Wednesday, April 19, 2017

በሦስት ክልሎች በተፈጠሩ ‹‹ሁከቶች›› 669 ሰዎች መሞታቸውን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋ አደረገ source mereja.com

ከሐምሌ 2008 ጀምሮ እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ‹‹ሁከቶች››፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞን ብሔርን መነሻ ባደረገ ግጭት የ669 ሲቪሎችና የፀጥታ አስከባሪዎች ሕይወት ማለፉን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይፋ አደረገ፡፡
ኮሚሽኑ በተጠቀሱት አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት አዘል ተቃውሞዎች በመመርመር ሪፖርቱን ማክሰኞ ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ከተጠቀሱት የሟቾች ቁጥር አብዛኛዎቹ ማለትም 495 ያህሉ ሕይወታቸው ያለፈው በኦሮሚያ በተነሳው ብጥብጥና ግጭት ነው፡፡
በኦሮሚያ በ15 ዞኖችና 91 ወረዳዎችና ከተሞች የተቀሰቀሰውን ግጭት አዘል ተቃውሞ በመመርመር ሪፖርት ያቀረቡት ኮሚሽነሩ፣ የግጭቱና የተቃውሞው መሠረታዊ መንስዔ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግርና የመብት ጥሰት፣ የሥራ አጥነት ችግር ሰፊ መሆን፣ የልማት ፕሮግራሞች መዘግየትና መታጠፍ፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ጥቅም በሕግ ተደንግጎ ተግባራዊ አለመደረግን ጠቅሰዋል፡፡ በአባባሽ ምክንያትነትም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) እና ሌሎች የሚዲያ አውታሮች የሕዝቡን ምሬት በመጠቀም፣ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ ከፍተኛ የአባባሽነት ሚና መጫወታቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
በቢሾፍቱ ከተማ በኢሬቻ ባህላዊ በዓል ላይ የተከሰተውን አሳዛኝ የሰዎች ሕይወት ሕልፈት አጋጣሚን በመጠቀም፣ መንግሥት በተዋጊ ጄቶችና በሔሊኮፕተሮች ኦሮሞን እየጨረሰ እንደሆነ በመቀስቀስ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች አመፁ እንዲስፋፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
አመፁን በማስፋፋት ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመግባት ጥረት እንደነበረም ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከፍተኛ የትጥቅ ትግልና ውጊያ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
በምሥራቅ አርሲ፣ በባሌ፣ በምዕራብ ጉጂና በጉጂ ዞኖች በጦር መሣሪያ የተደገፈ ውጊያ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ በሶዶ፣ በአዳአ በርጋ፣ በሜታ ሮቢ፣ በደንቢ የሙሉ ቀን ውጊያ የነበረ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ ሕግን የተከተለ፣ ተመጣጣኝና ተገቢ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ምዕራብ አርሲ፣ ሻሸመኔና በአርሲ ነገሌ ተመሳሳይ ውጊያ የተካሄደባቸው በመሆናቸው የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በአዳሚ ቱሉ ማረሚያ ቤት 14 እስረኞች ሊያመልጡ ሲሞክሩ በጥበቃ ኃላፊዎች መገደላቸው ሕግን ያልተከተለ፣ አላስፈላጊና ተመጣጣኝ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ በባሌ ዞን ሮቤ ከተማና በራይቱ ወረዳ የተካሄደው ሠልፍ በጦር መሣሪያ ያልተደገፈ በመሆኑ፣ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተመጣጣኝ አልነበረም ብለዋል፡፡
በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በአወዳይ ከተማ በተወሰደው ዕርምጃ 28 ሰዎች መሞታቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹ዕርምጃው ሕግን ያልተከተለና ተመጣጣኝ ያልሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እንዲሁም በምሥራቅ ወለጋ በነቀምቴ 12 ሰዎች ሕግን ባልተከተለና ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ መገደላቸውም ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ከሐምሌ 2008 እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ‹‹ሁከት›› የ462 ሲቪሎች ሲገደሉ 33 የፀጥታ አስከባሪዎችም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙንም ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ሁከትና ብጥብጥ እንደሚነሳ እየታወቀ ዕርምጃ ባልወሰዱ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ሲሉ ኮሚሽነሩ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
በአዳሚ ቱሉ ማረሚያ ቤት 14 ታራሚዎችን የገደሉ የጥበቃ ሠራተኞች በወንጀል ክስ እንዲመሠረትባቸው ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ኦነግና ተባባሪዎቹ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራርና አባላት ሊጠየቁ እንደሚገባ በተመሳሳይ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
በጌዴኦ ዞን አራት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በተቀሰቀሰ ብሔር ተኮር ግጭት 34 ሰዎች መግደላቸውን ገልጸዋል፡፡ የዚሁ ግጭት መንስዔ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ከእኩል ተጠቃሚነት ጋር የተገናኘ መሆኑን፣ መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በዲላ ጊምቦ የገበያ ቦታ ለሳሪንደን አክሲዮን ማኅበር እንዲሰጥ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ብይን የዞኑ አስተዳደር ለመቀበል አለመፈለጉና ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ከጌዴኦ ውጪ ያሉ ብሔሮች ዞኑን ለቀው እንዲወጡ ሲካሄድ የነበረ ቅስቀሳ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሞቱት በተጨማሪ 178 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን፣ ከጌዴኦ ወጪ ያሉ 8,450 የተለያዩ ብሔሮች አባላት መፈናቀላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ግጭትና ሕይወት መጥፋት፣ እንዲሁም አካል መጉደል በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ የጌዴኦ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የዞኑ የአመራር አካላትና ፖሊሶች በነበራቸው የመቀስቀስና የማደራጀት ሚና በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች በነበረው ተቃውሞና ግጭት 110 ሲቪሎች ሲገደሉ፣ 30 የፀጥታ ኃይሎች ተመሳሳይ ዕጣ እንደገጠማቸው በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡ የአካል ጉዳትን በተመለከተም 276 ሲቪሎችና 100 የፀጥታ አስከባሪዎች መጎዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአማራ የተከሰተው ግጭትና ተቃውሞ መንስዔም በተመሳሳይ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ፍትሕ ማጣት፣ የቦታ አሰጣጥ ችግር፣ ኢፍትሐዊ ግብር አጣጣልና የኑሮ ውድነት መሆኑን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡
አባባሽ ሁኔታዎች በሚል ያቀረቧቸው ደግሞ የወልቃይት ጉዳይ በጊዜ መልስ ሊያገኝ አለመቻሉ፣ የአማራ መሬት ለሱዳን ተሰጥቷል የሚል ቅስቀሳ መኖሩ፣ በሲቪክ የትምህርት መጽሐፍ ላይ ያልታረመው የክልሎች ካርታ ተጠቅሰዋል፡፡
ተመጣጣኝ ያልሆኑ ግድያዎች በአማራ ክልል መፈጸመቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ በጎንደር አዘዞ፣ በደንቢያ፣ በወንበራ፣ በደባርቅ፣ በደብረ ታቦር፣ በስማዳ፣ በእንጅባራ እንዲሁም በዳንግላ ተመጣጣኝ ያልሆኑ ግድያዎች ተፈጽመዋል ብለዋል፡፡
በጎንደር ማራኪ በሚባለው ቦታ የፌዴራል ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በወሰደው ዕርምጃ 12 የፀጥታ ኃላፊዎችና አራት ሲቪሎች መገደላቸውን፣ በማረሚያ ቤት የተወሰደው ዕርምጃም ሕግን የተከተለ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በአማራ ክልል ብሔር ተኮር ጥቃት በመካሄዱ 11,678 የትግራይ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ በሰጡት ምክረ ሐሳብም በተፈጠረው ረብሻና ብጥብጥ ለተከሰተው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም አጥፊዎች ተለይተው ለሕግ እንዲቀርቡ ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ምክር ቤቱ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ፓርላማው ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች መነሻ ምክንያትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በገለልተኛ አጣሪ እንዲመረመር ለኢትዮጵያ መንግሥት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ማክሰኞ ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ምርመራውን በራሷ ተቋም የማካሄድ አቅም አላት፤›› በማለት የተመድን ጥያቄ እንዳልተቀበሉት ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በገለልተኝነት እንደሚሠራ ለቢቢሲ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተቋሙ የአቅም ውስንነት አለበት ብለዋል፡፡ 
Standard (Image)

No comments:

Post a Comment