Friday, April 7, 2017

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጃዋር መሃመድ በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ተወሰነ | ዶ/ር መረራ ፍርድ ቤት ቀረቡ

ዶ/ር መረራ ጉዲና ፍ/ቤት ቀርበው ነበር (መጋቢት 29/2009)
*ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ ጃዋር መሃመድ፣ ኢሳት እና ኦኤምኤን በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ተወስኗል።
ባለፈው በነበረው ቀጠሮ በእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና መዝገብ ከሃገር ውጪ የሚገኙ ተከሳሾች ቀርበው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ የሚያደርግ ማስታወቂያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲወጣ እና የወጣውን ማስታወቂያ ለማየት ለዛሬ መጋቢት 29/2009 ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር።
ዛሬ መጋቢት 29/2009 በዋለው ችሎት መጋቢት 15/2009 የታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ገፅ 7 ላይ ከሃገር ውጪ የሚገኙት 2ኛ (ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ)፣ 3ኛ (አቶ ጃዋር መሃመድ) ፣ 4ኛ (ኢሳት) እና 5ኛ (ኦኤምኤን) ተከሳሾች ቀርበው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ የሚያደርግ ማስታወቂያ መታተሙን እና በመዝገቡም ላይ ኮፒው መያያዙን ዳኞች ያሳወቁ ሲሆን፤ የአቃቤ ህግን አስተያየት ጠይቀዋል። አቃቤ ህግም ተከሳሾቹ በጥሪው መሰረት ስላልቀረቡ ክሱ በሌሉበት እንዲታይ ጠይቋል። ዳኞችም፤ አቃቤ ህግ ሌላ ሃሳብ እስኪያመጣ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስረአት አንቀፅ 161 እና 163 መሰረት ተከሳሾቹ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ወስነዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና በዛሬው ችሎት ከማእከላዊ ቀርበው የነበረ ሲሆን ለሚያዚያ 16/2009 በሳቸው ላይ የቀረበውን ክስ መቃወሚያ ለመስማት የተያዘው ቀጠሮ እንደተጠበቀ መሆኑ ተገልፇል።

በተያያዘ ጉዳይ ዶ/ር መረራ የዋስትናውን ጉዳይ በተመለከተ ይግባኝ ብለው ዛሬ መጋቢት 26/2009 ከሰአት ጠቅላይ ፍ/ቤት ቀርበው ነበር። የይግባኙን ፍሬ ሃሳብ ወክለዋቸው የቀረቡት ጠበቆች አቶ ወንድሙ ኢብሳ፣ አቶ አለሙ ጎቤቦ እና አቶ ደሳለኝ ቀነኢ ለችሎት ያስረዱ ሲሆን፤ ዝርዝር ሃሳቡንም በፅሁፍ አስገብተዋል። የስር ፍ/ቤት በዶ/ር መረራ ላይ የቀረበው የመጀመሪያ ክስ ከእድሜ ልክ እስከ ሞት ያስቀጣል የተባለውን እንደሚቃወሙ የገለፁት ጠበቆቹ፤ በመጀመሪያው ክስ የተጠቀሰው አንቀፅ 238 (1) መነሻ ቅጣት 3ት አመት ከፍተኛው ደግሞ 25ት አመት መሆኑን ጠቅሰው የጥፋተኝነት ብይኑ እርግጠኛ ባልተኮነበት ሁኔታ ከፍተኛው መያዝ እንደሌለበት ተናግረዋል። በመጀመሪያው ክስ የተጠቀሰው ሌላው አንቀፅ 238(2) ን በተመለከተ ደግሞ ብቻውን መታየት እንደሌለበት ከአንቀፅ 238(1) ጋር አብሮ መያያዝ እንደሚኖርበት ገልፀዋል—ጠበቆች።
ዳኞቹም በጠበቆቹ በኩል የቀረበውን የይግባኝ ቅሬታ ከሰሙ በኋላ፤ ያስቀርባል አያስቀርብም የሚለውን ውሳኔ ከመጪው ሰኞ (ሚያዚያ 2/2009) በኋላ ጠበቆች ማረጋገጥ እንደሚችሉ እና የሚያስቀርብ ከሆነ ለክርክር በሚሰጠው ቀጠሮ ዶ/ር መረራ እንደሚቀርቡ ገልፀዋል።
ዶ/ር መረራ “ከክሴ ጋር የተያያዙት ማስረጃዎች ባለፉት 25 አመታት በፓርላማ ያረኳቸው ንግግሮች እና በተለያየ ጊዜ የፃፍኳቸው ሃሳቦች ናቸው። ጉዳዩ የፓለቲካ መሆኑን ያሳያል። ክሱ የፓለቲካ ነው። በዚህ በኩል እንድታዩት ነው።” የሚል አስተያየታቸውን ለዳኞች ተናግረዋል።
ዶ/ር መረራ ዋስትናውን በተመለከተ የይግባኙ ቅሬታ እና በአዲስ ዘመን የወጣው ማስታወቂያ ከዚህ ፅሁፍ ጋር ተያይዟል።
ዜናው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት ነው
Related Story
  1  120  121

No comments:

Post a Comment