Monday, October 16, 2017

አባዱላ ገመዳ የለቀቁበትን ምክንያት በዝርዝር አስረዱ source zehabesha

ምክንያት በዝርዝር አስረዱ
 



ከላይ በቀረበው የአባዱላ ንግግር ላይ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሸፈራው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል::
ስለ ኦህዴድ ብዙ ብዙ እየተባለ ነው። አባዱላ የህዝብና ድርጅት ክብር ስለተነካ ለቅቄያለሁ ብሏል። በመሰረቱ የህዝብ ክብር አሁን አይደለም የተነካው። ብዙ ሳንርቅ በ2008 እነ አባይ ፀሃዬ፣ እነ ጌታቸው ረዳ በህዝብ ላይ ምራቅ ሲረጩ እነ አባዱላ ጭጭ ብለው ነበር። ዛሬ ነቃን፣ መረረን፣ በዛ ካሉም መልካም ነው።
በ2008 የተነሳው ህዝባዊ ንቅናቄ ትንፋሽ ሲያሳጣቸው ሚዲያውን መግለጫ በመግለጫ አድርገውት ነበር። በዋነኛነት ችግሩ የህዝብ ሳይሆን የኢህአዴግ ነው ብለዋል። ይህን ብለው ግን በዚሁ ንቅናቄ ሰበብ የታሰሩትን አልፈቱም። እንዲያውም የሀሰት ክስ ቀርቦባቸዋል። የኢህአዴግ ችግር ነው በተባለው ጉዳይ የሀሰት ክስ ከቀረበባቸው መካከል እነ አቶ በቀለ ይገኙበታል!
እነ አቶ በቀለ የቀረበባቸውን የሀሰት ክስ ተከላከሉ ተብለው ለጥቅምት 27፣ 28 እና 29 ቀጠሮ ተይዟል። ለዚህ የሀሰት ክስ በምስክርነት የጠሩት ደግሞ ችግሩ የህዝብ ሳይሆን የእኛ ነው ብለው ህዝብን ይቅርታ የጠየቁትን እነ አባዱላ ገመዳ እና እነ ለማ መገርሳን ነው!
እነ አቶ በቀለ የተከሰሱት እነ አባዱላ ገመዳ ክብሩ ተነክቷል ያሉትን ህዝብ አነሳስታችሁዋል፣ አሳምፃችሁዋል ተብለው ነው። ጥቅምት27፣ 28ና 29 እነ በቀለ የሚያስመሰክሩት ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን በገዥዎቹ ስለተፈረጀው፣ ሽብር፣ አመፅ ፈጥሯል ተብሎ ለሚከሰሰው፣ አሁንም በየ ፍርድ ቤቱ ስሙ ሲነሳና ክብሩ ሲነካ ለሚውለው ህዝብ ነው!
እውነት እነ አባዱላ ፣ እነ ለማ ስለ ህዝብ ክብር ካሰቡ ጥቅምት 27፣ 28ና 29 ፍርድ ቤት ቀርበው እውነታውን፣ ቢያንስ ያኔ መግለጫው ላይ የሰጡትን ቃል ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል! ባለስልጣናት በምስክርነት ተጠርተው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተልኮላቸዋል ተብሎ ያልቀረቡበት ጊዜ አለ።
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያው ብዙ ለተባለላቸው የኦህዴድ ፖለቲከኞች ጥቅምት 27፣ 28ና 29 ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል! የመጀመርያው ለምስክርነት መቅረብ አለመቅረባቸው ነው! አይቀርቡም እንጅ ከቀረቡ ለመስቀለኛ ጥያቄው ከአሁኑ ፀሎት፣ ምህላ ማስደረግ ይጠበቅባቸዋል! ምክንያቱም ምስክርነቱ ከህዝብ ወይንም ከትህነግ ጋር እንደሚያቀያይማቸው እሙን ነው!

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከ እስር ከተፈታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለምልልስ ሰጠ – “እናቴን በደህና በማግኘቴ ከፍ ያለ ደስታ ተሰምቶኛል


ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለምልልስ ሰጠ – “እናቴን በደህና በማግኘቴ ከፍ ያለ ደስታ ተሰምቶኛል”

Thursday, October 5, 2017

ተመድ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራር አቶ አንዷለም አራጌ እንዲፈታ ጠየቀ


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው አቶ አንዷለም አራጌ እንዲፈታ ጠየቀ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት አቶ አንዷለምን ያሰረው ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌዎችን በመጣስ እንደሆነ የገለጸው ተመድ፣ በመሆኑም መንግስት ፖለቲከኛውን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ አሳስቧል፡፡ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንደገለጸው ከሆነ፣ አቶ አንዷለም አራጌ ለእስር የተዳረገው ያለ ምንም ጥፋት እና በደል ነው፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተለው ቡድን ባወጣው መግለጫ ላይ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የጸረ ሽብር አዋጁን በመጠቀም ህጋዊ የፖለቲካ ሰዎችን እያጠቃ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ መግለጫው ይቀጥልና፣ አቶ አንዷለም አራጌ ለእስር የተዳረገውም የጸረ ሽብር ህጉን በመቃወሙ እንደሆነም ያትታል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አቶ አንዷለም አራጌ ብቻ ሳይሆን ባልንጀሮቹ ጭምር ከእስር እንዲፈቱ የኢትዮጵያ መንግስትን አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኘው ስርዓት እጅግ አስከፊ መሆኑ በተለያየ ወቅት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይህን ጉዳይ የሀገሬው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ዓለም ዓቀፍ ተቋማት እና መንግስታት ጭምር እየመሰከሩት ያለው ሐቅ ከሆነም ሰነባብቷል፡፡ በሕወሓት የሚመራው ይኸው ስርዓት፣ ለስልጣኑ የሚያሰጉትን ፖለቲከኞች ሁሉ እስር ቤት አስገብቷል፡፡ ከአንጋፋ ፖለቲከኞች ጀምሮ ገና ወጣት የሆኑ ፖለቲከኞችን እስር ቤት በማስገባት እየተበቀላቸው የሚገኘው አገዛዙ፣ ሰብስቦ ባሰራቸው ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ታጋዮች የተነሳ ከዓለም ዓቀፍ የመብት ተከራካሪዎች ከፍተኛ ውግዘት እየገጠመው ይገኛል፡፡

Friday, September 15, 2017

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው source zhebsha

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በኦሮሞ ተወላጆች ላይ እየፈጸመ ያለው ጥቃት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉ ታወቀ፡፡ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንዳመለከቱት፣ በሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ከባድ ውጥረት አለ፡፡ ውጥረቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሔዱን የገለጹት የአካባቢው የዓይን እማኞች፣ በተለይ በሶማሌ ክልል የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችን የማፈናቀል ድርጊት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን እማኞቹ አክለው ተናግረዋል፡፡

ልዩ ኃይል የተባለው የሶማሌ ክልል ፖሊስ ህወሓት ለክልሉ ፕሬዚዳንት ለአቶ አብዲ በሚሰጠው ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚመራ ሲሆን፣ ልዩ ፖሊሱ በንጹኃን ሰዎች ላይ ግድያ እንዲፈጽም እየተደረገ ያለውም በህወሓት ሴራ ሆን ተብሎ እንደሆነ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ህወሓት በኦሮሞ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ መካከል ግጭት እንዳለ በማስመሰል የፖለቲካ ጨዋታ ለመጫወት እየሞከረ መሆኑንም ታዛበዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹ድርጊቱ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡›› ያሉት ታዛቢዎቹ፣ ህወሓት በመጨረሻው ሰዓት በሀገሪቱ ላይ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር እንደሚፈልግም ያክላሉ-ታዛቢዎቹ፡፡

በምስራቅ ኢትዮጵያ ሐረርጌ ልዩ ስሙ ሜኢሶ በተባለው አካባቢ ያለው ውጥረት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልም ደረስ መጣ እያለ ጥቃት እንደሚፈጽም ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ግጭት ተከስቶባቸዋል በተባሉ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሰፍረዋል ቢባልም፤ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ግን አሳቻ ሰዓት እየጠበቀ ጥቃት እንደሚፈጽም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የህወሓት አጋዚ ወታደሮች ሐረር ውስጥ ግድያ ፈጸሙ source zhebesha

በሐረር የተሰማራው የህወሓት አጋዚ ሰራዊት ግድያ ፈጸመ፡፡ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በኦሮሞ ተወላጆች ላይ እየፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ጥቃት ለመቃወም በሐረር ከትላንት ጀምሮ ህዝባዊ ተቃውሞ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ዛሬም ቀጥሎ የዋለውን የህዝብ ተቃውሞ ተከትሎ የአጋዚ ወታደሮች ወደ ተቃውሞ አቅራቢዎች በቀጥታ በመተኮስ የሰው ህይወት መቅጠፋቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የሟቾች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ አልታወቀም፡፡

ከሟቾች በተጨማሪም በጥይት ተመትተው የቆሰሉ ንጹኃን ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት መረጃዎች፣ ሐረር በከባድ ውጥረት ውስጥ እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡ በተለይ ሸዋ በር ተብሎ የሚጠራው የሐረር አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር ከዓይን እማኞች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ እስከ ምሽት ድረስ የቀጠለው የተኩስ ድምጽ ሐረርን የጦርነት ቀጠና እንዳስመሰላት የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በጅጅጋ ይኖሩ በነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ በፈጸመው ጥቃት ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል፡፡ በዛሬው ዕለትም የሟቾች አስከሬን ወደ ሐረር ሲጓጓዝ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ ትዕዛዝ ከጅጅጋ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ሐረር እየተወሰዱ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችም ሐረር ያለመጠለያ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት የሆነው ህወሓት፣ የሀገሪቱን ህዝብ እርስ በእርስ ለማባላት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች፣ ፈታኝ ጊዜ ላይ በመሆናችን በአንድነት ልንቆም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
BBN news September 14, 2017

Tuesday, September 5, 2017

ጀዋር መሐመድ መንግስት በቴዲ አፍሮ ላይ እየወሰደ ያለውን ተደጋጋሚ ክልከላ አወገዘ source zhabesha

(ዘ-ሐበሻ) የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዳይሬክተር ጀዋር መሐመድ አምባገነኑ የሕወሓት መራሹ መንግስት በቴዲ አፍሮ ላይ በተደጋጋኢ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አወገዘ::
“ገዥው አካል ለቴዲ አፍሮ የሚያቀርበውን ትርዒት በተደጋጋሚ በመሰረዙ ተገቢ ያልሆነ እና ኢፍትሃዊ ውሳኔ ነው” ያለው ጀዋር በቴዲ ላይ መንግስት የሚወስደው ክልከላ “ይህ ሁሉ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነትን እና ዒላማው የኪነጥበብ ጥቃትን ስለሚያካትት ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል” ሲል በፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፏል::
ይህ የመንግስት ኪነጠብን የማፈን ተግባር አዲስ ነገር አይደለም አይደለም ያለው ጀዋር “መንግስት ከማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የበለጠ ስነ-ጥበብ እና አርቲስቶችን ይፈራል::” ካለ በኋላ ሥርዓቱ በኦሮሞ አርቲስቶች ላይም ከስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የወሰደውን ጥቃት ጠቅሷል::

እንደጀዋር ገለጻ ሕወሓት መራሹ መንግስት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ የኦሮሞ አርቲስቶችን ገድሏል፣ አስሯል እና ከሃገር እንዲሰደዱ አድርጓል::

ኦነግ በኦሮሚያ የሚደረገውን አድማና ትግል እየመራ መሆኑን አስታወቀ source zhabesha

ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በቅርቡ የተደረገውን ቤት የመቀመጥ አድማ ጨምሮ በኦሮሚያ ወጣቶች በአፋኙ ስርዓት ላይ የሚያደርጉትን ትግል ከፊት ሆኜ እየመራሁት ነው ሲል አስታወቀ።
ድርጅቱ በኤርትራ አስመራ ለአስር ቀናት ያደረገውን ጉባዔ ሲያጠቃልል ባወጣው መግለጫ የኦነግ ክንፍ የሆነው የኦሮሞ ወጣቶች ክንፍ (ቄሮ) እያካሄደ ያለው ትግል ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን አስምሮበታል።
ኦነግ ለቄሮ የሚያደርገውን ድጋፍ በሶስት እጥፍ በማሳደግ በቀጣዮቹ ወራት በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለማስወገድ እንደሚንቀሳቀስ ተናግሯል።
ለኦሮሞ ነፃነት የሚታገሉ ድርጅቶች ሁሉ ከጎኑ እንዲሰለፉ የጠየቀው ኦነግ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ጦርን ወደተግባር ለማስገባት የገንዘብ የቁሳቁስና የሰው ሀይል አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ለማሰደግ እየሰራሁ ነው ብሏል። ደጋፊዎቹም ለዚህ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የጠየውቀው መግለጫው ከሌሎች ከተጨቆኑ የኢትዮጵያ ብሄሮች ጋር ለመተባበር ዝግጁ ነኝ ብሏል።
አስመራ የሚገኘው ኦነግ ከሶስቱ ዋና ዋና የኦነግ አንጃዎች አንዱ ሲሆን በአቶ ዳውድ ኢብሳ ይመራል።
በቅርቡ በኦሮሚያ የተደረገውንም ሆነ ሌሎች አድማና አመፃችን በማስተባበር በውጪ ሀገር ያሉ አክቲቪስቶች በተለይም የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሀመድ ሀላፊነቱን ወስዶ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል።