሾች በማንኛውም መልኩ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ በሚል በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 7(1) ስር ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት በቀጥታ በሽብር ወንጀል ተሳትፈዋል ተብለው ተከሰው ከነበሩት መካከል 1ኛ ተከሳሽ ጉርሜሳ አያና፣ 2ኛ ተከሳሽ ደጀኔ ጣፋ፣ 3ኛ ተከሳሽ አዲሱ ቡላላ፣ 5ኛ ተከሳሽ አብደታ ነጋሳ፣ 6ኛ ተከሳሽ ገላና ነገራ፣ 8ኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ፣ 11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዳ እና 12ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ሊበን ተመስርቶባቸው ከነበረው በቀጥታ የሽብር ወንጀል መፈፀም በሽብርተኝነት ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወደሚል ተቀይሮ ከፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 3 በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 7(1) ስር ተቀይሮ ይከላከሉ ሲል ክሳቸውን አሻሽሏል፡፡
በተመሳሳይ አቶ በቀለ ገርባ ላይ የቀረበው ማስረጃ የሽብር ወንጀልን የሚያቋቁም ስላልሆነ ከፀረ ሽብር አዋጁ ወጥቶ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀፅ 257 (ሀ) ስር የተደነገገውን ግዙፍ ያልሆነ መሰናዳትና መገፋፋት ክስ ተቀይሮ እንዲከላከል በይኗል፡፡ በሌላ በኩል በ1ኛ ክስ በጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 3 ስር ተከሰው ከነበሩት መካከል 7ኛ ተከሳሽ ጭምሳ አብደሳ፣ 9ኛ ተከሳሽ ፍራኦል ቶላ፣ 10ኛ ተከሳሽ ጌታቸው ደረጀ እና በማንኛውም መልኩ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ክስ ተመስርቶበት የነበረውና በዜግነት ኬንያዊ የሆነው 22ኛ ተከሳሽ አልካኖ ቆንጨራ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ወስኗል፡፡
በዚሁ መዝገብ በማንኛውም መልኩ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት 14ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ፣ 15ኛ ተከሳሽ የሱፍ አለማየሁ፣ 16ኛ ተከሳሽ ኢካ ተክሉ፣ 17ኛ ተከሳሽ ገመቹ ሻንቆ፣ 18ኛ ተከሳሽ መገርሳ አስፋው፣ 19ኛ ተከሳሽ ለሚ ኢዴቶ፣ 20ኛ ተከሳሽ አብዲ ታምራት እና 21ኛ ተከሳሽ አብዲ ኩምሳ ተከሰውበት የነበረውን አንቀጽ 7(1) ስር የተጠቀሰውን እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ይከላከሉ የተባሉበት አንቀፅ ዋስትና የሚያስፈቅድ በመሆኑ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው በጠበቆቻቸው በኩል ጥያቄ አቅርበው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ‹‹በፅሁፍ አስገቡ›› ሲል ለጥያቄው ውሳኔ ሳይሰጥ አልፎታል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን የመከላከያ ምስክር ለመስማት ከነሃሴ 8-12/2009 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment