Thursday, May 11, 2017

ቴዲ አፍሮ ከኢትዮኒውስፍላሽ እና ኤፒ ሪፖርተር ኤልያስ መሰረት ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ source zhabesha

ቴዲ አፍሮ ከኢትዮኒውስፍላሽ እና ኤፒ ሪፖርተር ኤልያስ መሰረት ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ

ጥያቄ: የአዲሱ ‘ኢትዮጵያ’ አልበምህ ዋና መሰረት እና ለመዳሰስ የሚሞክራቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ቴዲ: አርእስቱ ‘ኢትዮጵያ’ እንደመሆኑ መጠን ዋናው አላማ ኢትዮጵያዊነትን ከአደጋ ማዳን ነው። ይህ አልበም በዚህ አይነት ሀሳብ ላይ እንዲያተኩር የፈለግኩበት ምክንያት አንድነታችን አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ብዙ አመት ተደክሞበታል። አሁን እንደሚታወቀው በሀሳብ ከመደራጀት ይልቅ በዘር መደራጀት ይታያል። ያ ደግሞ አዝማሚያው ወደ አደጋ ያመጣው ይመስላል። እና ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ማዳን አላማ አድርጎ ነው የተሰራው።
ጥያቄ: እንዳልከው አንዳንዶቹ ስራዎችህ በኢትዮጵያውያዊነት እና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያጠነጥናሉ። እዚህ ላይ በጣም ትኩረት ለማረግ የፈለግክበት የተለየ ምክንያት ምንድን ነው?
ቴዲ: አገር እንግዲህ ብዙ ግዜ የሚቆመው ለሀገር ባለውለታ በሆኑ ሰዎች እና ብዙ የህብረተሰቡ አካላት በሚሰሯቸው ተግባራት ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊነት በነፃነት የመኖር ምልክት ነው። ድል ለማግኘት ምኒሊክን የመሰለ ጥሩ መሪ ያስፈልጋል። እንደገና ደግሞ እንደ ሀይለስላሴ ያሉ ትላልቅ ነገስታት ከአለም መንግስታት ጉባኤ ጀምሮ ያደረጓቸው አስተዋፆዎች እና የነበራቸው ተቀባይነት፣ ለሀገራቸው የሰሩት ተግባር ሳይደመር ኢትዮጵያ የምንላት ሀገር ልትኖር አትችልም። ይህ እንዳለ ሆኖ ምንግዜም ነገስታት የሚወክሉት ህዝብን እንደመሆኑ መጠን ከስሮቻቸው ደግሞ ያሉ ብዙ ባለውለታዎቻችንን እብሮ ለማየት የሚያስችል ትልቁ መስኮት ከፊት ያሉት ሰዎች ናቸው። በዚህ መሰረት ምልክቶች ካልተበረታቱ እና የሚገባቸውን ክብር ካላገኙ የሚቀጥለው ትውልድ ጥሩ ተግባር ለመፈፀም የሚያነቃቃ መሳርያ አያገኝም። ሁለተኛ ደግሞ ባለፉት ጥቂት አመታት ታሪክ የሚባለው ነገር እና ብሄራዊ ስሜት በብዙ ሁኔታ ፈተና ውስጥ ወድቋል። ስለዚህን ይሄንን አጠናክሮ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የትውልድ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። እኔ ደግሞ የዚህ ትውልድ አካል እንደመሆኔ መጠን ያንን ተግባር ለመፈፀም ነው የሞከርኩት። አፄ ቴዎድሮስ ደግሞ እንደሚታወቀው በአንድ ወቅት ዘመነ መሳፍንት በሚባለው እና ኢትዮጵያ በጎሳ መሪዎች እና በጎበዝ አለቆች ተከፋፍላ በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ህልም ይዞ ተነስቶ ከውጪ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም በገጠመው ብዙ የመረዳት ችግር ባክኖ የወደቀ ትልቅ ጀግና ነው። ከምንግዜውም በላይ ደግሞ የእርሱ መንፈስ አሁን አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ ምክንያቱም አስተሳሰባችን አገር ማከል አለበት።
ጥያቄ: በርካታ ሰዎች አዲሱ አልበምህ ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሰሩ የሙዚቃ ስራዎች በብዙ ረገድ የገዘፈ እና በሽያጭ ረገድም ሪከርድ የሰበረ ነው ይላሉ። ምን ያህል አልበም ታተመ እና ተሸጠ? አንተስ ይህንን ያህል ተቀባይነት ገምተህ ነበር?
ቴዲ: እውነት ለመናገር ከተለመደው ውጪ ይመስላል። ምን ያክል ኮፒ እንደተሸጠ ግን ለመግለፅ የሚችሉት አሳታሚዎቹ ናቸው። እና ስራው ወደ 600,000 ኮፒ አካባቢ ታትሞ እንደነበር አውቃለሁ። ይሁንና አሁን ያለውን ያክል ተቀባይነት ያገኛል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር።
ጥያቄ: ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ በአሁን ሰአት ለየት ባለ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ብዙ ሰዎች ደግሞ ቴዲ አፍሮ በቀደምትም ይሁን በአሁን ስራዎቹ የፖለቲካ መልእክቶችን አስተላልፏል ይላሉ። በስራዎችህ ላይ እነዚህን መልእክቶች አስተላልፈሀል? ከሆነስ እነዛ መልእክቶች ምንድን ናቸው?
ቴዲ: በኔ እምነት ብቻም ሳይሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ማንም ሰው ከፖለቲካ ውጪ ሊሆን አይችልም። የፖለቲካዊ ጉዳይን ማንሳት ደግሞ እንደ ኩነኔ የሚታይ ነገር መሆን የለበትም። ሁላችንም ጉዞአችን አንድ እንደመሆኑ መጠን የኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳይ እንደ ዜጋ ይመለከተናል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማተኮር መለመድ እና መበረታታት አለበት። የነገሮቹ ጥልቀት በአልበሙ ላይ በዝርዝር ተጠቅሰዋል።
…ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment