Wednesday, February 1, 2017

የአማራ ህዝባዊ ተቃውሞን (#AmharaProtests) ተከትሎ የተቃውሞ ድምጽ በሚያሰሙ ዜጎች ላይ እስርና ወከባው ቀጥሏል







በተቃውሞ ሰልፎች የተሳተፉ ወጣቶችን በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በገፍ ማሰሩ ተቃውሞዎች በበረቱባቸው ከተሞች ከፍተኛ ነው ፡፡ ለምሳሌ በጎንደር ከተማ በሚገኙ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ፖሊስ ጣቢያዎች በጠባብ ክፍሎች ውስጥ በአንድ ጣቢያ በአማካይ እስከ 140 ሰዎች እንደሚታሰሩ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ጎንደር ከተማ ውስጥ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ለሁለት ሳምንታት ታስሮ የነበረ ወጣት ደረጀ ጌቱ (ስሙ የተቀየረ) እንደሚናገረው በጣቢያው ውስጥ አብረውት ታስረው የነበሩት አብዛኞቹ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ መሳተፋችሁ በፎቶ ተረጋግጧል በሚል ለእስር ተዳርገው የነበሩ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲሁ በከተማዋ ተደርጎ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት በተሳተፉ ወጣቶች በገፍ እየታሰሩ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ ሲታሰሩ እና ሲፈቱ ሌሎች ደግሞ በተደጋጋሚ መታርና መፈተታ እንደሚገጥማቸው ማየት ተችሏል፡፡
በእነዚህ ፖሊስ ጣቢያዎች የሚታሰሩትን ማን እንደታሰረና፣ የት እንደታሰረ ቤተሰብና ዘመድ የማወቅ እድል ቢኖረውም ሌሎች የት እንደታሰሩ ሳይታወቅ ለቀናት፣ ለሳምንታትና ለወራትም የሚከርሙ መኖራቸውም ታውቋል፡፡ እነዚህ የእስር ስፍራዎች በይፋ የማይታወቁና በተቃውሞ እንቅስቃሴው እጃቸው በሰፊው አለበት በሚል መንግስት የጠረጠራቸውን “የሚመረምርባቸው” ናቸው፡፡
ከእነዚህ ድብቅ የእስር ቦታዎች መካከል ለምሳሌ ባህር ዳር አባይ ማዶ ከብአዴን ጽ/ቤት ጀርባ የሚገኝ ቀድሞ የመሳሪያ መጋዘን የነበረ ስፍራ ይገኝበታል፡፡ በዚህ ቦታ የሚታጎሩ ወጣቶችን ቤተሰቦቻቸው ለመጠየቅም ሆነ በዚያ ስፍራ ስለመኖር አለመኖራቸው ለማወቅ እንደማይችሉ ታስረው የተፈቱና፣ ታስረው እንደነበርም እንዳይናገሩ ማስፈራሪያ ደርሷቸው የወጡ ይመሰክራሉ፡፡ አበበ አስረስ (ስሙ የተቀየረ) በዚህ ድብቅ የእስር ቦታ ለ17 ቀናት ሲሰቃይ ቆይቶ መለቀቁን ይናገራል፡፡
‹‹ቦታው የሆነ መጋዘን ነገር ነው፤ ሰፊ አዳራሽ ነው፡፡ በዚህ አዳራሽ ውስጥ በጣም ብዙ ሰዎች አብረውኝ ታስረው ነበር፡፡ የእስራችን ምክንያት ብለው የነገሩን ባህር ዳር ነሐሴ 01/2008 ዓ.ም በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ሰልፉን አደራጅታችኋል የሚል ነው፡፡ በእስራችን ጊዜ ቤተሰቦቻችን አንድም ቀን አላገኙንም፡፡ በኋላ ብዙዎችን ወደ ብርሸለቆ ሲወስዷቸው እኔን ድጋሜ ሰልፍ ላይ ካገኘንህ እንገድልሃለን ብለው ዝተውብኝ የሆነ ወረቀት ላይ አስፈርመው ለቀውኛል፡፡ ማታ ላይ ነው በመኪና ከሌሎች ሦስት ልጆች ጋር ጥለውኝ የሄዱት›› ሲል ያስታውሳል አበበ፡፡
አበበ አስረስ ከድብቅ እስር ቤቱ መፈታቱን ተከትሎ ዘመድ ለመጠየቅ በሚል ከአካባቢው ዞር ለማለት አስቦ የቤተሰቦቹን ምክር ተቀብሎ ወደ አዲስ አበባ ዘመድ ጋር ሳምንታትን አሳልፏል፡፡ ‹‹በጣም ከባድ ጊዜ ነበር እስር ላይ ሆኜ ያሳለፍኩት›› የሚለው አበበ፣ ከሳምንታት የአዲስ አበባ ቆይታ በኋላ የገና በዓልን ከቤተሰቦቹ ጋር ለማሳለፍ ወደ ባህር ዳር በተመለሰበት ወቅት፣ ‹‹የት ጠፍተህ ከርመህ እንደመጣህ እናውቃለን!›› በሚል በድጋሜ ለእስር እንደተዳረገ ታውቋል፡፡
በድብቅ እስር ቤቶችም ሆነ በፖሊስ ጣቢያዎች የሚታሰሩ ሰዎች የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን፣ በተለይ ድብደባ በብዙዎቹ ላይ በምርመራ ወቅት የሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ በባህር ዳር ከተማ 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በምርመራ ወቅት ጥፍርን እስከመንቀል የሚደርስ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ይፈጸምባቸዋል፡፡
ብዙዎች በፖሊስ ጣቢያ ለሳምንታት እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ወደ ብርሸለቆ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም ለ‹ተሃድሶ ስልጠኛ› ተግዘዋል፡፡ በማሰልጠኛ ተቋሙ በሚኖራቸው ቆይታም ቢሆን ተመሳሳይ፣ አንዳንዴም የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸዋል፡፡ (በተሃድሶ ማሰልጠኛ ስፍራዎች ስለሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት በቅርቡ ለማሳያነት ይፋ ያደረገውን ሪፖርት መመልከት ይቻላል፡፡)
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት በዋናነት ቀድሞውንም በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ በሚታገሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ያነጣጠረ የእስር እርምጃ ሲወስድ ታይቷል፡፡ በተለይ በክልሉ በስፋት በሚንቀሳቀሱት የሰማያዊና መላው ኢትዮጵያ አንድነት ( መኢአድ) ፓርቲዎች አባላት ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ብዙዎች በየአካባቢው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው ሲገኙ፣ አንዳንዶች ደግሞ ወደፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከላል (ማዕከላዊ) ተላልፈው ጥቂቶች የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ፕሮጄክታችን ባደረገው ተጨማሪ ማጣራት ከብዙዎቹ መካከል የሚከተሉትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አክቲቪስቶች መታሰራቸው የሁኔታውን አሳሳቢነት ያሳያል በማለት አቅርበነዋል፡፡
*ከአማራ ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርገው የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው:-
1. ንግስት ይርጋ…………… የመብት ተሟጋች፣ አድራሻ ጎንደር…. ቃሊቲ እስር ቤት ታስራ ትገኛለች
2. አለምነው ዋሴ……………የመኢአድ አባል……….አድራሻ ጎንደር….. ቂሊንጦ በእስር ላይ ያለ
3. ቴዎድሮስ ተላይ……….አድራሻ ጎንደር……………………………………. ›› ››
4. አወቀ አባተ……………….የመኢአድ አባል……………………………… ›› ››
5. በላይነህ አለምነህ……………የሰማያዊ ፓርቲ አባል፣ አድራሻ ባህር ዳር……. ›› ››
6. ያሬድ ግርማ…………………. የመኢአድ አባል…………………………………>>
7. አታላይ ዛፌ
*ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት
7. ማሩ ዳኛው
8. ቢሆን
9. መልካሙ ታደለ
10. ሲሳይ ታፈረ
11. ወርቁ ጥላሁን
12. ድንቁ
13. ስማቸው ማዘንጊያ
14. እያዩ መጣ
15. ድርሳን ብርሃኔ
16. አንዳርጌ አባይ
17. ዮናስ ሰለሞን
18. መሃመድ ኑርየ
19. መምህር መሃመድ አሊ
20. መንግስቴ ብርሃኔ
21. ጌታነህ ደምሴ
22. ታደለ እንዳልፈራ
23. መምህር ለወየሁ ጌቱ
24. እሸቴ ደረሰ
25. ጌጤ ላሽተው
26. ሰይዒድ እንድሪስ
27. አህመድ በዛብህ
28. ጀማል ኡመር
29. አብደላ መሃመድ
30. አዲሱ ጌታነህ
31. ዘሪሁን እሸቱ
32. ጀማል ይመር
33. አበበ ጥላሁን
34. ተሻገር ወልደሚካኤል
35. እያሱ ሁሴን
36. በላቸው አወቀ
37. ዘውዱ ነጋ
38. ወልደመስቀል ማማየ
*የህዝቡን የመብት ጥያቄ (ህዝባዊ ተቃውሞ) ደግፋችኋል በሚል ከታሰሩት መካከል፡-
39. ገድፍ ጌታነህ……ሰሜን ጎንደር በለሳ ወረዳ
40. ሊቀሊቃውንት እዝራ (ቤተ-ክርስቲያንን ሽፋን አድርገው የህዝቡን ተቃውሞ ይደግፋሉ በሚል የታሰሩ)
41. ቀለመወርቅ ዓለሙ (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የጎንደር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ኃላፊ)
42. ሂሪያኮስ አበበ…..ጎንደር ከተማ
43. ዶ/ር ጋሹ ክንዱ
(ዶ/ር ጋሹ ክንዱ የቡሬ ዳሞት ሆስፒታል ሜዲካል ዳሬክተር ናቸው፡፡ ታህሳስ 27/2009 ዓ.ም ለገና በዓል ወደ ቤተሰቦቻቸው ባመሩበት ጊዜ ባህር ዳር ከተማ ለእስር ተዳርገው ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እንዲዛወሩ ተደርገው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡) የፕሮጀክታችንን የአማራ ህዝብ ተቃውሞ እና የመብት ጥሰት ሪፓርት ለማግኘት ይህንን ሊንክ ይጫኑ፡፡
(በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) የተዘጋጀ)

No comments:

Post a Comment