Thursday, May 11, 2017

ኢህአዴግና ወጣቱ source mereja

የሰሞኑ የህወኃት/ኢህአዴግ ወጣቱን ማማለያ ውይይት ምን ይመስላል ? በሰሞኑ ህወኃት/ኢህአዴግ ‹ትንፋሽ› ለመውሰድ << በ ጥልቁ ተሃድሶ ወጣቱ፣ ሥራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ>> በሚል ከወረዳ እስከ ፌደራል ባሉት የወጣት አደረጃጀት መዋቅሮችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተከታታይ ውይይት — ተያይዟል፡፡ በመጨረሻም በ27/08/09 ዓ.ም በተጀመረው የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አገራዊ የውይይት መድረክ/ ጉባኤ ተጠቃሏል፡፡ ካለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ በመንግስት ቴሌቪዥን ካየነው ፣ በኢዜአና ኤፍኤም ሩዲዮኖች ከሰማነው የውይይቱ ዓላማ የታዘብነው በጥቅል የሚከተሉትን ያሳያል፡፡ 1. ህወኃት /ኢህአዴግ ጠያቂና ሞጋች ማኅበረሰብ ፈጠርን ባሉበት አፋቸው ዛሬም ወጣቱን የማያስብና የሚነዳ፣ ጥቅምና ጉዳቱን የማይለይ አድርጎ ፣ ዛሬም ወጣቱን ለማጭበርበር ‹በካድሬ› ወጣቶች ‹ጠያቂና ተሟጋች › ወጣት የተፈጠረ ለማስመሰል. . . እየተጣጣረ መሆኑን ፣ 2. ወጣቱ ‹በውጪ ኃይል ታዛዥ የጥፋት ኃይሎችና የቀለም አብዮት ተሳታፊ የመሆን ሥጋትና እንቅልፍ የነሳው መሆኑን፣ 3. ለሥራ አጡ ወጣት የተለመደውን ‹‹የላም አለኝ በሰማይ›› ቀለብ ለመስፈር እንጂ ለዘላቂ ለውጥ ያልተዘጋጀ መሆኑን፣ 4. ዛሬም ችግርን በሌላው ማላከክ፣ ችግራችሁ ገብቶናል ተቀብለናል፣ መዝግበናል፤ በቀጣይ በምናዘጋጀው መድረክ ኃሳባችሁን እናካትታለን በማለት የክፉ ቀን ለመሻገር የተወጠነ መሆኑን ፤ 5. እንዲሁም ዛሬም ወጣቱ ችግሩንና ጥያቄውን በህወኃት/ኢህአዴግ ዓላማ ዙሪያ ‹ብቻ› ተደራጅቶ ሲያቀርብ መፍትሄ የሚያገኝ ፣ ለራሱ መብትና ጥቅም በራሱ በነጻነት ተደራጅቶ ሊቀርብ እንደማይችል ለማስረገጥ/ለማሳመን ሲታትር፣ ታዝበናል፡፡ ትዝብታችን እናፍታታው፡፡ ሰሞነኛው ውይይት ለ25 ዓመታት ከተለመደው የውይይት መድረክ አመራር የሚለየው በአቀራረብ ብቻ ነው፡፡ በተሳታፊዎች የቀረቡትን ሁሉንም ኃሳብ በሁሉም አወያይ ‹ተቀብለናል› መባሉና የማስፈራሪያ ቃላትና ፍረጃዎች አለመኖራቸው ብቻ ሳይሆን ፣ በምሁራን አወያይነት መታጀቡ ነው ፡፡ ይህም ህወኃት /ኢህአዴግ ጭንቅ ሲለውና ብርክ ሲይዘው ከተለመደው ለየት ባለ አቀራረብ የተለወጠ/ለመለወጥ የተዘጋጀ ለማስመሰል የሚጠቀምበት ማጭበርበሪያ ስልት ነው፣ ክፉው ቀን ሲያልፍ የማያስታውሰው ፡፡ ይህ እውነት ባለበት ወደዚህ ዓይነት ትዝብት የዳረጋቸውን በውይይት መድረኩ የተነሱ አንዳንድ አብነቶችን እንመልከት፡፡ በደቡብ ቴሌቪዥን /ሚያዚያ 24 ቀን 2009/ በተለይ የብዙዎቹን ወጣቶች ኃሳብ በማጠቃለል ያቀረበውና ቀልቤን የሳበው፣ ቴሌቪዥኑም ደጋግሞ ያሳይ የነበረው አንድ ወጣት ያነሳቸውን ነጥቦች እንመልከት፡፡ ወጣቱ አገዛዙን ይህ ሁሉ ተደራራቢ ከአቅማችሁ በላይ የሆኑ ችግሮች ተከማችተው ለጥፋት ሲዳርጉ የት ነበራችሁ፣ አደጋው ከደረሰ በኋላ ፣ ልማትና ፋብሪካ ከወደመ፣ ት/ቤት ለወራት ከተዘጉ በኋላ ፣ አስቸኳይ አዋጅ 6 ወር ቆይቶ ከተራዘመ በኋላ፣…… ዛሬ ከየት መጣችሁ ? ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ፣ በተለያዩ መድረኮች በህዝብና ወጣቱ የተነሱ ጥያቄዎችና ሂሶችን ተቀብለናል ካላችሁ ለምን መፍትሄ አልሰጣችኋቸውም ነበር ? የተለየ ኃሳብ የሚያቀርበውን ወጣት በተቃዋሚነት እየፈረጃችሁ ሲታሸማቅቁ ከነበረበት ለመለወጥ የቱን ያህል ተዘጋጅታችኋል ? ተቀብለናል በማለት ያለፋችኋቸው ወይም ‹ይፈታሉ› እያላችሁ ስታዘናጉ የነበሩ ችግሮች መቼ አልተፈቱም ፣ሃሳቦችም አልተስተናገዱም በቀጣይ እንዴትና መቼ እንደሚፈቱና እንደሚስተናገዱ የትናንቱ እንደማይደገም ምን ማስተማመኛ አለ ? በማለት ወጣቶቹ ጠይቀዋል፡፡ እንደመፍትሄም የቀረቡ ኃሳቦች ሲጠቃለሉ፡- ‹‹ እዚያ በማዕከል /ፌደራል ደረጃ ተቀምጦ የሚደረስበት ውሳኔም ሆነ የሚሰራጭ ፕሮፖጋንዳ መፍትሄ አላመጣም፣ ከጥፋት አልታደገንም፡፡ ችግሩም ሆነ መፍትሄና ሥራው ያለው ታች በወረዳ ደረጃ ነው፡፡ እዚህ ብቻ ወይም በአንድ ዞንና ክልል ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ከዳር ዳር በወረዳና ቀበሌ ወርዶ የህዝቡን ትክክለኛ ጥያቄ ሳትረዱ ከካድሬዎች የሃሰት ሪፖርት ተነስቶ የሚደረስ ማጠቃለያ ውጤትና ለውጥ አላመጣም፣ አያመጣም፡፡ እስከዛሬ ህዝቡ የሚያምናቸውን የምወዳቸውንና የሚያከብራቸውን ሳይሆን ለእናንተ ታማኝ የሆኑትን ስትሾሙና ስትሽሩ በመኖራችሁ – አሁን መንግስትና ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር ተራርቆ ነው ያለው ፡፡ በቀጣይ ለመልካም አስተዳደር በሉት በህዝብ ተቀባይነት ለማግኘት በህዝብ ክብር፣ ተቀባይነትና ታማኝነት ያላቸውን ቢጣሩ አቤት የሚባሉ፣ ቢሸመግሉና ቢናገሩ የሚደመጡ፣ አመራሮችን ወደፊት አምጡ እንጂ የተለመደው መንገዳችሁ መፍትሄ አያመጣም፡፡ ዩኒቨርሰቲዎችን ት/ቤቶችን ተከትለው ጫትና ሺሻ ቤት፣ የምሽት ክለብ፣ ፑል ቤት ….. በዩኒቨርስቲና ሁለተኛ ት/ቤቶች ዙሪያ እየተስፋፉ ተማሪውን/ወጣቱን ለሱስና አደንዛዥ እጾች አጋልጠው ሲያደነዝዙና ከትምህርት ገበታው ሲያርቁ የመከላከል እርምጃ ሳትወስዱ፣ ስለወጣቱ ባህሪይ መበላሸት ፣ የሥራ ፈጣሪነት መላሸቅና የትምህርት ጥራት፣ የተመራቂዎች ልቀትና ተወዳዳሪነት መውደቅ …. ስትናገሩ እስከዛሬ በህዝቡ ውስጥ አልነበራችሁም እንደማለት ነውና ወጣቱን /ተማሪውን ከነዚህ ዓይነት የጥፋት ድጊቶች ተጋላጭነት የመከላከል የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንጂ ችግሩን መዘርዘር አያዋጣምና በቀጣይ አስቡበት፡፡ ከዚህ በፊት ከህወኃት/ኢህአዴግ የተለየ ኃሳብ የሚያቀርበውን ወጣት በተቃዋሚነት እየፈረጃችሁ በግልጽና ተዘዋዋሪ መንገድ ስትቀጡ የመኖራችሁ ሃቅ ከዚህ ህዝባዊ እምቢተኝነት አድርሷችኋል ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅና ማራዘም አስከትሏል ፡፡ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተጠቅማችሁ ትክክለኛ የችግሩን መንሥኤ ከሥረ መሰረቱ ለመረዳትና ዘላቂ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ችግሩን ወደሌላ ውጪ ኃይል በማላከክ ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ለማፈን ነው የምትሞክሩት ፣ አሁን ዬሚያስፈልገው ለጥያቄዎቹ የፕሮፖጋንዳ መልስ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ ነውና ከተለመደው መንገድ ውጪ ካላሰባችሁ የተለየ ውጤት አትጠብቁ፤ የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እንደሚጠናቀቅ ፣ ዘላቂ መፍትሄ ካልተበጀ የተጀመረው ህዝባዊ እምቢተኝነት እንደሚቀጥል አትጠራጠሩ፡፡ ›› የሚሉ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ የወጣቱን ተስፋ የማጣት ስሜት የሚያረጋግጡና በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጣ ሆኖም ከየስደት አገራት ወደአገር ቤት ላለመመለስ ከሚያሰማው ውሳኔ ውስጥ ወጣቱ በአገሩ ‹ሰው ለመሆን› ላለመቻሉ የደረሰበትን ድምዳሜና ፣ በግዳጅ ቢመለስም ባየውና ባለፈበት ከሞት ጋር ግንባር ለግንባር የሚያጋፍጥ ሁኔታ ውስጥ ዳግም ለስደት መዳረጉን አስታውሰን ወደ ቀጣዩ ክፍል እንሸጋገር ፡፡ በአወያዮች / የወጣቶች ፌደሬሽን ተወካይ ፣የኢህአዴግ የከተማና ገጠር ፖለቲካ አደራጆችና ‹ምሁራን. / የቀረበው ምላሽን ስንመለከት ደግሞ የሚከተለውን ሥዕል እናገኛለን ፡፡ የወጣቶች ፌደሬሽን ተወካዮች በአብዛኛዎቹ መድረኮች ተመሳሳይ ‹‹ ወጣቱን ከጠላት ኃይል ተጋላጭነትና የቀለም አብዮት አራማጅነት ለመከላከልና ለመመከት ብቻ ሣይሆን የልማትና ዲምክራሲና መብት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በዘላቂነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ምሁራንን በመጠቀም/በማሳተፍ ስለህገመንግስት ሰነድ እናዘጋጃለን፣ ወጣቱን የሚያካትትና ተጠቃሚነቱን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ የልማት ፖሊሲ እናዘጋጃለን፣ የወጣቱን ሃሳብ ለመፍትሄው ግብዓትነት እንጠቀማለን፣ ለዚህም ተከታታይና ቀጣይነት ያለው የምክክር መድረክ እናዘጋጃለን ፣ እናወያያለን … ፡፡ ›› በማለት ምላሽ የሰጡ ሲሆን ይህም መልስ እንጂ መፍትሄ ካለመሆኑም ከህወኃት/ ኢህአዴግ ፈቃድ/ይሁንታ ውጪ በወጣቱ ፌዴሬሽን ስላለው/ ስለፈለገ ተፈጻሚነቱ አጠያያቂ ነው ፡፡ ለዚህ ደግሞ በደቡብ ክልል በተደረገው ውይይት ምሁሩ አወያይ የዲላ ዩኒቨርስቲ ም/ፕሬዝዳንት — ወጣቶች ከገለጹት ችግሮች በተቃራኒ ‹‹ ለዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር የቆረጠ ፣ በውጪ ለሚታዘዝ የጠላት ኃይልና የቀለም አብዮት አራማጆች የማይነበረከክ….. መንግስት አለን፡፡ ›› በማለት ያቀረቡት መወድሰ-መንግስት ህወኃት/ኢህአዴግ መድረኩን ለምን እንዳዘጋጀው የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን የወጣቶች ፌደሬሽን ምሁራንን አሳትፈን/ተጠቅመን የተለያዩ የወጣቱን መብትና ጥቅም የሚያረጋግጡ ‹ሰነዶች› ይዘጋጃሉ ያሉን እኒህ ዓይነቶቹን ‹ምሁራን › ከሆነ የሰነዶቹን ይዘት ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ያሳያል ፡፡ በተጨማሪ ፕ/ት ዶ/ር ሙላቱ ተሸመ ደግሞ እንዲህ ይሉናል ( ኢቢሲ 27/08/09) ‹‹ ……የተጀመረው ህዳሴ በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲቆም የኢትዮጵያ ወጣቶች ፈዴሬሽን ድርሻ የጎላ ነው›› ፡፡ ልብ አድርጉ የተባለው የኢትዮጵያ ወጣቶች ፈዴሬሽን እንጂ የኢትዮጵያ ወጣቶች አይደለም፤ ስለዚህ ወጣቱ የጎላ ድርሻ እንዲኖረው በኢህአዴግ ሥር መደራጀት አለበት ወይም በኢህአዴግ ፌደሬሽን አልደራጀም ያለ ወጣት ብልጭ ብሎ በህወኃት ድርግም እንደተደረገው እንደትናንቱ ‹‹የባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር›› በነጻ ተደራጅቶ ድርሻውን ማበርከት አይችልም ማለት ነው፡፡ ይህ በመንግስት ለወጣቱ የተቀመጠለት አቅጣጫ የት እንደሚያደርስ በጊዜ ውስጥ የምናየው ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ከሰሞኑ ከወጣቱ ጋር ከተደረጉ የውይይት መድረኮች የታዘብነውና አዋጪና ዘላቂው መፍትሄ ሲጠቃለል ፡- በ26 የህወኃት/ኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመናት ወጣቱ ከዲሞክራሲው ሥርጸት፣ ከባለሁለት ዲጂቱ ዕድገት፣ ከዕውቀት በረከትና የፖለቲካ ሰበካው ሣይሆን ከኑሮውና ከተለመደው ‹‹ ላም አለህ በሰማይ ›› የፕሮፖጋንዳ የተስፋ ዳቦ ( ከሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር አንጻር በወጣት ከመቶ ብር ከማያልፈው 10 ቢሊየን ብር መመደብ ጨምሮ ) በተቃራኒ በተጨባጭ በህይወቱ ካገኘው ተሞክሮ ከጠያቂና ሞጋችነት አልፎ ወደ ‹አብዮታዊ ታጋይነት › ተሸጋግሯል፡፡ የተለመደውን የህወኃት ፕሮፖጋንዳና እየተራመደ ያለው የዘር ፖለቲካና የከሸፈ አመራር ፣ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ … ‹በቃኝ› ብሏል፡፡ ከዚህ በኋላ በህይወቱ በቀጣይነት በማይጨብጠው የተስፋ ዳቦ አስገማጭ ዕቅድ/ፖሊሲና በቴሌቪዥንና የፕሮፖጋንዳ መድረኮች በሚቀርብለት ‹ብፌ› እንዲሁም በየስብሰባው በሚቀርብለት የ50 ብር አበል፣ ቁራጭ ማስታወሻ፣ ምሳ፣ የታሸገ ውሃና ኩኪስ ሊታለል እንደማይችል እንረዳለን ፡፡ በመሆኑም ዘላቂ መፍትሄው ደጋግመን እንዳልነው የቁጩ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶና ድርድር›› ሥም የሚከናወን የፕሮፖጋንዳ ውይይት ገለመሌ አይደለም፤ ብቸኛውና ዘላቂው መፍትሄ የወጣቱ መብትና ፍላጎት በወጣቱ የሚንጸባረቅበት በአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ሃይሎች፣ የማኅበረሰብ ነጻ አደረጃጀቶችና የህዝብ ተወካዮችን በሙሉ አካታች – አሳታፊ የብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ መድረክ መክሮና ዘክሮ የሽግግር መንግሥት መመስረት ›› መሆኑን እንረዳለን፡፡ ግርማ በቀለ ወ/ዮኃንስ፡፡ ግንቦት 02/2009 ዓ.ም›




No comments:

Post a Comment