Wednesday, May 3, 2017

በማዕከላዊ እስር ቤት በዶ/ር ጋሹ ክንዱ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰትንና በህክምናው ላይ የተጋረጠን ሌላኛውን እሾክ በድጋሜ ስለማውገዝ፤

በማዕከላዊ እስር ቤት በዶ/ር ጋሹ ክንዱ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰትንና  በህክምናው ላይ የተጋረጠን ሌላኛውን እሾክ በድጋሜ ስለማውገዝ፤
ከዐማራ ሀኪሞች ማኅበር Branna MediA
ዶ/ር ጋሹ ክንዱ የህክምና ዶክትሬት ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት የተመረቀ ወጣት የዐማራ ሀኪም ነው። ከተለያዩ ሀገራት የህክምናና የመሪነት ልምድን አካብቷል። ብዙ የግል ጥቅሞችን በመተው ወደሚያፈቅረው ገጠራማ የዐማራ ክፍል በመሔድ አገልግሏል። የቡሬ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ነው። የዐማራ ሃኪሞች ማኅበር ግንባር ቀደም መስራችና ፕሬዚዳንት ነው። እርዳታ በሚያስፈልጋቸው የተለያዪ የዐማራ ክፍሎች የሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል። ጥሪ በተደረገበት ቦታ ሁሉ በአፋጣኝ በመድረስ ብዙ ህይወትን ታድጓል።  የዐማራዉን ስር ሰደድ ድህነት፣ የሕክምና እጦትና መፍትሄዎች በበርካታ የዳሰሳና የምልከታ ጥናቶች አስደግፎ ለታዳሚው የሚያስተምር ምስጉን ሀኪም ነው።  አዋጭ የጤና ፖሊሲዎችን የሚተነትን ባለራዕይ የዐማራው ተስፋ ነው።  ምክንያቱም የዐማራ ሕዝብ  የጤና ሁኔታ ከሀገራችንና ከዓለማችን ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛው ነው:: በዚህ ታላቅ ነባርና ቀደምት ሕዝብ  ላይ ከባድ የበሽታ ሸክም ተንጃቦበታል፤ የጤና ሽፋን መጠኑ ከ42 በመቶ አይበልጥምና።  ባለው የደህንነት ስጋትና ቀውስ ምክንያት ዐማራው የሕክምና ባልሞያ  እንደልብ የማይገኝበት ነው።  ሁኔታውን ከባድና አሳሳቢ የሚያደርገው ሌላኛው ክስተት የህክምና ስነ-ምግባርን የጣሰ፣ ሀኪምን በእስር ቤት ማሰቃየት ነው፤  ዶ/ር ጋሹ ክንዱ ከወራት በፊት በኮማንድ ፖስት ከባህር ዳር ታፍኖ ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ እስር ቤት የተወስደ መሆኑ ይታወቃል። ያለምንም ፍርድ ለ3ኛ ጊዜም ተቀጥሯል።
በራሱ አንደበት የተነገረ ና የሚታይ አካላዊና ስነ- ልቦናዊ ኢሰብዓዊነት እየተፈፀመበት ነው።  ይህ ድርጊት ከ ‘ሜዲስን ፎር ፒስ’ (MFP, Cruelty and Denial, Medical Evidence for State-Sponsored Torture in Ethiopia ) ሪፖርት የተለየ አይደለም፤ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ አካላዊ ማሰቃያ ስልቱ በህቡዕና በብሄራዊ ደረጃ መዋቀሩን ያትታል፤ አብዛኞቹ ምሁራን  መሆናቸውንና እስከ 52%ቱ ዐማራ በመሆናቸው ብቻ መታሰራቸውን ይገልጻል። ከ50 በመቶ በላይ ከድብደባ እስከ ‘ፋላንጋ’ ና ‘ቴሌፎኖ ‘  የማሰቃያ ዘዴዎች እንደሚደርሱባቸው የተረጋገጠ ነው።  በዶ/ር ጋሹ ክንዱ ላይ ከዚህ የተለየ እጣ ፋንታ አልተለየዉም።
ዶር ጋሹ ከላይ በተገለፀው ማንነቱ የሚታወቅ እና የዐማራው ሁለገብ የጤና ቀውስ የሚያሳስበው እንጅ ለእስራት የሚያበቃ መረጃ አልተገኘበትም። ይህ ዶክተርን ፣ ቤተሰቡንና ተገልጋዩን የሚጎዳ አፋኝ እርምጃ መሆኑን የዐማራ ሀኪሞች ያምናሉ።
ህክምና በሞያው ፀባይ የሕዝብ  መሪ ማድረጉ አሁን ላይ ለመንግስት ፖለቲካዊ ስጋት አሳድራል።  የህክምና ባለሞያን ማጥቃት መዘዙ ብዙ መሆኑ ሁልጊዜ ም መታወቅ አለበት። የሰው ልጅ በበሽታ እንዲሰቃይና ሞቱ እንዲፋጠን ምክንያት ይሆናል። ህይወትን የማዳን ሩጫው እንዲገታ ይደረጋል።  በተባበሩት መንግስታት የጸደቀውና በሁሉም የህክምና ማህበራት የሚተገበረው እኩልና የላቀ ጤና የማግኘት መብት የተጣሰ ይሆናል።  ሀገራት የዜጎቻቸውን የጤንነት ሁኔታ ለመጠበቅ ለሀኪሞች ምቹ የመስሪያ ቦታ እና አስደሳች ጥቅማጥቅሞች እንዲያመቻቹላቸው ይደነግጋል። በሀገር ደረጃም በኢትዮጵያ የህክምና ማኅበር በ 2010 የጸደቁ  የጤና ህግጋቶች አሉ፤  ማህበሩና ተከታይ ሃኪሞች የሚያከብሯቸው የቶኪዮና ጀኔቫ ስምምነቶች ናቸው። በሀኪምና ቤተሰቦቹ ላይ የሚጋረጥባቸውን ማንኛውንም ጭቆና መፍትሄና ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ይደነግጋል።
ከላይ በተጠቀሱት መረጃወች መሰረት ዶ/ር ጋሹ የህሊና እስረኛ ብቻ ያደርገዋል። በዚህም መሰረት የሚከተሉት ህግጋቶችን በማክበር ሁሉም ሀኪምና ማህበራት የዶ/ር-ጋሹ-ክንዱን እስራትና ስቃይ በአስቸኳይ ለማስፈታት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የዐማራ ሀኪሞች እናምናለን።
1ኛ. በጅኔቫ የ1949 ዓ.ም አንቀጽ 6.1 መሰረት ሀኪም የህክምና ስነ ምግባርን አክብሮ እስካከመ ድረስ ማንም ይሁን ማን በምንም ምክንያት መቀጣት የለበትም።
2ኛ. የዓለም የህክምና ማኅበር የ1956; 1957 እና 1983 ዓ.ም ደንብ የሀኪም ተቀዳሚ ተግባር ሞያዊ ግዴታውን መወጣት ሲሆን፣  ህሊናውን ብቻ ተገዥ ያደርጋል፤ ይህን በማድረጉ በምንም ሁኔታ ወቀሳን ሊያመጣ አይገባም።
3ኛ. የኢትዮጵያ የህክምና ማኅበር አንቀጽ 7; 2010:  ዶክተር በሽታን ለመከላከልና ጤናን ለመገንባት የሚያስችል መረጃ መሆኑን ካመነበት ለሕብረተሰቡ ማስተማር ይችላል።
የህክምና ስነ-ምግባር መርሆችን በማክበር የሀኪምን እስራትና ስቃይ እንታደግ!
ሚያዚያ 2009 ዓ.ም
ከዐማራ ሀኪሞች ማኅበር
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment